የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን የኖቤል የሰላም ሽልማትን ተከትሎ አለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችና መንግስታት ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። መንግስታቱና የተቋማት መሪዎቹ ደስታዎ ደስታችን ነው፤ ስራዎትን እናውቃለንና ሽልማቱ ይገባዎታል ሲሉ መልዕክታቸውን አድርሰዋል። ይህ መልዕክትም እንዲህ ቀርቧል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሀመት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን በመስጠት የሚደነቅ ተግባር ፈፅመዋል ሲሉም ነው የገለፁት። እንዲሁም በሀገሪቱም ብሎም በቀጣናው እና በአህጉሪቱ መረጋጋት እንዲፈጠር እና ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን አንስተዋል።
የአለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስም ሌላው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ያስተላለፉ ሰው ናቸው። እርሳቸውም በዚሁ መልዕክታቸው፤ “ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ብልፅግና ለማስፈን ላበረከቱት አስተዋፅኦ ትልቅ እውቅና ነው” ብለዋል።
በተመሳሳይም የተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ዛይድ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “በኢትዮጵያ እና በአካባቢው ሰላምን ያሰፈነ እና ተስፋን የፈጠረ ብልህ ሰው ሲሉ አድናቆታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።”ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ላሳዩት ብቁ አመራር ይህ የኖቤል የሰላም ሽልማት ይገባቸዋል” ብለዋል ልዑል ሸክ መሀመድ ቢን ዛይድ።
የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በበኩላቸው፤ “የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ወንድም የኢትዮጵያ ህዝቦች የ2019 የኖቤል ሽልማት ዶክተር አብይ አህመድ በማሸነፋቸው እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀመዶክም የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የክብር እና የደስታ ምክንያት ናቸው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትክክለኛ አመራርነት እና አገልግሎት ለሁሉም ምሳሌ የሚሆን ነው” ሲሉም ገልፀዋቸዋል። በአካባቢው የኢኮኖሚ መረጋጋት እንዲፈጠር እና ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ነው አብደላ ሀመዶክም በመልዕክታቸው የገለጹት።
ሌላኛው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ የኬንያው ፕሬዚዳንት እሁሩ ኬንያታ ናቸው። እርሳቸውም፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና እርቅ እንዲፈጠር ላበረከቱት አስተዋፅኦ አለም አቀፍ እውቅና ይገባቸዋል። የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በማሸነፋቸው የኢትዮጵያ ህዝብ እና ዶክተር አብይ እንኳን ደስ አለዎት፤ ሽልማቱም ይገባዎታል” ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ኬንያታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በኢትዮጵያ ፣ በቀጣናው እና በአህጉሪቱ ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልፅግና እንዲፈጠር በከፍተኛ ሁኔታ እየሰሩ ይገኛል ሲሉም አክለዋል።
የላይቤሪያው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል የሰላም ሽልማት በማግኘታቸው ለአፍሪካና ለአለም ህዝብ ከፍተኛ ደስታ ፈጥሯል ነው ያሉት።
ለአፍሪካ ተጨማሪ ኩራት ለሆነው ለዚህ አጋጣሚ የላይቤሪያ መንግስት እና ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት ይፈልጋል ሲሉ በፌስቡክ ገፃቸው አስፍረዋል።
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሀሙዱ ቡሃሬ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለ20 ዓመታት የዘለቀውን የኢትዮ ኤርትራን ግጭት መቋጫ በመስጠት የኖቤል የሰላም ሽልማት ስላሸነፉ እንኳን ደስ አለዎ በማለት የደስታ መልዕክት አስተላልፈዋል። “ይህ እውቅና በሀገሪቱ እና በአጠቃላይ በአህጉሪቱ እየተካሄደ ላለው የሰላም ሂደት ጥሩ ምሳሌ ነው” ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር