ሙዚቃ ማለት የዓለም ቋንቋ ነው። ሰዎች አብዛኛውን ስሜታቸውን ማለትም ኀዘናቸውን፣ ደስታቸውን፣ ትዝብታቸውን፣ ቁጭትና ምሬታቸውን፣ ፍቅራቸውን ወዘተ… በዜማ የሚገልፁበት ቋንቋ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሙዚቃ የሰው ልጅ ምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ያለ እና አብሮ የሚቀጥል ጥበብ ነው። ሙዚቃ ለተዝናኖት ከመዋሉ በተጨማሪም ባህልን ለማስተዋወቅ፣ ለሀገራዊ አንድነት፣ ፍቅርና ስሜት፣ ለመግለፅ እንዲሁም የተለያዩ በጎ መልካም ሀሳቦችን ለማንፀባረቅ ይረዳል።
አንድ ሙዚቃ ለሕዝብ ከመድረሱ እና ከመሰማቱ በፊት ብዙ ውጣ ውረዶች ልፋት አሉት፡፡ ታዲያ ይህንን የዓለም ቋንቋን አድማጭ ጆሮ ከመድረሱ በፊት ትልቅ ሥራ ከሚሰሩት መካከል ግጥም ደራሲዎች እና የሙዚቃ አቀናባሪ እንዲሁም የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡ እኛም ለኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ አሻራቸውን ካኖሩ እና ሕይወታቸውን ለዚሁ ዘርፍ መስዋዕት ከአደረጉ የዘርፉ ተዋንያን አንዱ የሆነውን «የሙዚቃ መናኙን» ኤልያስ መልካን ስንብት ምክንያት በማድረግ በጥቂቱ ልናወሳ ወደድን፡፡
ትውልዱ እና ዕድገቱ በአዲስ አበባ ውስጥ አዲስ ከተማ ተብሎ በሚጠራውና ልዩ ስሙ አብነት በሚባለው ሰፈር ነው ኤልያስ መልካ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ሰባተኛ አማኑኤል አካባቢ በሚገኘው ኃይሉ ተስፋዬ በሚባል የሕዝብ ትምህርት ቤት ተማረ። ከዚያም ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ ከፍተኛ ሰባት ትምህርት ቤት ተምሯል። በልጅነቱ ጥሩ እግር ኳስ ተጫዋች እንደነበር ወዳጆቹ ይናገራሉ።
በኋላም የሙሉ ጊዜ ተማሪ በመሆን ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በ1987 ዓ.ም ገብቶ የተማረ ሲሆን በዋናነት «ቼሎ» በማጥናት ትምህርቱ በጥሩ ውጤት አጠናቀቀ። ኤልያስ ከተሳተፈባቸው የሙዚቃ ቡድኖች (ባንዶች) ፅዮን መንፈሳዊ የሙዚቃ ቡድን፣ መዲና የሙዚቃ ባንድ፣ 3M የሙዚቃ ባንድ ዜማ ላስታስ፣ አፍሮ ሳውንድ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው። ኤልያስ ሙዚቃን ማቀናበር የጀመረው ‘በገና ስቱዲዮ’ን አቋቁሞ ሲሆን በሙያው ታታሪና ጎበዝ እንደነበር አብረውት የሰሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በልጅነቱ አብረው የሰንበት ትምህርት በወንጌላውያን አማኞች ቤተ ክርስቲያን እየተማሩ ማደጋቸውን የሚናገረው ገጣሚ ዳዊት ፀጋዬ፣ ፒያኖ እና ጊታር ቤታቸው እየመጣ ይጫወት እንደነበር ያስታውሳል። ኤልያስ መልካ በአዲስ ከተማ ገነት ወንጌላውያን አማኞች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገለግል እንደነበር የሚናገረው ዳዊት፣ በጣም ተጫዋች፣ የዋህና ቅን እንደነበር ያስታውሳል።
በዋናነት ሊድ ጊታር ከመጫወት ባለፈ የሙዚቃና የዜማ ደራሲ እንዲሁም አቀናባሪ ነበር። በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ እያለ በኦሮምኛ ሙዚቃ ያሉ የተለያዩ የድምፅና የቅኝት አደራደሮች ላይ የሰራው አነስተኛ ጥናት በዘርፉ ተጠቃሽ መሆኑን መምህራኖቹ ይናገራሉ። በቅርቡም ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን አውታር የተሰኘ የሙዚቃ መሸጫ መተግበሪያ ሰርቶ ማስተዋወቁ ይታወሳል።
