የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሰላም እና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ጥረት በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀው የድንበር የይገባኛል ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ተነሳሽነትን በመውሰዳቸው የ2019 የኖብል የሰላም ተሸላሚ አድርጓቸዋል።
በተጨማሪም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በኢትዮጵያ፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ሰላም እና እርቅ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠትም እንደተመረጡ ኮሚቴው ገልጿል።
ኮሚቴው በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማምጣት ቃል መግባታቸውን በማስታወስ፣ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበል ሀገራቱ አስመራ ላይ የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙ ማስቻላቸውን ነው ያነሳው።
ከኤርትራ እና ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሻክሮ የነበረው የጅቡቲና ኤርትራ ግንኙነት እንዲስተካከል ሚና እንደነበራቸው አስታውሷል።
የኖቤል ኮሚቴው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤርትራ እና ኢትዮጵያ ለረጅም አመታት የነበረው ውጥረት እንዲፈታ ተነሳሽነት ሲወስዱ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ሃሳቡን በበጎ መልኩ ተቀብለዋል ብሏል።
ከዚህ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ በርካታ ለውጦችን በማካሄድ የሀገሪቱ ዜጎች ለተሻለ ህይወት ተስፋ እንዲያደርጉ አድርገዋል ብሏል ኮሚቴው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት በመጡ 100 ቀናት ውስጥ በሀገሪቱ ላይ ተጥሎ የነበረውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስተዋል፣ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ፈተዋል ። በመገናኛ ብዙሃን ላይ የነበረውን ሳንሱር አስቀርተዋል ነው ያለው የኖቤል ኮሚቴው።
እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሴቶች በሀገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን እርከን እና በማህበረ ሰቡ ውስጥ ላቅ ያለ ሚና እንዲኖራቸው ማድረ ጋቸው ተጠቁሟል።
በሀገሪቱ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጠናከር ቃል መግባታቸውን ነው ኮሚቴው ያስታወሰው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012