ደብረ ብርሃን፡– የዜጎችን በተለይም የአገር የወደፊት አለኝታ የሆኑ ወጣቶችን ህይወት በመቅጠፍ የሚታወቀው ኤች.አይ.ቪ./ኤድስ እንደገና በማገርሸት ሥርጭቱ ወደ ወረርሽኝ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።
ሰሞኑን በአገራችን ለ32ኛ፣ በዓለም አቀፍ ደግሞ ለ40ኛ ጊዜ በደብረ ብርሃን ከተማ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የመምህራን ቀን ላይ የቫይረሱን ሥርጭት፣ ያገጠሙ ችግሮች፣ የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች አስመልክቶ በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንደተገለፀው ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በአገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን ህይወት የቀማበት ወቅት እንደነበር አመላክቶ ነገር ግን በተቀናጀና በተጠናከረ ርብርብ ልንቆጣጠረው ችለን እንደነበር አስታውሷል።
ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ቫይረሱ ዳግም በማገርሸት ከሚገባው በላይ መስፋፋቱንና ዜጎችን በተለይም ለጋ ወጣቶችን እያጠቃ እንደሚገኝ ጥናቱ አመላክቷል። የጥናቱ አቅራቢ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ እንየው እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት የቫይረሱ ሥርዓት በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ወደ ወረርሽኝ ደረጃ እየደረሰ ይገኛል።
የቫይረሱ ተጠቂዎች ዕድሜያቸው በአብ ዛኛው ከ15 ዓመት እስከ 24 ዓመት የሚሆናቸው ወጣቶች ናቸው ያሉት ወይዘሮ ዓለም ፀሐይ በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በትምህርት ገበታ ላይ ያሉ ናቸው ብለዋል። በመሆኑም ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎቻቸው ስለቫይረሱ ግንዛቤ ከማስጨበጥ አኳያ በከፍተኛ ደረጃ በጀትና ጊዜ መድበው ሊሠሩ ይገባል።
እንደጥናት አቅራቢዋ ገለፃ የቫይረሱ ሥርጭት ምጣኔ በከተማና በገጠር ልዩነት ያለው ሲሆን የከተማው ከገጠሩ በሰባት እጥፍ ይበልጣል። በተለይ ከዋና መንገድ እስከ አምስት ኪሎ ሜትር የሚገኙ አካባቢዎች ሥርጭቱ በፊት ከነበረበት በአራት እጥፍ መጨመሩን መረጃዎች ያሳያሉ ያሉት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የከተሞች መስፋፋት በመኖሩ ምክንያት ቫይረሱ ከከተማ ወደ ገጠር በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ነው ብለዋል። በመሆኑም በዚህ ዙሪያ ያለማሰለስ በመሥራት ሥርጭቱ የሚገታበት መንገድ ሊፈጠር ይገባል።
በአሁኑ ሰዓት እየተከናወኑ የሚገኙ ቫይረሱን የመግታት ሥራዎች ከበፊቱ ጋር ሲነፃፀሩ ሙሉ ለሙሉ የሉም ማለት ይቻላል ያሉት ወይዘሮ ኣለምፀሐይ “በፊት መንግሥት በየቦታው ጽህፈት ቤት ከፍቶ ባለሙያና በጀት መድቦ ሲሰራ ነበር። አሁን ግን ይህ የለም። ጽህፈት ቤቱም ተዘግቷል። ቀደም ሲል በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት ይሠሩ ነበሩ። አሁን ግን አንድም የለም።
በጀትንም በተመለከተ ከመንግሥት በተጨማሪ በርካታ ድጋፍና ዕርዳታ ከውጭ ይገኝ ነበር። አሁን እሱም ቆሟል። ስለዚህ ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑና ዳግም የዜጎችን በተለይም የወጣቶችን ህይወት ከመቅጠፉ በፊት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡትና የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል” ብለዋል።
በቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የተጋለጡ አካባቢዎች በጥናቱ የተለዩ መሆናቸውን የሚናገሩት ጥናት አቅራቢዋ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በተጠያቂነትና ሃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ሊሰሩ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም ሊጠናከሩ እና ተጠቂዎችንም መንከባከብ እንደሚገባ፣ ሰነዶችም ለተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በተለያዩ ቋንቋዎች እየተተረጎሙ መሰራጨት ያለባቸው መሆኑን እንዲሁም መከላከልን መሰረት ያደረጉ ሥራዎች ሊሠሩ እደሚገባ በጥናታቸው አመላክተዋል።
ጥናቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአርባኛ ጊዜ በደብረ ብርሃን ከተማ በተከበረው የዓለም የመምህራን ቀን ላይ የቀረበ ሲሆን የተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎች፣ ምሁራንና የሚመለከታቸው ተመራማሪዎች እንዲሁም የትምህርት ባለደርሻ አካላት ተገኝተዋል። ጥናቱን መነሻ በማድረግም ከፍተኛ ውይይት የተደረገ ሲሆን ግብዓትም የተገኘበት ነው ተብሏል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2012
ግርማ መንግስቴ