አዲስ አበባ፡- የአንድነት ፓርክ መንግሥትንና ሕዝብን በማቀራረብ፤ የተለያዩ የማህበረሰብ አካላትን በማገናኘት እና የጋራ ታሪክን በማስገንዘብ የርዕስ በርዕስ ግንኙነትን የሚያጠናክር መሆኑን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደገለፁት፤ በብሔራዊ ቤተመንግሥት ውስጥ የተሠራው የአንድነት ፓርክ የአድዋ ጦርነት የታወጀበት፤ ከአድዋ ዘመቻ በኋላ በጦርነቱ ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች ሙታመት የወጣበት፤ ማይጨው ሲዘመት ክተት የታወጀበት፤ እስከ 1966 ዓ.ም ፍርድ የሚሰጥበት ዙፋን ችሎት የነበረ፤ ንግሥት ዘውዲቱ የነገሡበትና ያስተዳደሩበት፣ እንዲሁም እስከ ኢህአዴግ ድረስ ብዙ መልካምና አስከፊ ውሳኔዎች የተላለፉበት ታላቅ የታሪክ ቦታ ለህዝብ እይታ ክፍት መሆኑ ሁሉም ታሪክን ጠንቅቆ እንዲያውቅ ያደርገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ዘመናዊውን የኢትዮጵያን ታሪክ ምን ይመስል ነበር የሚለ ውንም ያስተምራል ብለዋል፡፡
“የአንድነት ፓርክ በየትኛውም አገር ያልተለመደ ነው፡፡ እንደ ሀገርም ትልቅ እርምጃ የተራመድንበት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በአፍሪካ ውስጥ ቀደም ሲል ቤተመንግሥት የነበሩ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሙዝየምነት ከማገልገል ውጭ እንደ ኢትዮጵያ ግማሹ የቤተመንግሥቱ አካል የአስተዳደርን አገልግሎት እየሰጠ ለህዝብ ክፍት የሆነበት ሀገር የለም። ይህም ሁኔታ ህዝብንና መንግሥትን በማቀራረብ በኩል ያለው ሚና ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ሕዝብ የሀገር ስሜት እንዲሰማው በማድረጉ በኩል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት” ሲሉ ተናግረዋል።
ህዝብና መንግሥት በአካልና በሥነ ልቦና ሲራራቁ ሀገርን በማስተዳደሩ ዙሪያም ክፍተትን ይፈጥራል። በአንድነት ፓርክ የተጀመረው ህዝብና መንግሥትን የማቀራረቡ ሁኔታ ወደፊትም አድጎ የሀገር መሪዎቻችን ልክ ንጉሡ ያደርጉት እንደነበረው በህዝቦች መካከል መሄድ ሊመጣ እንደሚችል ተናግረዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም እንዳብራሩት ታሪክ ህዝቦችን የማገናኛ መንገድ ነው። በተለይ ደግሞ አንድነት ፓርክ ህዝቦችን የማገናኘትና የማቀራረብ ከፍተኛ ኃይል አለው። የርዕስ በርዕስ ትስስርን ከመፍጠርም በላይ የተለያዩ ባህሎችን በመማማር ግንኙነታችንን አንድ ደረጃ ከፍ የምናደርግበት ቦታ ነው። ያለፈው ታሪክ ክፉም ይሁን ጥሩ ይቅር በማለት ወደፊት በአንድነት መጓዝ ያስፈልጋል።
“መደመር ሲባል ያለፈውን በመደምሰስ ሳይሆን እውቅና በመስጠት ነው “የሚሉት አቶ አበባው ያለፈውን ታሪክ መለወጥ ስለማንችል ይቅርታ በማድረግና እውቅና በመስጠት ወደፊት መጓዝ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2012
ሞገስ ፀጋዬ