2012ን ሀ ብለን የተቀበልንበትና በበርካታ ሕዝባዊ በዓላት የደመቀው ወርሃ መስከረም በመሰናበቻው ቀን ለእኛ ኢትዮጵያውያን ደስ የሚል ዜናን አሰምቶን ተሰናብቷል። መስከረም 30/2012 ዓ.ም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የዓለም የሰላም የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው ተበስሮበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ከበዓለ ሲመታቸው አንስቶ ስለሰላም አበክረው የመናገራቸውን ያህል ሰርተውም አሳይተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ሀሳብ ሰምሮ በአገር ውስጥም ሆነ በጎረቤት አገራት ሰላም የሰፈነው ደግሞ በመላ ኢትዮጵያውያን ያላሰለሰ ጥረትና ድጋፍ ነውና ድሉ የመሪያችን ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያንም ነው!
ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት ነው። ያለሰላም ወጥቶ መግባት፤ ደምቆ መኖር፤ ተምሮ መመረቅና ወልዶ መዳር አይታሰብም። ስለሆነም ለዚህ ቅዱስ ተግባር ለፍቶና ውጤት አስመዝግቦ መሸለም የሽልማቶች ሁሉ አልፋና ኦሜጋ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ስለሆነም ለዚህ ትልቅ ድል የበቁትን የአገራችንን ጠቅላይ ሚኒስትርና መላ ሕዝባችንን ደግመን ደጋግመን እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እንወዳለን!
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የዓለም የኖቤል ተሸላሚ መሆን ለአገራችን የሚያስገኘው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው። ለማንም ግልጽ እንደሆነው አገራችን ለዘመናት የምትታወቀው በሰላም መደፍረስና እጦት ነበር። ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ለመውጣትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የለውጥ አመራር ብዙ ደክሟል።
ክብር ለሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንና ልፋቱ ከንቱ ሳይቀር በብዙ ቦታዎች ይታዩ የነበሩ ግጭቶች እንዲረግቡና የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደየቀዬያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ተችሏል።
ጎረቤት ሰላም ካላደረ እኛም ሰላም አይኖረንም በሚል እሳቤም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተከናወነ አኩሪ ተግባር መቋጫ አይኖረውም የተባለለትን የኢትዮጵያና ኤርትራ ግጭትና ፍጥጫ በመፍታት በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል የፍቅር ድልድይ መገንባት ተችሏል።
የኤርትራና ጅቡቲን ግጭት በማስቆም ሰላም ለማስፈን በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ግንባር ቀደም መሪነት ብዙ ተደክሟል። ወንድም የሆነው የሱዳን ሕዝብ የገጠመውን ችግር ለመፍታትም ኢትዮጵያና መሪዋ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወታቸው አሁን በሱዳን ለሰፈነው ሰላም መሠረት ለመሆን ተችሏል። በየመን ለተከሰተው የሰላም መደፍረስ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን መፍትሄ እንዲያመጡ መመረጣቸውም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
በአጠቃላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የሰላም አምባሳደር በመሆን በአገራችንና በጎረቤት አገራት ካበረከቱት አስተዋጽኦ አንጻር ሽልማቱ ለተገቢው ሰው ተሰጥቷል ብሎ መደምደም ይቻላል። ከላይ እንደገለጽነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ሃሳብና ጥረት ፍሬ ያፈራው ደግሞ በመላ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ነውና ድሉ የመላ ኢትዮጵያውያንም ድል ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012