ሕገወጥ ንግድን መልክ ለማስያዝ ተጠባቂ የሆኑ አገልግሎቶች በተለያየ መልኩ እንደሚሰጡ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በመንግሥት ደረጃ መታቀዱ ደግሞ ኢኮኖሚው እንዲያንሠራራ ከማድረግ አንፃር የማይተካ ሚና እንዳለው ምሁራን ይገልፃሉ፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እንደተናገሩት፤ ሕገወጥ ንግድ አገሪቱን ከመጠን በላይ እየፈተናት ነው፡፡ ስለሆነም መልክ ማስያዙ ላይ በትኩረት መሠራት አለበት፡፡ ለዚህ መንግሥት በ2012 ዓ.ም ተጠባቂ የሆነ አገልግሎትን ለመስጠት ይሠራል። በተለይም የኮንትሮባንድ፣ የታክስ ማጭበርበርና ታክስ መሰወርን ለመግታት ፍላጎት ተኮር የሆነውን የአሠራር ዘዴ ወደ አቅርቦት ተኮር ማሸጋገር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
‹‹ በመንግሥት ደረጃ ይሄ መታሰቡ ከመቼውም ይልቅ ኢኮኖሚውን ከፍ ያደርገዋል›› ያሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሸዋፈራሁ ሽታው በበኩላቸው፤ የአገልግሎት አሰጣጡ ክፍተት ያለበት መሆኑ ለሕገወጥነት በር ይከፍታል። በሌላ በኩል ደግሞ መረጃ በተገቢው መልኩ ለተገቢው አካል ማድረስ አለመቻሉ ሕገወጦች እንዲንሠራፉ እንደሚያደርግ ይናገራሉ። አብዛኛው ህዝብ በህጋዊ መንገድ ከሚተላለፈው መረጃ ይበልጥ በተዘዋዋሪ የሚደርሰውን ስለሚቀበል ችግሩ በዚህ ምክንያት የመጣ መሆኑን ያነሳሉ። ነጋዴው ማህበረሰብም በመንግሥት መመሪያ እንዳይጓዝ የተገደበው በአሠራር ክፍተቱ መሆኑን ይገልፃሉ።
ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና አሁን ባለው ሁኔታ ነጋዴውን ወደ ሕገወጥነት እንዲገባ የሚያደርገው የታክስ ታሪፉ ከፍተኛ ጫና መኖር ነው ሲሉ የአቶ ሸዋፈራሁን ሐሳብ ያጠናክራሉ። መንግሥት ከነጋዴው ጋር በመተማመን ሳይሆን ሕጉን ተንተርሶ ብቻ ግብር እየጫነ ነጋዴውን ያስጨንቃል። ነጋዴውም ተገቢውን አገልግሎት እያገኘሁ ስላልሆነ በማለት ወደ ታክስ ማጭበርበርና መሰወር ይገባል። ስለዚህ ዕቅዱ መልካም ቢሆንም መጀመሪያ ግን ችግሩ በጥናት ተለይቶ መፍትሄ መቀመጥ አለበት ሲሉ ይሞግታሉ።
ሕገወጥ ንግድ እንደትልቅ ጉዳይ እንዲነሳ ያደረገው ድህነታችን ነው። የአብዛኞቹ ነጋዴዎች ሥራ ከእጅ ወደ አፍ ነው። ስለዚህ ችግራቸውን ለመፍታት ያልተደፈኑ የመንግሥት ክፍተቶችን ማየት ላይ ያተኩራሉ። ስለዚህ ታክስ ሲጣል ለሚገባው የሚገባውን ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።
የዓለም ባንክ በጥናቱ የንግድ አሠራሩ በጣም ደካማ ነው ሲል አስቀምጧል። ስለሆነም በአሠራር ላይ አትኩሮ ለመሥራት መታቀዱ ይበል ያሰኛል ያሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ ሰኔ ላይ የቢዝነስ አሠራርን ቀላል ለማድረግ የሚያስችል አዋጅ መውጣቱ፤ አሁንም ለመሥራት መታቀዱ ብዙ ችግሮችን እንደሚፈታ ይናገራሉ።
ህብረተሰቡን ጠያቂ እንዲሆን ማስቻል፣ የንግድ አሠራርን ቀላል ማድረግ፣ የታክስ መጠንን ዝቅ አድርጎ መሥራት መፍትሄ መሆኑን የሚያስረዱት አቶ ሸዋፈራው፤ አሁን ባለበት ደረጃ መንግሥት ከሚሰበስበው ይልቅ የተሰወረው ግብር ይበዛል። ስለሆነም ታክስን ቀንሶ ብዙ መሰብሰብ ላይ ማተኮር አለበት ይላሉ። የታዳጊ አገራት የኢኮኖሚ ችግሮች ከሚገለጽባቸው ጠባያት አንዱ መረጃን በወቅቱ በተሳለጠ ሁኔታ ለተገቢው አካል ያለማድረስ ነው። በዚህም ትክክለኛ መረጃ በወቅቱ ለተዋንያኑ ማድረስ ላይ መሠራት እንዳለበት ይመክራሉ። አሁንም ሕገወጥ ንግድን መልክ ለማስያዝ የታክስ ጉዳይ በአግባቡ መታየት እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በ2011 ዓ.ም ከገቢ ኮንትሮባንድ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እና ከወጪ ኮንትሮባንድ 0 ነጥብ 33 ቢሊዮን ብር በድምሩ ግምታዊ ዋጋቸው ብር 1 ነጥብ 63 ቢሊዮን የሚሆን ገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ሥር ውሏል። በኮንትሮባንድ ተግባር ላይ የተሳተፉ 1 ሺ 107 ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል።
መንግሥት ያቀደውን ነገር ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ከተደረገ እና በአሠራር ያሉ ችግሮች ከተደፈኑ በቀጣይ ሕገወጥ ንግድ መልክ ይይዛል። ሕገወጥነት ተወግዶ አገር በትክክለኛው የኢኮኖሚ ዕድገት መስመር ትጓዛለች።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው