አዲስ አበባ፡- አስራ ሁለተኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ አላማችን የብዝኃነታችን ድምር ውጤትና የአንድነታችን ምሰሶ ነው” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ እንደሚከበር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።
ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 3 የተቀመጠውን የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ትርጓሜ መሰረት በማድረግ የወጣ የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 እንዲሁም በተሻሻለው አዋጅ
ቁጥር 863/2006 አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንዲከበር ተደንግጓል።
ባለፉት ረዥም ዓመታት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሀገሪቱ ነፃነት የተደረጉ ትግሎች የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነት መገለጫና ለህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ምልክት መሆኑ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ሥራ መሰራቱን ምክር ቤቱ በመግለጫው ጠቅሷል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ ሲከበር በሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ ጥናቶች እየቀረቡ ግልጽነት ቢፈጠርም ሰንደቅ ዓላማው ሉዓላዊነት መገለጫና ለህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ምልክት መሆኑ ላይ የጎላ ልዩነት ባይኖርም በዓርማው ላይ ግን በሚፈለገው ደረጃ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር አለመቻሉን ተናግሯል።
እንዲህ ዓይነት ልዩነቶች ሲኖሩ በህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ከሕዝብ ጋር በሚኖር ውይይት የሚነሱት ጥያቄዎች እየተመለሱና መግባባት እየተፈጠረባቸው እንደሚሄድ ጠቁሟል።
የዘንድሮ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል መከበር የሚነሱትን የተለያዩ ጥያቄዎች ለህዝብ በማቅረብ በለውጡ ሂደት ላይ ተቀራራቢ ግንዛቤ ለመፍጠር ያግዛል ያለው ምክር ቤቱ፤ በሕገ መንግሥታዊ ስርዓት በምትተዳደር ሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው የጋራ በሚያደርጉ ሀገራዊ እሴቶች ላይ እንዲወያዩ ዕድል እንደሚሰጥም አመልክቷል።
የሀገሪቱ ዜጎችም በልዩነት በሚያነሷቸው ጉዳዮች ላይ የተደራጀ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በሕግ የጸደቀውን የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ በማክበር ላይ አቋም እንዲይዙ ማድረግ እንደሚያስችልም ምክር ቤቱ በመግለጫው አስረድቷል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2012
መርድ ክፍሉ