አዲስ አበባ፡- የኢህአዴግ ውህደት አገራዊ አንድነትን ከማስቀጠል አኳያ በጣም አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን የሐረሪ እና የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንቶች ገለፁ፡፡
የሐረሪ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኦርዲን በድሪ እና የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ከኢህአዴግ ጋር የሚደረገው ውህደት ለአጋር ድርጅቶች በአገራቸው ጉዳይ ላይ የመወሰን ዕድልን የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ አገራዊ አንድነትን ከማስቀጠል አኳያም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችንም መቋቋም የሚቻለውም አገራዊ አንድነትን ማረጋገጥ ሲቻል ነውና አንድ ፓርቲ መመስረቱ ለነገ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡
እንደ አቶ ኦርዲን ገለፃ፤ ዓለም አቀፉ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ግንባር፣ ነፃ አውጭ እና ንቅናቄ የሚባሉት የፓርቲ ስያሜዎች ሥርዓትን ለመቃወም የሚደራጁና በአብዛኛው ተቃውሞን የሚያሳዩ ናቸው። ስለሆነም ኢህአዴግ ራሱ ግንባር ሆኖ መቀጠል አይኖርበትም። የግድ ወደ ፓርቲ መቀየር አለበት። ይህ ሲሆን ደግሞ አጋር ድርጅቶች እስካሁን በአገራዊ ጉዳይ ላይ እንዳይሳተፉ ማነቆ መሆኑ ያበቃና በባለቤትነትና ቁርጠኝነት ለመንቀሳቀስና የጎላ ተሳትፎ ለማድረግ ዕድል ይሰጣል። ውህደቱ አጋር ድርጅቶች ኢህአዴግ የወሰነውን ውሳኔ ብቻ እንዲተገብሩ የመገደዳቸው ጉዳይ እንዲያከትምም ያደርጋል።
አቶ ኦርዲን እንደገለፁት፤ ውህደቱ ሲመጣ አጋር ፓርቲዎች ድምፃቸውን በአግባቡ የሚያሰሙበት ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህም በአገር ጉዳይ ላይ የጋራ የሆነ ውሳኔ ማስተላለፍ ይቻላል። ለተግባራዊነቱም በባለቤትነት ለመንቀሳቀስ ይገፋፋል። በእርግጥ እስካሁን ባለው አጋጣሚ በብሔራዊ ማንነት ላይ፣ በፌዴራል ማንነት ላይ እና በእያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰቦች ላይ የተሠሩ ሥራዎች አሉ፤ እነዚህም መልካም የሚባሉ ናቸው። ይሁንና በጋራ ማንነትና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተሠሩት ሥራዎች የዚያን ያህል ጎልተው አልታዩምና ኢህአዴግ እንደ አንድ ፓርቲ ሁሉንም አቅፎ ሲንቀሳቀስ በጋራ እሴቶችና ማንነቶች ላይ ለመሥራት የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጠራል የሚል እምነት አላቸው። በሕገ መንግሥቱ ላይም እንደተቀመጠው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር የሚያስችል አጋጣሚ እንዲኖርም ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ ለመተጋገል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው፤ ኢህአዴግ የአገሪቱን ሥልጣን እንደተቆጣጠረ ከእህት ድርጅቶቹ በስተቀር አጋር የሚባሉ ድርጅቶች በአገሪቱ ጉዳይ ምንም አይነት የመወሰን እድል እንዳልነበራቸው ጠቅሰው፤ ‹‹በአንድ አገር ውስጥ የምንሠራ ሆነን በሚወሰኑ ጉዳዮች ላይ የተወሰኑ አካላት ብቻ እንዲወስኑ መደረጉ በዜጎች መካከል ልዩነት እንዲፈጠር አድርጓል።›› ሲሉ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ አጋር ድርጅቶች ያልወሰኑትን ጉዳይ አስፈፅሙ መባላቸው ሞግዚት እንዲሆኑ ያስገደደ መሆኑና ሞግዚት ላለመሆን ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎችና መድረኮች የመዋሀድን ጥያቄ ከማቅረብ አለመቦዘናቸውን አመልክተዋል። በወቅቱ ሲመለሱላቸው የነበሩ ምላሾችም አጥጋቢ እንዳልነበሩ አስታውሰዋል።
የውህደቱ መዘግየት እንደ አጋር ድርጅት የጎዳቸው ነገርን አስመልክተው ፕሬዚዳንቶቹ ሲያብራሩ፤ የአገሪቱ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሲቀረፁም ሆነ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ ዕድል እንዳያገኙ ሲያደርግ ቆይቷል። ከዚያም የተነሳ የባይተዋርነት ስሜት እንዲፀባረቅ ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም የተወሰነን ነገር ተግባራዊ እንዲያደርጉ ከመገደድ ውጭ በሚቀመጡ አጀንዳዎች ላይ የበኩላቸውን ሐሳብ አመንጭተው እንዳይከራከሩ ዕድሉን አሳጥቷቸዋል። በመሆኑም ውህደቱ በአገር ጉዳይ ላይ እንዳይወስኑ መደረጋቸውን ያስቀረዋል።፡
“ውህደቱ በፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ላይ ምንም የሚያሳድረው ጫና የለም። ፓርቲ ራሱን የቻለ ሲሆን፣ መንግሥት ደግሞ መንግሥት ነው። ስለዚህ ፓርቲዎች ስለተዋሃዱ ፌዴራሊዝም ይፈርሳል የሚያስብል ነገር አይኖርም። ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር ተያይዞም ምንም የሚያመጣው ችግር አይኖርምና በዚህ ረገድ ሥጋት ያላቸው አካላት አስተሳሰባቸው ስህተት ነው” ሲሉ የሁለቱ ክልል ፕሬዚዳንቶች ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2012
አስቴር ኤልያስ