ልቧ ብሩህ ቢሆንም አይኖቿ ግን ብርሃን የላቸውም። ጥቁር መነጽሯን አድርጋ፤ አቅ ጣጫ መጠቆሚያ በትሯን ይዛ በየጊዜው ወደ ትምህርት ቤት ስትመላለስ ያይዋት የነበሩ የሚረዳት ቢኖር እንጂ ብቻዋንማ አትኖርም ብለው ይናገሩ እንደነበር አትረሳውም። ፒያሳ አካባቢ ደግሞ ሎተሪ ስታዞር የሚያዩዋት ትማራለች ብለው አይገምቷትም ነበር።
እርሷ ግን ብርቱ ነች ከትምህርት መልስ በምታገኛት ጊዜ ሎተሪ አዙራ ከምታገኘው ገቢ የቤትኪራይ እና የትምህርት ወጪዋን ችላ ለዓመታት ኖራለች። የምትኖረው ደግሞ ብቻዋን ነው። ማንም ረጂ ማንም ሃሳብ ተካፋይ በሌለባት አንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ተከራይታ። ባለታሪኳ ቃልኪዳን ማንያዘዋል ትባላለች አሁን ላይ 12ኛ ክፍልን አጠናቃ ወደዩኒቨርሲቲ የሚያስገባትን ውጤት አግኝታለች።
ወጣት ቃልኪዳን «ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሬ ስማር ሎተሪ እየሸጥኩ እራሴን ችዬ ኖሬያለሁ። አካል ጉዳተኝነቴ ሳይበግረኝ እራሴን በእራሴ አስተምሬ ለዜህ በመብቃቴ ደስተኛ ነኝ» ትላለች። በቀለመወርቅ ጥሩነህ ትምህርት ቤት ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃትን ውጤት በማምጣቷ በርቺ ለማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ7ሺ500 ብር ድጋፍ በማድረግ ከምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ እጅ ደግሞ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላታል።
በልጅነት ሕይወቷ ሰበታ አይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት የቆየችው ወጣቷ በቀጣይ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የሕግ ትምህርትን ለመከታተል ወጥናለች። ይበል የሚያሰኘው ጥረቷ ግን በዩኒቨርሲቲው እና በተለያዩ ተቋማት ካልተደገፈ አሁንም ሎተሪዋን እያዞረች የመማሯ ጉዳይ እንደማይቀር ነው የምትናገረው። ያም ሆነ ይህ ግን በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ውጤቷ ለእራሷ ኩራት ለአገሯም ተስፋ የሰጠ በመሆኑ በእራሷ ደስተኛ ነች።
ወይዘሮ አባይነሽ ገበየሁ ደግሞ መስማት የተሳነው ወንድ ልጅ አላቸው። ልጃቸው 10ኛ ክፍል መልቀቂያን ጥሩ ውጤት በማምጣቱ በከተማ አስተዳደሩ የሦስት ሺ ብር ድጋፍ ሲደረግለት አብረው ተገኝተዋል። ልጃቸው ያሬድ አሁን 11ኛ ክፍል ነው። በዚህ ደስተኛ ቢሆኑም ባለፉት ጊዜያት ግን ክፍል ውስጥ አካል ጉዳት ከሌለባቸው ተማሪዎች ጋር ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ተቀላ ቅሎ የሚማር በመሆኑ ችግር ውስጥ እንደነበር አይዘነጉትም።
በመሆኑም እርሱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች በአስተርጓሚ ወይንም የምልክት ቋንቋ በሚችል መምህራን ቢማሩ ዕውቀታቸው መሰረት እንደሚይዝ ይገልጻሉ።
አስተርጓሚ ባለመኖሩ ከዚህ ቀደም ልጄ ትምህርት ቤት ውሎ እንጂ ተምሮ አይመጣም የሚሉት ወይዘሮ አባይነሽ እርሳቸው የምልክት ቋንቋ ተምረው ቤት ውስጥ ባይደግፉት እና በእራሱ ጥረት እያነበበ ትምህርቱን ባልከታተል ወድቆ ይቀር እንደነበር ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ወይዘሮዋ እንደ ሚሉት፣ መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች ከትምህርቱ ይልቅ ወደቴክኒኩ ሙያ የሚያዘነብሉ በመሆኑ ትምህርት ቤቶች እና ተቋማት ልዩ ፍላጎታቸውን በመረዳት እንደየችሎታቸው ቢያስተምሯቸው የተሻለ ውጤት ይገኛል። አንዳንዶች ኤሌክትሪካል ሙያ፣ ሌሎች መካኒካል ሲወዱ ሌሎች ደግሞ በስፖርቱ መስክ መሰማራት ፍላጎት አላቸውና ችሎታቸውን ለይቶ ለመደገፍ ትኩረት ያስፈልጋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ደግሞ አካል ጉዳተኞች ፈተናዎችን አልፈው በትምህርታቸው ባመጡት ውጤት ሊኮሩ እንደሚገባ ገልጸው በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው እንደሚቆም ቃል ገብተዋል። ሕይወት በፈተና የተሞላች በመሆኗ ቀጣይ ፈተናዎችንም በማለፍ ስኬት ላይ ለመድረስ መጠንከር እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። ተማሪዎቹ በ10ኛ እና 12 ክፍል የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ላገዙ ቤተሰቦች ልዩ ክብር እንደሚገባ እና በዚህ ደስተኛ ሆነው ለሌሎችም አርአያ እንዲሆኑ አበረታተዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመጡት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላ ቸው፤ ምቹ ሁኔታ ተዘጋጅቶላቸው ዕድላቸውን ሳይጠቀሙ ፈተና ውስጥ የወደቁ ተማሪዎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ አይቻልም የሚለውን አልፈው የጥንካሬ ተምሳሌት መሆን የቻሉ ተሸላሚ ተማሪዎችን ጀግኖች ናችሁ ሲሉ አሞካሽተዋል። ውጤታማ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎቹንም «ምቹ መንገድ ላይ ሳይሆን የተደራረበ መሰናክል ላይ ሮጣችሁ ለዚህ ውጤት በመብቃታችሁ እናንተ ለእራሳችሁ ደስታ ለአገራችሁ ደግሞ ተስፋ ናችሁ» ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በ10ኛ እና በ12 ክፍል ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው ላለፉ አካል ጉዳተኞች በሦስት ደረጃ የተከፋፈለ የገንዝብ ሽልማት አበርክቷል። ከ10 ሺ ብር ጀምሮ እስከ 3ሺ ብር የሚደርስ ሽልማትም ለ79 አካል ጉዳተኞች ያበረከተ ሲሆን በዕለቱም ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የምስክር ወረቀቱን ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
ጌትነት ተስፋማርያም