ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታንና የውሃ አሞላልን አስመልክቶ ለአራት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ውይይት ምንም ውጤት አላመጣም በማለት የግብፅ መገናኛ ብዙሃን በርካታ አፍራሽ ዘገባዎችን እየሠሩ ይገኛሉ።
መስከረም 28 ቀን 2012 ደግሞ የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሹኩሪ ለአገሬው ፓርላማ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ላይ የያዘችውን አቋም ክፉኛ ተችተዋል።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች መስከረም 2012 ዓ.ም ሱዳን ላይ በህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ላይ የተደረገውን የሦስትዮሽ ምክክር፤ በግብፅ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለፅ የሦስተኛ ወገን አደራዳሪዎች ጣልቃ እንዲገቡ ፍላጎት እንዳላት ጠቁማለች።
ኢትዮዮጵያ እና ሱዳን ደግሞ ሃሳቡን ተቃውመውታል። በፈረንጆቹ አቆጣጠር በመጋቢት 2017 ተደርጎ የበረውን የሦስትዮሽ ስምምነትም እንደሚፃረር በመግለፅ። ለመሆኑ ግብጽ በተለያዩ ወቅቶች ተለዋዋጭ አቋሞችን እንድትይዝና ከድርድሩ እንድታፈነግጥ ያደረጋት ምን ይሆን?
ግብጽ አቋሟን በየጊዜው የምትቀያይርበት ምክንያት በእርግጠኝነት ይህ ነው ብሎ መናገር ያስቸግራል የሚሉት በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ውሃዎች ጉዳይ አማካሪና የሦስትዮሽ ብሄራዊ ኮሚቴ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ተፈራ በየነ ናቸው።
ግን ዋነኛው ማጠንጠኛው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመርም ሆነ መጠናቀቅ ለግብፆች ራስ ምታት ሆኖባቸዋል። በተቻላቸው አጋጣሚ ሁሉ ፍትህን እየሸሹ ለማደናቀፍ መሞከር ሥራቸው አድርገውታል። በአሁኑ ወቅትም እያደረጉት ያለው መወራጨት ከዚህ የዘለለ ትርጉም እንደማይኖረውና ኢትዮጵያን ከሥራዋ የሚያደናቅፋት አለመሆኑን ያብራራሉ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው፤ ግብጽ ግድቡ ከተመጀረ ጊዜ አንስቶ በርካታ ህፀፆችን እየመዘዘች ስትከራከር መቆየቷን ያስታውሳሉ። ይህ እየሆነ ያለው ግን ያለአንዳች ምክንያት አይደለም ባይ ናቸው።
እንደ ኢንጅነሩ ሃሳብ፤ ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት የኖረ የበላይ ተጠቃሚ ሆና ያለማንም ተቀናቃኝ መቆየት ትፈልጋለች። አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያም ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማንገስ ብትሠራም አይዋጥላቸውም። ለዘመናት የቆየው የበላይነትን አስጠብቆ ለማቆየት ከማሰብ ውጪ አንድም ትርጉም የሚሰጠው አይደለም። ይህ በመሆኑ ተለዋዋጭ አቋም መያዛቸው አይቀሬ እንደሆነ ይጠቁማሉ። የሆነው ሆኖ ግድቡ የሲቪል ሥራ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ፍፃሜውን ያገኛል ሲሉ ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኃይድሮ ፖለቲክስ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ እንደሚሉት፤ የግብፅ አቋም መለዋወጥ አዲስ ነገር ነውን? ሲሉ ይጠይቃሉ። የግድቡ ግንባታ ከተጠነሰሰበት ጊዜ ጀምሮ ግብፆች ሲቃወሙና እና ሂደቶች እንዲጨናገፉ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅም ቀድሞ የያዙትን አቋም በጠነከረ መንገድ ለማስቀጠል የመከጀል ካልሆነ የተለየ ሃሳብ የላቸውም። ቀደም ባሉት ዓመታትም በርካታ የገንዘብ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ አካላት ለኢትዮጵያ ብድር እንዳይሰጡ ሲያከላክሉም ነበር። በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳይገነባ ለዘመናት የራሳቸውን ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፤ አሁንም ቢሆን ተቃውሟቸውን መቀጠላቸው አይቀሬ ነው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 68 ከመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በ2013 ዓ.ም ሁለት ተርባይኖች ኃይል ያመነጫሉ። እስካሁንም ለግድቡ 99 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን፤ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ 40 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል። በርካታ አገራት መሰል ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ከዓለም ትልልቅ የገንዘብ ምንጮች ብድር የሚያገኙ ቢሆንም ግብፅ ባደረገችው ጉትጎታ በዓለም ላይ ያሉ ተቋማት ለኢትዮጵያ ጀርባቸውን ሰጥተዋል።
ታዲያ ምሁራኑ በግብፅ አቋም መቀያየር እና የተለያዩ አማራጮችን ለመመልከት ማማተሩ ለዘመናት አብሯቸው የቆየ አሰራር በመሆኑና ብዙም የማይደንቅ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ እየገነባች ብቻ ሳይሆን በዓለም አደባባይ ፍትህ እንዲነግስ እየሠራች ያለች አገር ናት። የአባይ ውሃም ለትብብር እንጂ ለፀብ ምንጭ አይሆንም፤ ሊሆንም አይገባም ባይ ናቸው።
ሆኖም ግብፆች ትንንሽ ቀዳዳዎችን ባገኙ ቁጥር አጋጣሚውን ለራሳቸው ጥቅም ማዋል ይፈልጋሉ። በተለይም ውስጣዊ ድክመቶች ተከስተዋል ብለው ባሰቡ ወቅት ጣልቃ የመግባት ፍላጎታቸው የላቀ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ለውስጣዊ ችግሮቿ እልባት እያበጀች በግድቡ ግንባታ ላይ የያዘችውን ፍትሃዊና ጠንካራ አቋም ልትቀጥል ይገባል የሚል አቋም አላቸው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር