- ቀደም ሲል ሌሎችን ብሄሮች ወደ አመራርነት ያለማምጣት ጉዳይ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው፡፡ እኔ ከመከላከያ ሠራዊት የወጣሁት በብሄሬ ምክንያት ነው፡፡
- የኤርትራ መንግሥት ሰላም የፈጠረው ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከጂቡቲና ከሶማሊያ ጋር ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ይከፍታል ተብሎ አይታሰብም፡፡
- መቀሌ ቁጭ ብለህ አቃቂር ከማውጣት እዚሁ ሃሳብ ሰጥተህ ችግሮች መፈታት ቢችሉ ጥሩ ነው፡፡
- ከለውጡ በፊት የነበረው መንግሥት ስልጣንና የማድረግ አቅም አለው፣በአንጻሩ ከለውጡ በኋላ የመጣው መንግሥት ደግሞ የህዝብ ተቀባይነትና የማድረግ አቅም አለው፡፡
- መንግሥት ተዳክሟል የሚሉ ግለሰቦች እኮ አሜሪካን ሄደው በነፃነት ሻይ መጠጣት አይችሉም ነበር፣ዛሬ የመንግሥት ባለስልጣናት ውጭ አገር ቢሄዱ የሚጮህባቸው ሰው የለም፡፡
- እርግጥ ነው ተስፋዬ ጥሩ ፀሐፊ ነው፡፡ እኔም አደንቀዋለሁ፡፡ ነገር ግን ስለእኔ የጻፋቸው መቶ በመቶ ውሸት ናቸው፡፡ በእኔ ሥራ ብቃት ደካማነት ዙሪያ የጻፋቸው ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ተስፋዬ እኔን አያውቀኝም… አሥመራ ላይ ሆኖ የነገረው ሰው ዛሬ አዲስ አበባ ከእኛ ጋር አለ፡፡
- ከአዜብ ጋር ጫት ይሸጣል የተባለው ነገር ፈጸሞ ውሸት ነው፡፡ እኔ ጫት አልነገድኩም፡፡ እሷም የነገደች አይመስለኝም፡፡
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ
ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ በሰራዊቱ ውስጥ ለ35 ዓመታት ሠርተዋል። በሰራዊቱ በተለያዩ የአመራርነት ቦታዎችም አገራቸውን አገልግለዋል። የምስራቅ እዝ አዛዥ ነበሩ። የውጊያ ምህድስና ዋና መመሪያ ኃላፊም ሆነዋል- ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፡፡ በኢትዮ-ኢርትራ ጦርነትም በቡሬ ግንባርና በሶማሊያ አልሸባብን ለመደምሰስ በተደ ረገው ውጊያ በአመራርነት ተሳትፈዋል። ከሁለት ዓመት በፊትም ከሰራዊቱ ተገልለዋል። አሁን በግል ሥራ ተሰማርተዋል፡፡ በመከላከያ አዲስ አደረጃ ጀት፣ መከላከያ ውስጥ ስለነበረው ብሄር ተኮር ችግር፣ ተስፋዬ ገብረአብ ስለርሳቸው በጻፋቸው ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ መጠይቅ አድርገንላቸዋል፡፡ እነሆ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመከላከያ ሚኒስቴር ሪፎርም ዙሪያ ምን አስተያየት አለዎት?
