ደብረ ብርሃን፡- የመማር ማስተማሩ ተግባር ላይ የመምህርነትን ሙያ ለማሳደግ ወጣቶችን ወደሙያው ማስገባት ተገቢ መሆኑ ተገለፀ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአርባኛ፣ በአገራችን ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ «ወጣት መምህራን -የሙያው የወደፊቱ ባለቤቶች» Young Teachers: The Future Of The Profession» በሚል መሪ ሐሳብ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተከበረው የዓለም የመምህራን ቀን ላይ እንደተገለፀው የመምህርነት ሙያና የመማር ማስተማር ተግባር ስኬታማ ሆኖ ቀጣይነት እንዲኖረው ከተፈለገ ወጣቱ ሙያውን እንዲወደው፣ እንዲመርጠውና በዘርፉ ተሰማርቶ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ማድረግ ይገባል።
በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር (ኢመማ) እና በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጋራ ትብብር በተዘጋጀው በዚህ ኮንፈረንስ ላይ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ እንዳሉት የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የመምህራን ቀን የሚያስተላልፈው መልዕክት የመምህርነት ሙያ ቀጣይነት እንዲኖረው ወጣት መምህራንን ወደሙያው ማካተት አስፈላጊ ሲሆን በሌላ በኩል ይህ ተግባር ለወጣቱ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጋርም የተያያዘ ነው።
ዶክተር ዮሐንስ እንደሚሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያሳየው በርካታ ቁጥር ያላቸው መምህራን ከሙያው እየተሰናበቱ በምትካቸው ወጣት መምህራን ቦታውን እየተረከቡ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ በትምህርት ሥራ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም።
የዘንድሮው መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ማህበር (አይኤልኦ)፣ ዩኒሴፍና የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP) በጋራ ሆነው የመምህርነት ሙያንና የወጣቱን ሁኔታ ገምግመውና አጥንተው ያፀደቁት እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ዮሐንስ ችግሩ ዓለም አቀፍ መሆኑም ይናገራሉ።
እንደ ዶክተር ዮሐንስ ገለፃ አንጋፋ መምህራን በጡረታም ሆነ በተለያዩ መንገዶች ቦታውን ሲለቁ እነሱን ተክተው ሙያው ውስጥ የሚገቡ መምህራን የትምህርት ጥራትን የሚያስጠብቁና የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት የሚያሟሉ ሊሆኑ ይገባል።
ወጣቱን ወደሙያው ማምጣት፣ ተተኪ ማፍራትና ሥራውን በፍቅር እንዲያከናውኑ ማድረግ ግድ ነው የሚሉት ዶክተር ዮሐንስ ይህንን ለማድረግ በቂና ተመጣጣኝ የክፍያ ሥርዓት መዘርጋትና መተግበር፣ የተለያዩ ማበረታቻዎችንም ማቅረብ ከመንግሥት ይጠበቃል ብለዋል።
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚ ዳንት ዶክተር ደረጀ አንዳርጌም ይህንኑ የዶክተር ዮሐንስን ሐሳብ ይጋራሉ። እንደ ዶክተር ደረጀ ገለፃ መጪው ጊዜ የወጣቱ በመሆኑ ወጣቱም ይህንኑ ተገንዝቦ በእውቀት ራሱን መገንባትና በክሂሎት ማዘጋጀት እንደሚጠበቅበት ጠቅሰዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2012
ግርማ መንግስቴ