ኤልያስ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ አሻራቸውን ካሳረፉ ወጣት ባለሙያዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎችና ለሙዚቃ ቅርብ የሆኑ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች የመሰከሩለት ከያኒ ነበር። የሙዚቃ አቀናባሪ፣ ገጣሚ፣ የዜማ ደራሲ እና ጊታሪስት የሆነው ኤልያስ መልካ ዕድሜው በአርባዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበረ ድንቅ ከያኒ ነው። ይህ የኪነጥበብ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ የተሰማው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።
የሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ ኤልያስን በቅርበት ያወቁት ከሦስት ዓመት ወዲህ መሆኑን ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ይጠቅሳሉ። ከዚያ በፊት በሥራዎቹ ብቻ ነበር የማውቀው የሚሉት አቶ ዳዊት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ «የሙዚቃ ባለሙያዎች መብት አልተከበረም፣ ሥራቸው አላግባብ እየተነገደበት ነው፣ ጥቅም አላገኙም» በሚል እንቅስቃሴን በመጀመር ሲመራ የነበረ ሰው ነበር።
«ኤልያስ ለራሱ ሳይሆን ለሌሎች መኖር የታገለ ነበር» ሲሉም ይገልፁታል። ሥራዎቹ ዝም ተብለው የሚተዉ አይሆንም የሚሉት አቶ ዳዊት ይፍሩ፣ ተሰብስበው እንዲጠኑና በክብር እንዲቀመጡ ለእርሱም ቋሚ መታሰቢያ ለማኖር ሙዚቀኛው ማህበር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ኤልያስ ሙዚቃን ማቀናበር የጀመረው ‘በገና ስቱዲዮ’ን አቋቁሞ ሲሆን በሙያው ታታሪና ጎበዝ እንደነበር አብረውት የሰሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ኤልያስ መልካ በዋናነት ሊድ ጊታር ከመጫወት ባለፈ የሙዚቃና የዜማ ደራሲ እንዲሁም አቀናባሪ ነበር።
ኤልያስ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ አሻራቸውን ካሳረፉ ወጣት ባለሙያዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎችና ለሙዚቃ ቅርብ የሆኑ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች የመሰከሩለት ከያኒ ነበር። «ሙዚቃ ከነሙሉ ክብሯ በኤልያስ በኩል ታልፋለች» ሲሉ የሚመሰክሩለት ባለሙያዎች፣ የድምፃዊ ቴዲ አፍሮን «አቡጊዳ» ፤ የሚካኤል በላይነህን በ«አንተ ጎዳና» የዘሪቱ ከበደን የሙዚቃ ሰንዱቆች ያቀናበረው ኤልያስ ነው።
የሚኪያ በኃይሉን «ሸማመተው» የእዮብ መኮንንን «እንደ ቃል»፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ኃይሌ ሩት፣ አረጋኽኝ ወራሽ፣ ኩኩ ሰብስቤን፣ ትዕግስት በቀለ፣ የትግርኛ ዘፋኝዋ ማህሌት ገብረጊዮርጊስ፣ ጌቴ አንለይ፣ ቼሊና የኤልያስ ሥራዎች ካረፈባቸው ሥራዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
ኤልያስ መልካ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሕብረ ዝማሬዎችን ያቀናበረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል መላ መላ፣ ማለባበስ ይቅር፣ ለአፍሪካ ሕብረት፣ በትራፊክ አደጋ መከላከል ላይ ያተኮሩት ተጠቃሽ ናቸው። ሁለገብ የሙዚቃ ባለሙያው ኤልያስ ለሙያው ፍቅር በማደር ትዳርም ልጅም አድርጎ የኖረው ሙያውን ነበር። ሥራዎቹ ታዲያ አስመሰገኑት እንጂ አላሳፈሩትምና በተለያዩ ሥራዎቹ ሽልማቶችንና እውቅናን ከተለያዩ ወገኖች አስገኝቶለታል። ኤልያስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በፋና የድምፃውያን ተሰጥኦ ውድድር ላይ በዳኝነት ሲያገለግል መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል።