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- በመከላከያ ውስጥ የሚደረግ ሪፎርም ከአሁን ቀደም ተደርጎ የማይታወቅ፣ በአገሪቱ ካለው ለውጥ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ነው፡፡ እናም በእኔ ሃሳብ ሪፎርሙ የሚያተኩርባቸው በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡ አንዱ የሰራዊቱን አስተሳሰብ መለወጥ ነው፡፡ ይህ ማለት ሰራዊቱ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ፣ እሱም በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባና አገራዊ ሰራዊት እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ይህ በአንድ ጀንበር የሚቀየር ባይሆንም ሂደቱ ተጀምሯል፡፡
ሁለተኛው የሪፎርሙ አካል የሆነው በመከላከያ ውስጥ የደንቦችንና የህጎችን ተፈጻሚነት ማረጋጋጥ ነው፡፡ ቀደም ሲል ህግ ቢኖርም ህግ የሚጣስበት ሁኔታ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ህጎችና ደንቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡ ከእነዚህ ህጎችና ደንቦች መካከል መቀየር ያለባቸው ደግሞ በሪፎርሙ ተቀይረዋል፡፡ ለምሳሌ እስካሁን ድረስ በሰራዊቱ የእጩ መኮንነት ምልመላ የሚደረገው ከሰራዊቱ የበታች መኮንኖች ብቻ ነው፡፡
ይህ ይጠቅመናል ብለን ሰርተንበታል፡፡ ሆኖም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ አንደኛ ሰራዊቱ የተማረ የሰው ሃይል ሊያገኝ አልቻለም፡ ጠንካራ ሰራዊት መምራት የሚችል አመራር የሚገኘው ከእጩ መኮንን ነው፡፡ እናም በመከላከያ ውስጥ የተማረ የሰው ሃይል ያስፈልጋል፡፡
ቀደም ሲል የተማረ የሰው ሃይል ለማግኘት ይሰራ የነበረው ሰራዊቱን በርቀት ትምህርት ማስተማር ነው፡፡ የርቀት ትምህርቱንም የሚማረው ካምፕ ውስጥ የሚኖረው እንጂ ግዳጅ ላይ ያለው አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት ሚዛናዊ አካሄድ አይደለም፡፡
ሌላው የመከላከያ ሰራዊት የተማረውን ሃይል የመጠቀም እንጂ የማስተማር ተልዕኮ የለውም፡ ስለዚህ አገሪቱ የምትፈጥረውን የተማረ የሰው ሃይል መጠቀም አለበት፡፡ ይህን ለመጠቀም ህጉ መቀየር ስላለበት ህጉን ቀይረውታል፡፡ በዚህ መሰረትም እጩ መኮንን ከሲቪልና በተመሳሳይ መንገድ ከሰራዊቱም ውስጥ መስፈርቱን የሚያሟላ ተወዳድሮ የመግቢያ ፈተና የሚያልፍ ይገባል፡፡
ይህ በአጼ ኃይለ ሥላሴም ሲሰራበት የነበረ ነው፡፡ በዚያ ዘመን ሁለት የእጩ መኮንኖች አካዳሚዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው ሆለታ ገነት ሲሆን ሁለተኛው ሀረር አካዳሚ ነው፡፡ የሀረር አካዳሚው ከ10ኛ ክፍል ወስዶ 11 ኛንና 12ኛ ክፍልን አስጨርሶ ከዚህ በኋላ ሶስት ዓመት አሰልጥኖ ዲፕሎማ ሰጥቶ በምክትል መኮንነት ያስመርቃል፡ከዚህ የወጡት እስከ ጄነራልነት ይደርሳሉ፡፡ የሆ ለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ደግሞ፤ ከሰራዊት ውስጥ ከምክትል አስር አለቃ እስከ ሻለቃ ባሻ ድረስ ካሉት ተወዳድረው የምክትል መቶ አለቃነት ትምህርት ይከታተላሉ፡፡ በንጉሡ ጊዜ ይሰራበት የነበረው አሰራር ይኸ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ ሀረር አካዳሚ ብቻ ነው የነበረው፡፡ እኛ ስንገባ ደግሞ የተማረውን የሰው ሃይል ትተን ከሰራዊቱ ውስጥ ብቻ እንዲሆን ነው ያደርግነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለምን እንዲህ እንዲሆን ተፈለገ?
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- ይህ የሆነበት ምክንያት በዚያን ጊዜ በነበረን አስተሳሰብ ከሰራዊቱ ውስጥ የምናመጣው ሰው የውጊያ ልምድ አለው ከሚል እምነት ነው፡፡ ሌላ ከረጅም ጊዜ አኳያ ያላየነው ነገር የመከላከያን የተማረ የሰው ሃይል ማግኝት አልተቻለም፡፡ ሁለተኛ ከኦፊሰር አኳያ ብቃት ያለውና ብሄራዊ ተዋጽኦንም ያመጣጠኑ መኮንኖችን ማፍራት አልቻልንም፡፡ ለዚህ ነው ከትምህርት ቤት መመልመል አለበት የሚል ነገር የመጣው፡፡ ስለዚህ ሪፎርሙ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው የሚባለው፤ በሌሎች ጉዳዮችም ላይ እንዲሁ ለውጥ ይኖራል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመከላከያ ሰራዊት አመራር ምደባ የብሄር ተዋጽኦን ያመጣጠነ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ሪፎርሙ ይህን ይቀይራል የሚል እምነት አለዎት?
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- ሪፎርሙ ይህን ይቀይራል፡፡ አሁን እኮ በሰራዊቱ ውስጥ ብሄራዊ ተዋጽኦን ለማመጣጠን አዲስ የሰው ሃይል አልመጣም፡፡ ቀደም ሲል ስራ ብንሰጣቸው ያበላ ሻሉ በሚል ያልታመኑት ናቸው አሁን ሃላፊነት የተሰጣቸው፡፡ ስለዚህ አሁን ተመጣጥ ኗል፡፡ ለምሳሌ፤ አንድ ኮማንድ ውስጥ አራት ሰው ነው ያለው፤ አንደኛው አዛዥ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክትል አዛዥ ነው፡፡ ሶስተኛው የሰው ሀይል አስተዳደር ነው፡፡ አራተኛ ሎጂስቲክ ነው፡፡ በእነዚህ ውስጥ የተደጋገመ ብሄር አይታይም፡፡
ይህንን ቀደም ሲልም መስራት ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን አመራሮቹ ትክክልኛ ካልሆነ አመለካከት በመነጨ አዛብተውት ቆይተዋል፡፡ ምክንያቱም አሁን የመጡት አመራሮች ዛሬ የተፈጠሩ ሳይሆኑ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከ30 እስከ 40 ዓመታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ ሰራዊቱን በሚገባ የሚያውቁ፣ ህይወታቸውን ሁሉ በውትድርና ያሳለፉ፣ ቅንነት ያላቸውና ለውጥ ፈላጊ የነበሩ በመሆናቸው አሁን የብሄር ተዋጽኦን ሊያመጣጥኑት ችለዋል፡፡ ሰው የሚያይ ዐይን ተፈጠረ፡፡ ይህ ነው እንዲመጣጠን ያደረገው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ማመጣጠን ያልተቻለው ሆን ተብሎ ነው? ወይንስ ቦታውን የሚመጥን አመራር ባለመኖሩ ነው?
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- በአንድ በኩል ልምድ ያለው ሰው በውትድርና ላይ ቢመራ ይሻ ላል፤ ችግር ሲያጋጥም ይፈታልናል ከሚል በጎ አስተሳ ሰብ የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ወደ አመራርነት ብናመጣ ነው የሚሻለው ከሚል ነው፡፡ ይህ የተደረገው ሆን ተብሎ ሌሎችን ላለማምጣት ከመነጨ አስተሳሰብና ካለ ፍላጎት የተነሳ ነው፡፡ መነሻውም ሥርዓቱን ያመጣሁት እኔ ነኝ፡፡ እኔ እንደፈለኩት ማድረግ አለብኝ ከሚል አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው፡፡
ምክንያቱም፤ የመከላከያ አመራር በኢትዮ-ኢርትራ ጦርነት ተፈትኗል፡፡ አሁን የአመራር ቦታውን የያዙትም በዚህ ውስጥ ያለፉ ናቸው፡፡ ዕዞችንና ክፍለ ጦሮችን የሚመሩት በሰራዊት ውስጥ ያላቸው ዕድሜ ትንሹ 30 ዓመት ነው፡፡ ልምድ የላቸውም ሊሰሩ አይችሉም የሚባሉ አይደሉም፡ እናም ሌሎችን ብሄሮች ወደ አመራርነት ያለማምጣት ጉዳይ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው፡፡ የተለያዩ መነሻዎች ቢኖሩትም ዋናው መነሻ ግን ሆን ተብሎ ሌሎችን ወደ አመራርነት ለማምጣት ስላልተፈለገ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የነበሩ አመራሮች በብሄራቸው ምክንያት እምነት አይጣልባቸውም ይባላል፡፡ ምን ያህል እውነትነት አለው?
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- ባለፉት 27 ዓመታት በማንነትህ አሸባሪ፣ ጠባብና ትምክህተኛ ትባላለህ፡፡ ጠባብና ትምክህት ለብሄር ነው የተሰጡት፤ ጠባብ ለኦሮሞ፤ ትምክህት ለአማራ ነው የተሰጠው፡፡ አሸባሪ ከተባለ ደግሞ ግንቦት ሰባት ለአማራ፤ ኦነግ ለኦሮሞ፤ ኦኤልኤፍ ለሶማሌ ነው፡፡ እነዚህ ሶስቱ ናቸው እስር ቤት የነበሩት፤ አሸባሪም ተብለው የሚቀጡትም እነዚህ ብሄሮች ናቸው፡፡ ሆኖም በየማረሚያ ቤቱ እግር የሚቆርጠው፣ የሚያኮላሸው፣ ግብረሶዶም የሚፈጸመው ይኸው አሸባሪ ነህ ሲል ሲፈርጅ የነበረው አካል ነው፡፡
እናም ያለመታመንም ከዚህ ነው የሚመነ ጨው፡፡ ይህም በሽታ በሰራዊቱም ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ሌላው ብሄር ወደ ከፍተኛ አመራርነት እንዳይመጣ የተደረገው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ሆኖም ይች አገር የሁሉም ናት፡፡ ስለዚህ ብቃትና ጤንነት ኖሮህ፤ እንዲሁም ለህገ መንግስቱ ታማኝ ሆነህ ሳለ በማንነትህ ብቻ ከሰራዊቱ ትገለላለህ፤ ወይ ትታሰራለህ፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ይህ ነበር ሲሆን የቆየው፤ ከሰራዊቱ ውስጥ በተለያየ መንገድ ወደ እስር ቤት የተወረወሩም ይሁን ከሰራዊቱ የወጡ በማንነታቸው ምክንያ ነው፡፡ ስለዚህ በአገ ሪቱ የነበረው የማንነት ጉዳይም በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ችግር ፈጥሯል፡፡ በማንነት ምክንያት ሰዎች የሚቀጡበት ዘመን ነው የነበረው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ከመከላከያ ሰራዊት አመራርነትዎ የተገለሉት በብሄርዎ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል?
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- አዎ በማንነቴ ምክንያት ነው የምለው፤ እዚህ ድምዳሜ ላይ እንድደርስ ያደረገኝ እኔ ከሰራዊቱ የወጣሁበትን ምክንያት አላውቀውም፡፡ በመተካካት ነው እንዳትል ደግሞ መተካካቱ መመዘኛ ወጥቶ ለታ፡፡ ዕድሜ፣ የስራ አፈጻጸምና ጤንነት ታይቶ ነው አንድ የመከላከያ አመራር በመተካካት ከሰራዊቱ መሰናበት ያለበት፤ እኔ የተነገረኝ ነገር የለም፡፡ ዝም ብዬ ነው የወጣሁት፤ በአፈጻጸም ነው እንዳልል ደግሞ፤ እኔ በወጣሁ ጊዜ የእኔ ክፍል የልማት አርበኛ ተብሎ ተሸልሟል፡፡ ስለዚህ በዕድሜ፣ በጤንነትና በአፈጻጸም ተመዝኜ ከሰራዊቱ ካልተገለልኩ በማንነቴ ብቻ ነው ያስወጡኝ ማለት ነው፡፡
ማንኛውም ቢሆን ጠመንጃ ለመተኮስ ወይም እስክብሪቶ ለመያዝ የተፈጠረ ብሄር የለም፡፡ምክንያቱም አመራር በልምድና በትምህርት የሚገኝ ስለሆነ ነው፡፡ የአሰራሩ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ከመከላከያ መውጣቴ የሚያስቆጨኝ ነገር የለም፡፡ እኔ መከላከያ ውስጥ የማገለግለው ለአገሬ ነው እንጂ፤ ለኑሮ ከሆነ አሁን ያለሁበት ስራ አንድ ሺ ጊዜ እጥፍ ይበልጣል፡፡ እናም ቀደም ሲል የነበረው የአሰራር ሥርዓት ለመከላከያም ሆነ ለአገር ጥሩ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በማንነት ላይ ነው ያተኮረው፤ ከተጠቂዎች መካከል እኔም አንዱ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም አስፍነዋል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ወገኖች አሁንም የጸጥታ ስጋት ሊፈጠር ይችላል የሚሉ አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- የጸጥታ ስጋት አለ ወይም የለም ለማለት የወቅቱን ሁኔታ መገምገም ያስፈልጋል፡፡ ግን አጠቃላይ ካለው ሁኔታ አንጻር አሁን በኤርትራ በኩል ስጋት አለብን የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኤርትራ ለኢትዮጵያ ስጋትነቷ አቁሟል፡፡ ማንም ያልጠበቀው፤ ይሆናልም ብሎ ያላሰበው፣ የተደራጀ ሰራዊት አልፈህ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ አስመራ መገኘት ጀግንነትነው፡ሲመለስ በህዝቡ ቢገደልም እስራኤልና ግብጽ ተፋጥጠው እያሉ ወደ እስራኤል የሄደው የግብጹ ፕሬዚዳንት የነበረው ገማል አብዱል ናስር ነው ፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ ሰላም ከተፈጠረ ወዲህ ድንበር ተከፍቷል፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱም ተጧጡፏል፡፡ ከዚህ ወደ አስመራ ከአስመራ ወደዚህ ሰዎች ይመጣሉ፤ ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ ኤርትራ የመጀመሪያ ስጋት አይደለችም፡፡ ወደፊት የጅቡቲ አይነት ስትራቴጂክ ግንኙነት ለመፍጠር መሰረት እየተጣለ ነው፡፡ እናም ኤርትራ ስጋት ልትሆን ቀርቶ ሁለታችንም ገና የእርቁን ‹‹ሀኒ ሙን›› አልጨረስንም፡፡
በእኔ እምነት አሁን የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን በጦርነት አይፈልጋትም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ፤ ኤርትራ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች፡፡ ሁለተኛ፤ ኤርትራና ኢትዮጵያ የሸቀጥ ልውውጥ ጀምረዋል፡፡ በዚህ ሁለቱም ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ሌላው የኤርትራ መንግስት ሰላም የፈጠረው ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከጂቡቲና ከሶማሊያ ጋር ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ይከፍታል ተብሎ አይታሰብም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ውስጥ እዚህም እዚያም በሚነሱ ብሄር ተኮር ግጭቶች ጀርባ ስውር እጆች ይኖሩበታል ይላሉ? እነማን ናቸው?
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- እዚህም እዚያም ለሚነሱ ግጭቶች ከጀርባ ስውር እጆች አሉ በት፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ግጭቶች በፊትም ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚህ ስውር እጆች መነሻ የሚያደርጉት ነገር አለ፡፡ በህገመንግስቱ የብሄር ብሄረሰቦችንና የህዝቦችን መብት ማስጠበቅ ጉዳይ እንደምሰሶ ነው የተቀመጠው፡፡ የብሄር፤ ብሄረሰቦችና የህዝቦች መብት የሚጠበቀው ደግሞ የዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በርካታ የልማት ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም የዴሞክራሲው ምህዳር አልሰፋም፡፡ በዚህ ምክንያትም ብሄር የሚባለው ጉዳይ እየጦዘ ሄዶ የራሱን ደሴት ሰርቷል፡፡ ስውር እጆች ይህን አስተሳሰብ ነው የሚጠቀሙት፤
ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ብሄር ሌላውን ሲጨቁን ወይም ሲገዛ አልታ የም፡፡ እርግጥ ነው ከዚያ ብሄር የወጡ ጨቋኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም፤ ይህን እንደሽፋን በመ ጠቀም፤ አንተን የፈጁህ እኮ እነእገሌ ናቸው፡፡
የእገሌ ብሄር ነው የጨቆነህ፤ እያሉ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡ አሁንም ብሄርን እንደሽፋን ተጠቅመው ነው ግጭት የሚለኩሱት፤
አዲስ ዘመን፡- ችግር ካለ በውይይት መፍታት ሲቻል ለምን ግጭት መፍጠር አስፈለገ?
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣው ለውጥና አሁን ያለው መንግስትም እንዲቀጥል አይፈልጉም፡፡ ግጭት በመፍጠር ይህ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ሰላምን አላመጣም፣ ዜጎች በፈለጉበት ቦታ ተቀሳቅሰው መስራት አልቻሉም፡፡ በአጠቃላይ የህግ የበላይነትን አረጋግጦ ሰላምን ሊያሰፍን ባለመቻሉ፣ አገሪቱን መምራት ያቃተው ደካማ መንግስት ነውና ይህን መንግስት መቀየር አለብህ ብሎ የኢትዮጵያን ህዝብ በመቀስቀስ በመንግስት ላይ ህዝብን ማነሳሳት ነው ዓላማቸው፡፡ ለውጥ ማለት በአገር ላይ በነጻነት መኖር ነው፡፡ ይህ ለውጥ ለሰው ልጅ ክብር ነው የሰጠው፤ ከአገር ውስጥ እስረኞችን መፍታት ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም የታሰሩ ዜጎችን ጭምር አስፈትቷል፡፡ ይህን ሥርዓት ነው እንዲቀጥል የማይፈልጉት፡፡
ቀደም ሲል በእስር ቤት ውስጥ ለመናገር የሚቀፉ ነገሮች ተደርገዋል፡፡ በማንኛውም አገር የምርመራ ቴክኒክ ያልሆነ ግብረሶዶም ሲፈጸሙ ነበር፡፡ የጽኑ ሃይማኖተኞች በሆነች አገር ግብረሰዶምን እንደምርመራ ቴክኒክ መጠ ቀም ያሳፍራል፡፡ ይህን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይቀጥል ያደረገውን ለውጥ ማደናቀፍ የሚፈልጉ ናቸው ስውር እጆች የሚባሉት፡፡ ጠላት ካልፈጠሩ በስተቀር የኖሩ የማይመስላቸው ሰዎች ለውጡ እንዲቀጥል አይፈልጉም፡፡ ስለዚህ መንግስት ደክሟል የሚሉ ሰዎች ስውር እጆች ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ መንግስት ላይ የዘመቱ በጣም ተከፋይ ማህበራዊ ሚዲያዎችም አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ደክሟል፣ አገሪቱ ተዋርዳለች፡፡ ስለዚህ ጠንካራ መንግስት ያስፈ ልጋታል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን ሃሳብ አለዎት?
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- መንግስት ደክሟል የሚሉት ሰዎች እንደምክንያት የሚ ጠቅሱት ጉዳይ የዜጎች መፈናቀልና የህግ የበላ ይነት አልተረጋገጠም የሚል ነው፡፡ ሆኖም፤ መንግስት ተዳክሟል የሚሉ ግለሰቦች የሚመሩት መንግስት በነበረበት ጊዜ ከሶማሌ ክልል በአዋጅ በፕሬዚዳንቱ ተመርቶና እዚያ በነበሩ የመከላከያ ጄነራሎች መኪና አቅራቢነት አንድ ሚሊዮን ኦሮሞ ሲፈናቀል ትንፍሽ አላሉም፡፡ እነዚህ ሰዎች ጠንካራ መንግስት ነን ብለው በሚመሩበት ዘመን ከጉራ ፈርዳ አማራ ሲፈናቀል ትንፍሽ አላሉም፡፡ደግሞ መፈናቀል ዛሬ አይደለም የተጀመረው፡፡ ግን መፈናቀል መቆም አለበት፤ የህግ የበላይነት መከበር አለበት፡፡ ነገር ግን መቀሌ ቁጭ ብለህ አቃቂር ከማውጣት እዚሁ ሃሳብ ሰጥተህ ችግሮች መፈታት ቢችሉ ጥሩ ነው፡፡
መንግስት ተዳክሟል ለማለት መመዘኛዎች አሉት፡፡ እነዚህም ስልጣኑ፣ የማድረግ አቅሙ፣ ተቀባይነቱና አገልግሎት አሰጣጡ ናቸው፡፡ ከዚህ በመነሳት አሁን ያለው መንግስት የህዝብ ተቀባይነት አለው፡፡ የህዝብ ተቀባይነት ደግሞ የስልጣንና የሃይል ምንጭ ነው፡፡ የህዝብ ተቀባይነት የሌለው መንግስት የፈለገውን ያህል የማድረግ አቅም (ጠንካራ ፖሊስና መከላከያ) ቢኖረው እሱን ብቻ ይዘህ ሰላም ማስከበር አትችልም፡፡
ስለዚህ ከለውጡ በፊት የነበረውን መንግስ ትና ከለውጡ በኋላ የመጣውን መንግስት ማነጻጸር ይቻላል፡፡ ከለውጡ በፊት የነበረው መንግስት ስልጣንና የማድረግ አቅም አለው፡፡ህዝብ የሚፈልገውን አገልግሎት ግን መስጠት አልቻለም፡፡ የህዝብ ተቀባይነት አጥቷል፡፡ ስልጣኑም በሰራዊትና በፖሊስ ብቻ ተንጠላጥሎ ቀርቶ ነበር፡፡ በአንጻሩ ከለውጡ በኋላ የመጣው መንግስት ደግሞ የህዝብ ተቀባይነትና የማድረግ አቅምም አለው፡፡ የህዝብ ተቀባይነት ስላለው የማድረግ አቅሙን ከተጠቀመ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈልገው ሁኔታ ላይ መድረስ ይች ላል፡፡ የማ ድረግ አቅሙን የመጠቀም ስልጣንም አለው፡፡ ስለዚህ ሶስቱንም ነው የሚያሟላው፡፡ አገልግሎ ቱን ለህዝቡ ተደራሽ ማድረግ ነው የሚቀረው፡፡ ስለዚህ ሰላምን ማስፈን አለበት፡፡ ይህን ማድረግ የሚያስችል ቁመና ደግሞ አለው፡፡
ከዚህ ተነስቼ አሁን ያለው መንግስት በፊት ከነበረው የተሻለ ጥንካሬ አለው፡፡ ዋናው የጥንካ ሬው መሰረትም በህዝብ ተቀባይነት ማግኘቱ ነው፡፡ ዓለም የተደነቀበት ለውጥ ያመጣ ጭምር ነው፡፡ መንግስት ተዳክሟል የሚሉ ግለሰቦች እኮ አሜሪካን ሄደው በነጻነት ሻይ መጠጣት አይችሉም ነበር፡፡ እያንዳንዳቸው የዘሩትን ነው ያጨዱት፡፡በእድሜያችን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ውጭ አገር ሄዶ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ሰብስቦ ሲያናግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ የመጀመሪያው ነው፡፡ ዛሬ የመንግስት ባለስልጣናት ውጭ አገር ቢሄዱ የሚጮኸባቸው ሰው የለም፡፡ ይህ ነው የህዝብ ተቀባይነት፡፡
ስለዚህ፤ የራስህን ደሴት ስትሰራ ሌሎች ነገሮችን ማየት አትችልም፡፡ የመፈናቀሉ ጉዳይም ቢሆን በፊት የነበረው መንግስት ውጤት ነው፡፡ እንዲያውም የአሁኑ መንግስት ሸክም የሆነው የቀደመው መንግስት የሰራው ደባ ነው፡፡ መንግስት ተዳክሟል የሚሉ ግለሰቦች አይ ሌላ ጠንካራ መንግስት ነው የሚያስፈልገን ካሉ ደግሞ፤ እሱ በምርጫ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ውሳኔ እንጂ እነዚህ ግለሰቦች የሚወስኑት አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተስፋዬ ገብረአብ በእርስዎ ስም ተጠቅመው በጋዜጣ የሚጽፉ የመንግስት ባለስልጣናት እንደነበሩ በመጽሀፉ ጽፏል፡፡ ምን ያህል አውነትነት አለው?
