ሊቀጳጳስ ዶክተር አቡነ አረጋዊ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ያገኙት የሰላም ኖቤል ሽልማት ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ኩራት ነው። ኢትዮጵያ የተለያዩ ሁከቶች ባጋጠሟት በዚህ ወቅት ሽልማቱ መገኘቱ ለሰላም ዋጋ እንዲሰጥ የአደራ መልዕክት ጭምር የሚያስተላልፍ ነው።
ሽልማቱ ከአሁን በፊት ለተሰሩት ሥራዎች ብቻ ሳይሆን ወደፊትም በሰላም ዙሪያ ያላሰለሰ ጥረት መደረግ እንዳለበት አመላካች ነው። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በሰላም ዙሪያ ጠንክሮ መስራት በሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ሽልማቱ መገኘቱ መልካም ዜና ነው። ለኢትዮጵያ መጻኢ ተስፋ ጥሩ መሠረት ይሆናል።
አባ ሀጎስ
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህን
ኢትዮጵያ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆና ሽልማቱ መገኘቱ ደስ አሰኝቶኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በአመራርነታቸው በወሰዱት ተነሳሽነትና በሚመሩት ሕዝብ ድጋፍ የተገኘ እንደሆነም አምናለሁ።
ሽልማቱ በሰላም ዙሪያ፣ አብሮ በመኖርና በመተሳሰብ ላይ መልካም የሆኑ እሴቶችን ለማጎልበት ትልቅ ጥቅም አለው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አንድ በሚያደርገው ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ በጋራ ወደ ልማት እንዲገባና እንዲረባረብ ብሎም በጎ አመለካከት እንዲኖረው ያበረታታል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር እድሪስ
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት
የዶክተር ዓብይ የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማት የሚያስደስተው እርሳቸውን ብቻ አይደለም። ይልቅ መሸለማቸው የሚያስደስተው በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ላሉ ኢትዮጵያ በሙሉ ነው። አንድነት ፓርክ ሲከፈት የተመለከቱትም በዓለም ማማ ላይ የሚያስቀምጣቸው ተግባር መሆኑን ተገንዝበዋል።
እርሳቸው ከእዚህም በላይ የሚገባቸው ሰው ናቸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ የሰሩት ሥራ ቢቆጠር እያንዳንዱ ተግባር ይህንን ሽልማት የሚያስገኝ ነው።
በዚህ ሽልማት አላህ የተቆጣው ካልሆነ በቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ወንዱ፣ ሴቱ፣ አስተማሪው፣ ተማሪው፣ ወላጁ፣ ልጁ፣ የሃይማኖት አባቶች በአጠቃላይ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ያሉ በሙሉ ይደሰታሉ። ደስታችን እጥፍ ድርብ ነው።
ለወደፊቱም በአገራችን ሰላም እንዲሰፍን እመኛለሁ። ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት ሕዝቡ ደህና ሲሆን ነው። አስተማሪው በመልካም ሥነ ምግባር ትውልድ ሊቀርጽ፣ ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን ሊከታተሉ፣ ወላጆችም ልጆቻቸውን በአግባቡ ሊያሳድጉ ይገባል። በመንግሥት ኃላፊነት ከላይ እስከ ታች ያሉ አመራሮች የተጣለባቸውን አደራ ሊወጡ ይገባቸዋል።
የጸጥታ አካላትና አገልግሎት ሰጪ አካላት ሕዝባዊ እና አገራዊ አመለካከት ሊያሰርጹ ይገባቸዋል። ይህ ሲሆን አንድነታችን ይጠናከራል፣ ሰላም ይሰፍናል፣ አገር ይለማል፣ ከድህነትም እንወጣለን።
ፓስተር ጻድቁ አብዶ
የዶክተር ዓብይ የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማት የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የተሰጠ ሽልማት ነው። ሽልማቱን የሰጡት አካላት በርካታ ጉዳዮችን ከግንዛቤ አስገብተዋል ብዬ አምናለሁ፤ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ከ20 ዓመታት በኋላ ለፈጠረችው ሰላም፣ በደቡብ ሱዳን እና በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ዶክተር አብይ የተጫወቱትን ሚና፣ በአገር ውስጥም ሁከትና አለመግባባት ሲኖርና ብዙዎቻችን የሕግ የበላይነት መቼ ነው የሚከበረው ብለን ስንጠይቅ በትዕግስትና በሰላም ለመፍታት የሚይዙበት አጠቃላይ መንገድ ለመሸለማቸው ምክንያት ነው።
‹‹እንደ አንድ ኢትዮጵያዊና በቅርበት ዶክተር አብይን እንደሚያውቅ ሰው በመሸለማቸው እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። አገሪቱን እየመሩ በመሆኑም እንዲሳካላቸው እጸልያለሁ››