የልጅነት ጓደኛው እንደሆነ የሚናገረው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ኀዘኑን እንዲህ በማለት ነበር በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ያስፈረው «የሙያ ወንድማችን በነበረው በተወዳጁ የሙዚቃ አቀናባሪ ኤልያስ መልካ ህልፈተ ሕይወት የተሰማኝን ጥልቅ ኀዘን እገልፃለሁ:: ኤልያስ አጭር ሊባል በሚችል የሕይወት ዘመኑ በሙዚቃው ዘርፍ ባኖረው አሻራና የአስደናቂ ችሎታው ውጤት በሆኑት ሥራዎቹ ለምንጊዜውም ከመቃብር በላይ ሲታወስ ይኖራል:: ልዑል እግዚአብሔር ነፍሱን በአፀደ ገነት እንዲያኖርልን እየተመኘሁ ለመላው አድናቂዎቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና የሙያ አጋሮቹ በሙሉ መፅናናትን እንዲሰጥ ከልብ እመኛለሁ።» ሲል ነው።
የዚህ ድንቅ ከያኒ ታላቅ አሻራ ከአረፈባቸው አንዷ የሆነችው ዘሪቱ ከበደ በብሔራዊ ቲያትር በተዘጋጀው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ ስለሙያ አጋሯ በእንባ በመታጀብ እንዲህ ነበር ያለችው «ኤልያስ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት እንዳዘነብል ስላደረከኝ፤ መካሪዬ ስለነበርክ፣ ታዛዥ እና ቅን ስለሆንክም አመሰግንሃለሁ፣ እወድሃለሁ ፣….» በወቅቱ ሽኝቱንም ሊታደሙ የመጡ ሁሉ በዘሪቱ ንግግር አንብተዋል። በኋላም በዕለቱ አርቲስት ዘሪቱ እንዲህ በማለት ተቀኝታለች፡፡
«እንግዳ ነኝ እኔ ስኖር በዚህች ዓለም
ሀብቴም በሰማይ ነው በዚህ ምንም የለም
መላዕክት ይጠሩኛል የሰማይን ደጅ ከፍተው
ከእንግዲህ ይህ ዓለም ፍጹም ቤቴ አይደለም»
ሌላኛው ደራሲ እና ሙዚቀኛ ዮናስ ጎርፌ ሲናገር ኤልያስን የሚያውቀው የያሬድ መዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለ መሆኑን ጠቅሶ ሙዚቀኛ ኤልያስን የመሰለ ማጣት በጣም ልብ የሚሰብር ኀዘን መሆኑን ተናግሯል። ኤልያስ ሙዚቀኛ ብቻ ሳይሆን ፈላስፋም ጭምር ነው ሲል ገልጾታል፡፡«እኔ እና ኤልያስ ምንም እንኳን አብረን የሙዚቃ ሥራ ባንሰራም ጊታር መማሪያ የምትል አንድ መጽሐፍ በጻፍኩበት ወቅት የአርትኦት ሥራ የሰራልኝ እርሱ ነው» በማለት ሁለገብ አዋቂ ተባባሪ ባለሙያ እንደነበር መስክሯል።
ድምጻዊ ጃኪ ጎሲ በበኩሉ «እንደ ኤልያስ መልካ ሁሉም የተስማማበትን ባለሙያ ማግኘት ከባድ ነው። ኤልያስ ሁሉን ያስማማና ያሳመነ ባለሙያ ነው። ኤልያስ መልካ ከ1990ዎቹ ጀምሮ የመጡ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶችን ወደ ፊት ያመጣ እና የጥበብ አሻራውን በከፍታ ያስቀመጠ አንጋፋ እና ታታሪ አቀናባሪ ነበር፡፡ እንደግልም ሆነ እንደ ሀገርም ታላቅ የጥበብ ሰው አጥተናል፤ እንዲህ ዓይነቱ ሙሉ የሆነ አርቲስት ማጣት እጅግ በጣም ልብ ሰባሪ ነው፡፡ ለቤተሰቦቹ ለወዳጅ ዘመዶቹ ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን እመኛለሁ» ብሏል፡፡
ባለድንቅ ተሰጥኦው ኤልያስ መልካ አይረሴ የሆኑትን የጥበብ ሥራዎቹን የከወነባት በገና እስቲዲዮ ዋናዋ ናት። ኤልያስ ለ19 ዓመታት በቆየበት የሙዚቃ ሕይወቱ 40 የሙዚቃ አልበሞችን አበርክቶ በተወለደ በ42 ዓመቱ አርብ መስከረም 23 ቀን 2012ዓ.ም ከሌሊቱ 9 ሰዓት ይህችን ዓለም ተሰናብቷል። የቀብር ሥነሥርዓቱ ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም ጴጥሮስ ወ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተፈጽሟል። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የዝግጅት ክፍልም ለወዳጅ ዘመድ እንዲሁም ለአድናቂዎቹና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ይመኛል፡፡ መልካም ዕለተ ሰንበት!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2012
አብርሃም ተወልደ