ጠቅላይ ሚኒስትር ዶከተር አብይ አህመድን የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል። ይህ ሽልማት በብዙ መልኩ እንደሚገባቸው ብዙዎች እየተናገሩ ነው። ሰላማዊው ተቋምም ዶክተር አብይ ለዚህ ሽልማት ያበቃቸው በድንበር ግጭት ምክንያት ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ የነበሩትን የኢትዮጵያንና የኤርትራን ፍጥጫ መፍትሄ እንዲያገኝ በማድረጋቸው መሆኑን አስታውቋል።
ዶ/ር አብይ በሚያዝያ 2011 በኢትዮጵያና ኤርትራና መካከል የነበረውን የድንበር ፍጥጫ የቋጩት ሁሉንም ወገን ባስደመመና ለ20 ዓመታት ከቆየው ጸብ አንጻር ይሆናል ተብሎ ባልተገመተ መንገድም ጭምር ነው። ራሳቸው ኤርትራ በመሄድ የፕሬዚዳንት ኢሳያስን እጅ ጨብጠው ዓለምን አስደምመዋል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃ በአገራቱ ጸብ ምክንያት ልባቸው ተሰብሮ የነበሩ የሁለቱ አገራት ዜጎችን አስነብቷል፤ የዓለም አገራትንም ምሳሌ የሚሆን የግጭት አፈታት አስብሏል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ጉዞ በኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴ ዓይን ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸው ነበርና ወዲያውኑ ዕጩ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል። ከወራት የልየታ ማጣራት በኋላም ዶ/ር አብይን ትናንት ረፋዱ ላይ የ2019 የኖቤል የሰላም አሸናፊ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ናቸው ሲል ብስራቱን ለአገራችን፤ ብስራቱን ለሰላም ወዳድ የዓለም ሕዝብ ሁሉ አሰምቷል።
ይህንን የደስታ ዜና ተከትሎም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት፣ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የክልል መንግሥታት እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን ደስ አለን መልዕክት አስተላልፈዋል። እነዚህን የደስታ መልዕክቶችም ጋዜጣችን እንዲህ ይዟቸዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
«ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዓብይ አህመድ የ2019 የኖቤል ሠላም ሽልማትን አገኙ! እንኳን ደስ አለዎት! እንኳን ደስ አለሽ እናት አገር ኢትዮጵያ! በአገራችን አራቱ ማዕዘን፤ በዓለም ዙሪያ የምትኖሩ የዚች የተባረከች አገር ልጆች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ!»
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር
አቶ ደመቀ መኮንን
«ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በሰላም የኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው የተሰማንን ልዩ ደስታ እና ጥልቅ ክብር ለመግለፅ እንወዳለን። ሽልማቱ ለሀገራችን እና ለትውልዱ የሚኖረው አወንታዊ ትርጉም እጅግ የላቀ በመሆኑ ሁላችንም እንኳን ደስ አለን»።
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት በማሸነፋቸው የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክት አስተላልፏል። «ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተሸለሙት የኖቤል የሰላም ሽልማት ሀገሪቱ የጀመረችው የሰላም ጉዞን አጠናክሮ ለመቀጠል እንደሚያስችል እምነታችን ነው» ብለዋል።
የአፋር ክልላዊ መንግሥት
የአፋር ክልላዊ መንግሥት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንኳን ደስ አለዎት ብሏል። የአፋር ክልል መንግሥት በመግለጫው፤ «ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገብታ የነበረችውን ሀገር ብልሃት በተሞላበት አመራራቸው ወደ ተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምትሸጋገርበት ምዕራፍ ላይ በማድረሳቸው ሽልማቱ ይገባቸዋል» ብሏል።
የአማራ ክልላዊ መንግሥት
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት ማሸነፍን ተከትሎ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላልፏል። «ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሸነፉት ሽልማት መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በሰላም በመኖር በኩል ካላቸው የረጅም ጊዜ የካበተ ልምድ ተቀድቶ ለፍሬ የበቃና ለሰላም ወዳድ ዜጎቻችን ሁሉ የተበረከተ ታላቅ ሽልማት ነው። ሽልማቱ በሰላም፣ በእርቅና ይቅርታ በኩል የተጀመሩ መልካም እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ታላቅ አደራን ጭምር ያሸከመ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም የጀመሩትን የሰላምና የአንድነት መንገድ አጠናክረው እንደሚቀጥሉና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውም ሰላምና መረጋጋት ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ የክልሉ መንግሥት ጽኑ እምነት አለው»።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማትን በማሸነፋቸው እንኳን ደስ አለዎት ብለዋል። «ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ»።
የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸው ደስታቸውን በክልሉ ሕዝብ እና በራሳቸው ስም ገልፀዋል። በዚሁ መልዕክታቸውም፤ «ዶክተር አብይ አህመድ በሀገራዊ ለውጥ ብቻ ሳይሆን በአጠቃይ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሰላም አየር እንዲተነፍስ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሽልማቱ ይገባቸዋል» ብለዋል።
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ በራሳቸውና በክልሉ ሕዝብ ስም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። «ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙት ስኬት ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም በአርአያነቱ የሚጠቀስ ነው። ሽልማቱ ሀገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ይበልጥ ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ ነው። የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማብሰር እንደ ማዕዘን ድንጋይ የሚያገለግል ይሆናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመደመር እሳቤ የሀገራችንን ሕዝቦች ወደ ብልጽግና ለማሻገር እያደረጉት ያለው በሳል የአመራር ክህሎት የሚደነቅ ነው»።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተሰጠውን የሰላም ኖቬል ሽልማት በማስመልከት የደስታ መልዕክት አስተላልፈዋል። «ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያገኙት ዓለም አቀፍ የሰላም ኖቬል ሽልማት በቀጣይም ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ የማድረስ የአመራር አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ ነው»።
የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን ተከትሎ ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። «ሽልማቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሰላም የይቅርታ እና የእርቅ ሥራ ፍሬ ነው፤ ሽልማቱም የመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሽልማት ነው»።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ በእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክታቸውም ተከታዩን መልዕክት አስተላልፈዋል። «ሽልማቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሰላም፣ የይቅርታ እና የእርቅ ሥራ ፍሬ ነው። ይህ ሽልማት የዶ/ር አብይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሽልማት ስለሆነ ሁላችንንም እንኳን ደስ ያለን። የከተማ አስተዳደሩ ዶ/ር አብይ አህመድ ባገኙት የኖቤል ሰላም ሎሬት ሽልማት የተሰማውን ኩራት ይገልፃል»።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸው የተሰማውን ደስታ በከተማ አስተዳደሩ እና ሕዝብ ስም በመግለጽ መልካም የሥራና የስኬት ጊዜ ተመኝቷል።
የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት በማግኘታቸው መደሰቱን የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ገለጹ። የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሽልማቱን በማግኘታቸው የክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ደስታ ተሰምቷቸዋል። የአልፍሬድ ኖቤል ተቋም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን በዓለም ታዋቂነት ካላቸው ሰዎች መካከል አወዳድሮ መሸለሙ ምስጋና እንደሚገባውም ተናግረዋል።
ሽልማቱ ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱና በጋምቤላ ክልል ላደረጉት አስተዋጽኦ ዕውቅና መስጠት መሆኑንም አመልክተዋል። በተጨማሪም ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች መካከል ሰላምን ለማምጣት ያደረጉት ጥረት መገለጫ አድርጎ መውሰድ እንደሚቻልም ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሰላም ስምምነት በማድረግ ያስመዘገቡት ውጤት ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል። በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል የነበረው አለመግባባት በሰላም እንዲፈታ ያደረጉት እንቅስቃሴም ተጠቃሽ መሆኑን አቶ ኡሞድ አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሱዳን የአመራር ለውጥ ከተደረገ በኋላ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በመፍታት የተጫወቱት ሚና ቀላል እንዳልነበር አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር