• 11 ረቂቅ አዋጆችን ለቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል
አዲስ አበባ፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ በፓርላማው መክፈቻ ላይ ባቀረቡት የ2012 የመንግሥት ዕቅድ ላይ የድጋፍ ሞሽን ለመስጠት በይደር አስተላልፎታል፡፡የቀረቡለትን 11 ረቂቅ አዋጆች ለሚመለከታቸው አካላት ለእይታ መርቷል።
የተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት የጋራ ስብሰባ ባቀረቡት የበጀት ዓመቱ ዕቅድ ባቀረቡት ዕቅድ ላይ ውይይት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቡትን የመንግሥታቸው አቋም በማዳመጥ የድጋፍ ሞሽን የሚካሄድበትን ጊዜ በቀጣይ የሚገለጽ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ምክር ቤቱ በተጨማሪም፤ በሰዎች መነገድንና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመቆጣጠር፤ የፌዴራል ማረሚያ ቤትን አዋጅ ለማሻሻል፤ የአነስተኛ ፋይናንስ ሥራ አዋጅን ለማሻሻል የሚሉ፤ እንዲሁም ሌሎች የብድር ስምምነቶችን ለማጽደቅ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን ወደ ሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ለእይታ መርቷል፡፡
የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 26 ቀን ያደረጉት ንግግር የፌዴራል መንግሥት በ2012 ዓ.ም ሊያከናውናቸው ያቀዳቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ያካተተ ነው፡፡ምክር ቤቱ ዕቅዱን የሚቀበለው መሆኑን ለማሳወቅ የድጋፍ ሞሽን እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በፕሬዚዳንቷ ንግግር ዙሪያ ውይይት በማድረግና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቡትን የመንግሥታቸው አቋም በማዳመጥ የድጋፍ ሞሽኑ የሚጸድቅበት ጊዜ በቀጣይ የሚገለጽ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሰዎች የመነገድ ወንጀል በሰው ልጅ ላይ ከሚፈጸሙ አስከፊ ወንጀሎች አንዱ መሆኑን የገለጹት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ በሰዎች የመነገድን፤ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገርንና ሕገ ወጥ የውጭ አገር የሥራ ስምሪትን ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር ረቂቅ ሕጉ መዘጋጅቱን አብራርተዋል፡፡
ወንጀሎቹን በመከላከልና በመቆጣጠርም ዜጎች በተፈጥሮና በሕግ ያገኟቸውን መብትና ነፃነቶች መጠበቅና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለሕግ በማቅረብ ተገቢና አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ የሕጉ ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፌዴራል ማረሚያ ቤትን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተም የታራሚዎችን የሰብዓዊ መብት ክብር ከሚያዋርድና አድሏዊ ከሆነ አያያዝ ለመጠበቅና ሲፈጸም የነበረውን አካላዊና ሥነ ልቦናዊ የመብት ጥሰት ለመከላከል መሆኑን አምባሳደር መስፍን ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ በትናንት ውሎው የተለያዩ 11 ረቂቅ አዋጆችን አይቶ ለዝርዝር ዕይታ ወደ ሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡አባላቱም በፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ ላይ «የጊዜ ቀጠሮ እስረኞች ለምን ያህል ጊዜ በቀጠሮ መቆየት እንዳለባቸው በረቂቁ አዋጁ ቢካተት፤ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ትኩረት ቢሰጠው» የሚሉ አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው የ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባው የምክር ቤቱን 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ቃለ ጉባኤ መርምሮ አፅድቋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2012
ጌትነት ምህረቴ