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- የእኔን ስም ተጠ ቅሞ ጋዜጣ ላይ ጽሁፍ መጻፉን አላየሁም፡፡ በእኔ ስም ለመጻፍ ቅርበት ሊኖረን ይገባል፡፡ ሆኖም፤ ጻፉ ከተባሉ ሰዎች ጋር ቅርበት የለኝም፡፡ ተስፋዬ ገብረአብ ስለእኔ ብዙ ነገር ጽፏል፡፡ በሁሉም መጽሐፎቹ ላይ የእኔ ስም ተነስቷል፡፡ ከተስፋዬ ጋር መቼም ቢሆን ለአንድ ደቂቃ እንኳ ዐይን ለዐይን ተያይተን አናውቅም፡፡
እሱ ደቡብ አፍሪካ አግኝቸዋለሁ ነው የሚለው፡፡ ውሸቱን ነው አላገኘኝም፡፡ ደቡብ አፍሪካ አገኘሁት ብሎ የቀባጠራቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እኔ አላነጋገርኩትም፣ አላገኘሁትም፡፡ እሱ ባለበት ጊዜ እውነት ነው ለህክምና ደቡብ አፍሪካ ሄጀ ነበር፡፡ ሆኖም ይችን እውነት ተጠቅሞ በእስክብሪቶ የሚፈጥረው ነገር ደግሞ ሀሰት ነው፡፡ እርግጥ ነው ተስፋዬ ጥሩ ጸሀፊ ነው፡፡ እኔም አደንቀዋለሁ፡፡ ነገር ግን ስለእኔ የጻፋቸው መቶ በመቶ ውሸት ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስ ትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ጋር ጫት ትሸጡም ነበር ብሏል፡፡ ይህስ ምን ያህል እውነት ነው፡፡
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- ከአዜብ ጋር ጫት ይሸጣል የተባለው ነገር ፈጸሞ ውሸት ነው፡፡ ሀረር የሰራሁት ለ13 ዓመታት ነው፡፡ ለአዜብ ጫት ካልሸጣቸሁ ብሎ የሀረርጌን አርሶ አደሮች ፈጃቸው ነው ያለው፤ ስለዚህ ይህን ባደርግ ኖሮ ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረብ አለብኝ፡፡ ሁለተኛ፤ ከተጠቀሰችው ሴት ጋር አይደለም ጫት ልነግድ ከርሷ ጋር ሁለት ቀን ብቻ ነው ተገናኝተን ያወራነው፤ ጫትም አብሬ አልነገድኩም፡፡ ፈጸሞ ውሸት ነው፡፡ ያኔ የመከላከያ ሰራዊት አባል ሆኜ አይደለም አሁን እንኳን ጫት አልነግድም፡፡ ይህን ስልህ ግን የሰራዊት አባል ሆነው የነገዱ የሉም ማለት አይደለም፡፡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን ጫት አልነገድኩም፡፡ እሷም የነገደች አይመስለ ኝም፡፡ ምክንያቱም እዚያ አካባቢ ላይ ረጅም ጊዜ ስለነበርኩ የጫት ነጋዴዎች እነማን እንደሆኑ እናውቃቸዋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሙዚቃ ቅርብ ናቸው ተብለዋል እውነት ነው?
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- እኔ ከ1976 እስከ 1978 ዓ.ም ድረስ ሙዚቀኛ ነበርኩ ጊታር፣ ቤዝ ጊታር፣ ሊድ ጊታር፣ ሳክስፎንና ጃዝ እጫወታ ለሁ፡፡ ድምጻዊ ግን አይደለ ሁም፡፡ ሆኖም ከ1978 ዓ.ም በኋላ ትቻለሁ፡፡ ምክንያቱም ወደተለያዩ ሃላፊነቶች ስለተዛወርኩ ነው፡፡ ታዲያ ተስፋዬ በእኔ ስራ ብቃት ደካማነት ዙሪያ የጻፋቸው ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ተስፋዬ እኔን አያውቀኝም ከየት አመጣው? ማን ነገረው? የሚል ጥያቄ ብታነሳ ድብቅ ዓላማ አለው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ፖለቲካዊ የእኔን ስም ለማጥፋትና ከህዝቡ እንድራራቅ የሚፈልግ ሰው ነው የነገረው፤ ማን እንደነገረው አውቃለሁ፡፡ እሱን ዛሬ አልገልጸ ውም፡፡ ወደፊት ከተስፋዬ ጋር ተገናኝተን ቁጭ ብለን እናወራ ይሆናል፡፡ አስመራ ላይ ሆኖ የነገረው ሰው ዛሬ አዲስ አበባ ከእኛ ጋር አለ፡፡ ሰው የው ማን እንደሆነ አንድ ቀን እነግራችኋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጊዜዎን ሰውተው ለቃለ መጠይቁ ስለተባበሩኝ በጣም አመሸግናለሁ፡፡
ሌተናል ጄነራል ባጫ፡- እኔም በጣም አመሰ ግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011
በጌትነት ምህረቴ