አዲስአበባ ፡- ባለፈው ዓመት የምዘና ፍተሻ ከተደረገላቸው ሰማንያ ስድስት የውሃ ምርቶች መካከል ስምንት ያህሉ ተገቢውን የውሃ ምዘና መስፈርት ባለማሟላታቸው የብሄራዊ ደረጃዎችን የመጠቀም ፍቃዳቸውን እንደተነጠቁ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ይስማ ጅሩ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የውሃ ምርቶቹ የመጠቀሚያ ፈቃዳቸውን ለመነጠቅ የቻሉት በየሶስት ወሩና በድንገት በተደረጉ የፍተሻ ሂደቶች ነው።
እንደዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በዚህ የፍተሻ ሂደት ከተቀመጠው ደረጃ በታች የሆኑ የውሃ ምርቶች ያጋጠሙ ሲሆን፤ ከእነዚህ በተጨማሪም የውሃ ምርት ፈቃድ አውጥተው ስራ ከጀመሩ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ያቋረጡና በዚሁ ምክንያትም ፈቃዳቸው የተወሰደባቸው አምራቾች ይገኙበታል።
በየጊዜው በሚደረጉ ፍተሻዎች ከሚጠበ ቀው ደረጃ በታች ሆነው የሚገኙ ምርቶች እንደሚኖሩ የጠቀሱት አቶ ይስማ፤ ይህ አይነቱ ሁኔታ ሲፈጠርም ምርቶቹ ከገበያ ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ኤጀንሲው ይህን መሰሉን ድርጊት ለመከላ ከል ለሚመለከታቸው አካላት ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሲሆን በየዘርፉ ያሉ ተቋማትም የምርት ጥራቱን በመቆጣጠር ተገቢውን ክትትል እንደሚያደርጉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
አምራቾቹ ደረጃውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማስቻል ኤጀንሲው የቴክኒክ እገዛ የሚሰጥ ሲሆን፤ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀ ትም የምርት ጥራቱ እንዲጠበቅ ጥናት የማድረግ ድጋፍ እንደሚያካሂድ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም የምርት አይነቶቹ የሚመዘኑት በማሸግ፣በማጓጓዝና በማከማቸት ሂደት የተቀመጡትን መስፈርቶች አሟልተው ሲገኙ መሆኑን ገልጸው፤ በኤጀንሲው የምዘና ፍተሻ የሚደረግላቸው የቧንቧ፣ የታሸጉና ሌሎች የማዕድን ውሃዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው አመት የምዘና ፍተሻውን ካለፉ ሰባ ስምንት የታሸጉ የውሃ ምርቶች መካከል አስሩ የማዕድን ውሃዎች መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ይስማ፤ ምርቶቹ ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅት የምስክር ወረቀት በመውሰድ ከኤጀን ሲው ብሄራዊ የደረጃዎች ምልክትን የመጠቀም ፈቃድ አግኝተው ገበያ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
መልካምስራ አፈወርቅ