ዕለቱ ቅዳሜ ነው። የረፋዷ ፀሐይ ከረር ማለት ጀምራለች። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርማ ያለበት አውቶቡሶች በሰልፍ ቆመዋል። አካባቢው ነጭ ቲሸርት በለበሱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሚሠሩ ተማሪዎች ተሞልቷል። በላምበረት መናኽሪያ የተደረገው ይሄ ዝግጅት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው የተመደቡ ተማሪዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ ለመቀበል ነው።
ሰዓቱ ደርሶ ተማሪዎቹ መምጣት ጀምሩ፤ ግማሹ ቀሪ ተማሪዎችን ሲጠባበቅ የተቀረው በጊዜ የደረሱትን ተማሪዎች በተዘጋጁት አውቶቡሶች በመያዝ ጎዞ ወደ ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ አደረግን። በተማሪዎች ፊት ላይ ደስታ፣ ተስፋ እና ወንድማማችነት ይታያል። ከአዲስ አበባ ውጭ የሚመጡ ተማሪዎች 3ሺ 500 ድረስ እንደሚሆኑም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ደመቀ አጭሶ ገልፀዋል።
እንደ ዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገለፃ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ከተለያዩ የአገሪቱ ቦታ የሚመጡትን ተማሪዎች እንዲህ ባለ መልኩ መቀበል ተማሪዎችን ከውጣውረዶች ከማዳን ባሻገር ተማሪዎቹ በግቢው ውስጥ ለሚኖራቸው ቆይታ ትልቅ ተስፋ እንዲሆናቸውና የመማር ፍላጎታቸውን ከፍ ያደርገዋል።
ተማሪዎችን በማስተናገድ ላይ ሲተጋ የነበረው የሦስተኛ ዓመት የጂኦግራፊ እና ኢንቫይሮመንታል ሳይንስ ተማሪ የሆነው አስፋው ደሞዝ ነው፤ ዘንድሮ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የተደረገው አቀባበል ደስ የሚል መሆኑንና የአቀባበሉን ሥነ ሥርዓት የሚከውኑት በበጎ ፍቃድ እንደሆነ ይናገራል። ተማሪዎች ሳይጉላሉና ንብረት ሳይጠፋባቸው ደስ ብሏቸው ትምህርታውን እንዲያከናውኑ በማሰብ ነው። ተማሪዎቹም በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸው እሱንም ደስታ እንደፈጠረለት ነው የተናገረው። ይሄ መተሳሰብ ተማሪዎች በቀጣይ ለሚኖራቸው የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ትልቅ ስንቅ እንደሚሆናቸው ገልጿል።
ሌላኛዋ በበጎ ፍቃድ ተማሪዎችን ስታስተናግድ የነበረችው የሦስተኛ ዓመት የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ተማሪ ማናይም ጀምበሩ ናት። እንደ ማናይም ገለፃ ከተማሪዎች አገልግሎት ቢሮ አዲስ ገቢ ተማሪው የትኛው የመኝታ ክፍል እንደተመደቡ መረጃ በመቀበል እንዲሁም ከክልል የመጣ ተማሪ በራሱ ቋንቋ አናግሮ የሚቀበለው ሰው በማዘጋጀት ምንም ዓይነት መጉላላት ሳይደርስበት በሰላም ወደተመደበበት መኝታ ክፍሉ እንደሚያስገቡ ተናግራች።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2012
አብርሃም ተወልደ