«የልማት ድርጅቶች በራሳቸው ውል የመግባት ስልጣን አላቸው» የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ
አዲስ አበባ፡- የመንግስት ተቋማት በግዥና ሽያጭ ወቅት የውል አስተዳደር ህግና አሰራርን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ። የመንግስት የልማት ድርጅቶች በራሳቸው ውል የመግባት ስልጣን እንዳላቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ገልጿል፡፡
በጠቅላይ አቃቤ ህግ የፍትሀብሄር የፍትህ አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ ተስፋዬ፤ የመንግስት ተቋማት ውል ሲገቡና ሲያስተዳድሩ የተቀመጠውን ህግና አሰራር ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዳላደረጉ፤ በዚህም በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ሄኖክ ገለፃ፤ የባለ በጀት መስሪያ ቤቶች በተለይም የመንግስት የልማት ተቋማት የሚያደርጓቸውን ትላልቅ የውል ረቂቆች ለጠቅላይ አቃቤ ህግ አያቀርቡም።
የተቋማቱ የስራ ክፍሎች ተቀናጅተው አይሰሩም። የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ተቋማት ከልማት ድርጅቶች ሪፖርት ከመቀበል ባለፈ አይቆጣጠሩም። ይህን ለመወጣት የሚያስችል የህግ ክፍልም የላቸውም።
በሌላ በኩል “እኛ እናግዛችሁ” ስንል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምን አገባው እንደሚሉ የሚናገሩት አቶ ሄኖክ፤ ባደረግነው የዳሰሳ ጥናት ተቋማት በሚያደርጓቸው ዓለም አቀፍ ውሎች በድርድሩ መሳተፍ የሚገባቸው ባለሙያዎች እንደማይሳተፉ ጠቁመዋል። የኮንትራት አስተዳደር፣ የህግና የግዥ ክፍሎችም በድርድሩ እንደማይሳተፉና በአንድ ኃላፊ ድርድር ተደርጎ ኮንትራት እንደሚገባ ገልፀው፤ ለድርድር የሚበቃ የቋንቋ ችሎታ የሌላቸው ሰዎች እንደሚሳተፉና በዚህ የተነሳ ምክንያታዊ ያልሆኑ ውሎች እንደሚፈፀሙ አብራርተዋል።
ከዚህ በፊት የተደረጉ ውሎችን ቁጥር ብቻ በመጠቀም ውል መግባት፣ ድርድር ያደረጉባቸውን ጉዳዮች አጠቃለው በውሉ አለማስገባት፣ ውል ሲገቡ ይዘው የሚመጡትን ችግር አለመገንዘብ፣ የዳኝነት ስርዓትና የህግ መረጣ ችግር፣ ውል የሚያስፈጽሙበትን መንገድ ለይተው አለማስቀመጥ፣ ከአቅም በላይ የሆኑ ነገሮች በውል ውስጥ ማካተት እና የውል ማቋረጫ ምክንያቶችን ለይቶ አለማስቀመጥ በውል ስምምነቱ እንደሚታይም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ተቋማት በሚያደርጉት የውል ስምምነት መሰረት እንደማያስተዳድሩና ውል ፈጽመው ኃላፊነታቸውን እንደማይወጡም ጠቅሰዋል። በዚህ የተነሳም “ባልተወጡት ኃላፊነት ተዋዋዩን ተጠያቂ ያደርጋሉ፣ ጊዜው ያለፈበት ውል ያለማሻሻያ እስከ ስምንት ዓመት ያቆያሉ፣ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ የሚያማክሩትም ችግሩ ሲብስ ነው” ብለዋል።
“የመንግስት ተቋማት ኪሰራ ደርሶባቸዋል፣ ጥራት ያለው እቃ አይገዛም፣ እቃው በወቅቱ ባለመገዛቱ ህብረተሰቡ አገልግሎቱን እንዳያገኝ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሯል” ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ለዩኒቨርሲቲዎች የሚገዙ የቤተ ሙከራ መሳሪያዎች ከጥራት በታች መሆናቸውንም እንደምሳሌ ያነሳሉ።
የሚፈለገውን የተማረ የሰው ሀይል ማፍራት እንዳልተቻለ፣ የመንግስት ግንባታዎች በአንድና በሁለት ዓመት መፍረስ የሚጀምሩበት ሁኔታ መፈጠሩን፤ የሚገጠሙት እቃዎችም ከጥራት በታች መሆናቸውን አንስተዋል።
የሚገዙ ኬሚካሎችም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው የተቃረበ፣ ለግብርና የሚገዙት ግብዓትም ችግር ያለባቸው፣ ለመንገድና ለኤሌክትሪክ ስራ የሚገዙ እቃዎች ከጥራታቸው በታች መሆን፣ ወዘተ… ችግሮች በመኖራቸው በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አንስተዋል። ጉዳቱ ከተለካም አስደንጋጭ ስለሆነ መንግስት ግልጽ አቅጣጫ ይዞ ማስተካከል አለበት ሲሉ ምክትል ዳይሬክተሩ አስጠንቅቀዋል።
እርሳቸው እንደገለጹት ችግሩን ለመፍታት በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግን ጨምሮ ሁሉም ተቋማት የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማስቻል፣ ዘርፉን በሙያ መምራት፣ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ፣ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት እንዲሁም ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራርን መዘርጋት እንደሚገባም ምክረ ሃሳብ ሰንዝረዋል።
የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የህግ ዳይሬክተር አቶ ተስፋ ቶላ በበኩላቸው፤ የልማት ድርጅቶች ዓላማቸውን ለማስፈጸም በራሳቸው ውል የመግባት ስልጣን እንዳላቸው ጠቁመው፤ ኤጀንሲው እያንዳንዱን ውላቸውን ጣልቃ በመግባት እንደማይቆጣጠር፤ ነገር ግን ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ እንደሚያግዙና የአቅም ግንባታ ስራ እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል፡፡
የባለበጀት መስሪያ ቤቶችን ግዥ የሚያከናውነው የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢቴሳ ደሜ በበኩላቸው፤ “ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሚያደርጋቸው ውሎች ጣልቃ ባይገባም ከህግ ረቂቅ እስከ አፈፃፀም ድረስ እንደ አንድ ተቋም በጋራ እየሰራን ነው፤ በስራዎቻችንም እስካሁን የገጠመን ችግር የለም” ብለዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