የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማት ለኢትዮጵያውያን ተስፋ ለአገር መሪዎች እና ለሲቪክ ማህበራት ቃል ኪዳን መሆኑን በሳውዝ ኢስት ኖርዌይ የማህበራዊ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር ግሩም ዘለቀ ገለፁ፡፡
ዶክተር አብይ የኖቤል ተሸላሚ እንዲሆኑ ጥቆማ ያደረጉት ዶክተር ግሩም እንደሚናገሩት ዶክተር አብይን መከታተል የጀመሩት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው በሚሰሩበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳሉ። ከተሾሙም በኋላ እያንዳንዱን ንግግራቸውን እና ተግባራቸውን ሲከታተሉ እንደነበርም ይናገራሉ።
እንደ ዶክተር ግሩም ገለፃ ዶክተር አብይ ለሰው ልጆች ያላቸው አክብሮት፣ ሰላማዊ መሆናቸው፣ እጅግ በጣም በሚማርከው ስብዕናቸው የሚያስገርሙ መሪ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህ ስብዕናቸው ስለማረካቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኖቤል እጩ እንዲሆኑ መጠቆም እንዳለባቸው መወሰናቸውን ይናገራሉ። ዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ አንድ ሰው በሚሰራው ሥራ መመስገን አለበት እንደሚሉት እኔም ሁሌም ሰው ሲያጠፋ ብቻ ከመውቀስ ይልቅ ሲሰራም ማበረታታት ያስፈልጋል በማለት ለዕጩነት ለማቅረብ ሠርቻለሁ ብለዋል።
ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እጅግ የሚያስመሰግን ሥራ ሠርተዋል የሚሉት ዶክተር ግሩም ከሰሯቸው አያሌ ሥራዎች መካከል በተለይ ግጭትን በመፍታት ዙሪያ ማለትም ሰዎች በእኩል አይን መታየት እንዳለባቸው፣ ለይቅርታ መሥራታቸውና፣ ኅብረተሰቡን ለማረጋጋት የሚያደርጓቸው ንግግሮች በመሪ ደረጃ በታሪክም ከነበሩ መሪዎች እንደሚለዩ ገልፀዋል። ዶክተር አብይ ባላቸው የፍልስፍናም ሆነ የተግባር ዕውቀት ሽልማቱ ይገባቸዋል ብዬ አስባለሁ ያሉት ዶክተር ግሩም በዚህም ምክንያት ነው ለዕጩነት ለማቅረብ ስሰራ የነበረው ብለዋል። ለዕጩነት የማቅረብ ሥራ አንድ ዓመት እንደፈጀባቸው በመጠቆም።
እንደ ዶክተር ግሩም ገለፃ ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ያደረጉትን ንግግሮች ወደ እንግሊዘኛ በመተርጎም የግል ሐሳቦቼን በማከል ለዕጩነት ለማቅረብ 61 ገጽ ደጋፊ ጽሑፎችን አዘጋጅቻለሁ። ለጥቆማ የተጠቀምኩት ከደብዳቤ ባሻገር አብዛኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ፊት ያደረጓቸውን ንግግሮች ነው ያሉት ዶክተር ግሩም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ደግሞ ከአልፍሬድ ኖቤል የመመዘኛ ነጥቦች ወይም ማመሳከሪያዎች ጋር የሚገናኙ በመሆናቸው ነው ለድጋፍ እንደተጠቀሙበት የተናገሩት።
እንደ ዶክተር አብይ አይነት መሪ ማግኘት እጅግ ይከብዳል በዓለምም ያሉት በጣም ጥቂቶች መሆናቸውን ጠቅሰው ታዲያ እንዲህ ያለ መሪ በዓለም ትልቅ የሆነ ሽልማት ሲሸለም በጣም ነው የሚያስደስተው። እኔ እራሴ መጀመሪያ ዜናውን ስሰማ አላመንኩም ነበር። እንደገና ወደኋላ በመመለስ ካዳመጥኩኝና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ካየሁ በኋላ ነው እውነት መሆኑን ያወቅኩት ብለዋል።
ይህ ሽልማት የኩራት ምንጭ የሆነ እና አንገትን ቀና የሚያስደርግ ነው። በህይወቴ ትልቅ ሽልማት ከምላቸው አንዱ እና ዋናው ነው። ሽልማቱ ታሪካችንን የምናድስበት እንደ አገር እንደገና ጠንካራ ሆነን የምንመጣበት እንዲሁም አንድነታችንን የሚያጠናክርልንና ወደ ቀድሞ የመቻቻል እና ሰላም የሚመልሰን ይሆናል ብዬ አስባለሁ ብለዋል። ለማንኛው ነገር ትዕግስት ቁልፍ ጉዳይ ነው የሚሉት ዶክተር ግሩም በጣም ጥሩ መሪ አለን፤ መሪያችን የሚታመኑ ናቸው ስለዚህ በመታገስና የተከሰቱ ችግሮች መፍትሄ እንዳለቸው በማመን በመጨረሻም ወደምንፈልገው ደረጃ እንደምንደርስ ልናስብ ይገባል።
ኖቤሉ ለኢትዮጵያውያን ተስፋ ነው ለአገር መሪዎች፣ ለሲቪክ ማህበራት እና ለሚዲያ ቃልኪዳን ነው፤ ስለዚህም ከዚህ በኋላ የአገራችንን አንድነት እና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር እንደ አንድ ህዝብ ሆነን መንቀሳቀስ ይገባናል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2012