• አንድ ሆነን ለሰላም ፣ይቅርታና ፍቅር ስንገዛ ሁሉንም ነገር ማሸነፍ እንደምንችል ማሳያም ነው።
አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያሸነፉት የ2019 የኖቬል የሰላም ሽልማት የመላው ኢትዮጵያውያን ሽልማት እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገለፀ።
ሽልማቱን አስመልክቶ የጽ/ቤቱ ፕሬስ ሴክሬታርያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ትናንት ከሰዓት በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሽልማቱ አንድ ሆነን ለሰላም፣ ለይቅርታ እና ፍቅር ስንገዛ ሁሉንም ነገር ማሸነፍ እንደምንችል ማሳያ ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሰላም እጦት መንታ መንገድ ላይ በቆመችበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት መምጣታቸውን ያስታወሱት አቶ ንጉሱ፤ ስራቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ጥላቻ፣ ቁርሾና ቂም በቀልን በማስወገድ ሰላም፣ ፍቅርና ይቅርታ እንዲሰፍን ማቀንቀናቸውን በዚህም ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች በሙሉ መነሻና መድረሻቸውን ሰላም በማድረግ ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ቂም በቀልና ቁርሾዎችን በማስወገድ ኢትዮጵያውያንን አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ መስራታቸውን አቶ ንጉሱ ገልፀዋል።
ተደምረን ሀገራችንን በማበልፀግ መልካም እሴቶች እንዲጎለብቱና አንድነታችን እንዲጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መስራታቸውን የገለፁት አቶ ንጉሱ፤ እስረኞችን በመፍታት፣ የዲሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት፣ በሃይማኖት ተቋማት መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ልዩነት በመፍታት፣ ሰላምን የሚያረጋግጡ ተቋማትን በማዋቀርና በሌሎችም በርካታ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጎረቤቶቻችን ሰላም መጠበቅ ለእኛ የውስጥ ሰላም መረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው ብለው እንደሚያምኑ እና በዚህም በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የተፈጠሩ የሰላም እጦት ችግሮችን ለመፍታት በመንቀሳቀስ በደቡብ ሱዳን ፣ በሶማሊያ፣ ሱዳንና ሌሎችም ሀገራት የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላም እንዲፈቱ ማድረጋቸውን አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።
ለ20 አመታት ያህል ተቋርጦ የነበ ረው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት እንዲስተካከልና ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ወደቀደመ ትስስራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጫወቱት ሚና አንቱ የሚያሰኝ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፤ ሀገራቱ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑንም አንስተዋል።
አቶ ንጉሱ ሽልማቱ ለተሰራው ስራ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለምንሰራቸው ስራዎች መልእክት የተገኘበት ነው ያሉ ሲሆን፤ አንድ ሊያደርጉንና ሊያስማሙን የሚችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንድንሰራ የሚያደርግ እንደሆነም ተናግረዋል።
አቶ ንጉሱ በመግለጫቸው ስለሰላም፣ ፍቅርና አንድነት የለፉ ሁሉ ድካማቸው ፍሬ ማፍራቱን በመግለፅ ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቬል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ትናንት በኖርዌይ ኦስሎ ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
በድልነሳ ምንውየለት