በፊትም በጋራ በእዚህ አገር ኢትዮጵያውያን አብረን ኖረናል። ክፉ ደጉን ተመልክተን እዚህ ደርሰናል። የብሔር፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የጾታ፣ የመደብ እና የእምነት ልዩነት ቢኖረንም ኢትዮጵያውያኖች ነን። ሰው መሆናችን እና አፍሪካውያን በመሆናችንም አንድ ያደርገናል።
በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ለአንተ ሊደረግልህ የምትወደውን እንዲሁ ለሌላው አድርግ፣ አንተ ላይ እንዲደረግብህ የማትወደውን በሌላው ላይ አታድርግ፣ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ እንደሚለው መኖር ይገባናል ብለዋል።
በሰላም በፍቅር፣ በመከባበር፣ በአንድነት ኖረን ለሌላው ዓለም ምሳሌ እንድንሆን እመኛለሁ። ከመቻቻልም ባለፈ እርስ በእርሳችን ተቀባብለን፣ ተከባብረን ተዋድደን መኖር ይገባናል። በመከባበር፣ በፍቅርና በአንድነት አብረን የምንኖርባት፣ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያ እንድትኖር ፍላጎቴም ምኞቴም ነው።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ
በግልም ሆነ በአገር ደረጃ ደስ ይላል። ደስ የማይለው ሰው መኖር የለበትም። በጣም ጥሩ ነው ደስ ብሎናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአገራት ጋር ስለሰላም ትልቅ ነገር ሠርተዋል።
በመጀመሪያ ኤርትራ ከዚያ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ሶማሊያ በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ የተጫወቱት ሚና ሽልማቱን የሚያስገኙና መስፈርቱን የሚያሟሉ ናቸው። በሠሩት ሥራ ሽልማቱን እንደሚያገኙም እጠብቅ ነበር። ለብዙ ዓመታት አይነኬ፣ አጨቃጫቂና አከራካሪ የነበረውን ጉዳይ በድፍረት ኤርትራ ድረስ ሄደው ሁኔታዎችም ያረገቡትና ያደረጉት ነገር ቀላል ነገር አይደለም።
ኢህአዴግ በፖሊሲ ደረጃ ወስነናል ማለታቸውን ሰምቼ ነበር። በመሪ ደረጃ ግን ይህን ደፍሮ ያደረገ አልነበረም። የኖቬል ሽልማት ግለሰብ ወይንም ድርጅቶች ሊሸለሙ ይችላሉ። እያንዳንዱ አገር ሽልማቱን ያገኘው ድርጅት ወይንም ግለሰብ የሚኮራበት ነው።
ይህ ሲባል የኢትዮጵያ ሕዝብ ትብብር ባይኖር ሊያገኙ አይችሉም ነበር። ለምሳሌ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ፍጥጫ ለማርገብ የነበረውን እርምጃ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ቢቃወም ለዚህ አይበቁም ነበር። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሚና አለው፤ ሽልማቱም የሕዝቡ ጭምር ነው።
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ
እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። ሽልማቱ በጣም የሚያስደንቅ ነው። በታላቁ ዓለም አቀፍ የኖቤል ሽልማት እንኳን ማሸነፍ ዕጩ ሆኖ መቅረቡ ብቻውን ወርቃማ ገድል ነው። ሽልማት ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንደሚሰጠው ለመገንዘብ ለዚህ ሽልማት የበቁትን ወደኋላ መለስ ብሎ መመልከትና ኔልሰን ማንዴላን ማስታወስ ብቻ በቂ ነው።
ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማት በመውሰዱ ዓለም እኛን እንዲመለከት ያደርጋል። ድሉ የአገሪቱ ስም በደማቅ ወርቃማ ቀለማት ተፅፎ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሲታወስ እንዲኖር የሚያደርግ ነው።
በአትሌቲክስ ስናሸንፍ ኢትዮጵያዊው አትሌት ተብሎ እንደሚጠራው ይህ ሽልማት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሆንም የምትጠራው አገሩ ናት። አሸናፊው ዶክተር አብይ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም ናት። ይህም ሽልማቱን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሽልማት ያደርገዋል።
የአገሪቱ ሕዝብ ለሰላም ያለው ዋጋ ምን ይህል እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነውና ይህን ሽልማት፣ እንደርሳቸው ብቻ ሳይሆን እንደ አገር መወሰድ ግድ ይለዋል። ይህን በመመልከት ለሰላም የምንሰጠው ዋጋ ከፍተኛ መሆን አለበት። ሰላም እንደሚያሸንፍ ለመረዳት ከዚህ በላይ በቂ ምስክር የለም። ሰላም ስንሆን አሸናፊ እንደምንሆን መረዳት ካለብን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወርቃማ ድል ነው። አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር