አዲስ አበባ፦ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተለያዩ መስፈርቶችን ሳያሟሉ ተምረው ያስመረቋቸውና በመማር ላይ ያሉ ተማሪዎችን በተመለከተ መንግስት ውሳኔ እንዲሰጥበት ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረቡን አስታወቀ።
በኤጀንሲ የዕውቅና አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ አብይ ደባይ፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተለያዩ መስፈርቶችን ሳያሟሉ አስተምረው ያስመረቋቸውና በማስተማር ላይ የሚገኙት ተማሪዎች ቁጥር በርካታ ነው።
የተማሪዎችን መረጃ ለመደበቅ ሁለት ሬጅስትራር ያሏቸው፤ ግብር እንዳይከፍሉ የተለያዩ መረጃዎችን የሚያቀርቡ ተቋማት እንዳሉ ተገንዝበናል። ተቋማቱ አስተምረው ያስመረቋቸውና ተጠያቂነትን በመሸሽ ለኤጀንሲው ያላቀረ ቧቸው ሊኖሩ ስለሚችሉ ችግሩ የሰፋና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚዊና ማህበራዊ በመሆኑ ከፍተኛ አመራሩ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ቀርቧል::
ዳይሬክተሩ ‹‹በአዲስ አበባና በዙሪያው በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በርካታ ተቋማት እውቅና ሳይሰጣቸው በመደበኛና በርቀት መርሃ ግብር ትምህርት የተሰጡ ተማሪዎች አሉ። እንዲያስተምሩ ከተፈቀዳላቸው ቁጥር በላይ አስተምረው ያስመረቁ፤ መንግስት ያወጣውን የመግቢያ መስፈርት ሳያሟሉ የተማሩና በመማር ላይ ያሉ ፤ በአግባቡ ትምህርት ሳይከታተሉ የተመረቁና ለትምህርት ባልተሰጠ ንግድ ፍቃድ ትምህርት አስተምረው ያስመረቁና በማስተማር ላይ ያሉ ተገኝተዋል›› ብለዋል።
ኤጀንሲው በአዋጅ ቁጥር 261/2004 ዓ.ም ለግል የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ለሚሰጡት ትምህርት ቤት መጽሐፍት፣ የመማሪያ ክፍል፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የቤተ ሙከራና የማሳያ፣ ጥራት ያለው የአሰራር ስርዓት፣ ችሎታ ባላቸው መምህራን፣ የተሟላ አደረጃጀትን፣ የማስተማሪያ ከባቢያዊ ሁኔታን፣ የጥራት ማስጠበቂያን፣ የጥናትና ምርምርን፣ የማህበረሰብ አገልግሎትን፣ የተማሪዎችን ልዩ አገልግሎቶችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ሙሉ ለሙሉ ባልተሟላ ሁኔታ ማስተማራቸውን አመላክተዋል።
ዳይሬክተሩ ‹‹የግል ተቋማቱ እውቅናቸው በአቅማቸው በተፈቀደላቸው የተማሪ ቁጥር ልክ፣ በተፈቀደላቸው ቦታ፣ የትምህርት መስክ፣ ደረጃ፣ የትምህርት አሰጣጥና የጊዜ ገደብን በመተላለፍም የተማሩ ዜጎች አሉ። መስፈርቱን ሳያሟሉ ተመርቀው ወደ ስራ የገቡ፣ ሌላ ትምህርት በመቀጠል የተማሩ ። በመንግስት ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በማንሳት የችግሩ ግዝፈት ከጠበቅነው በላይ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹ለጉዳዩ ተጠያቂ የሚሆኑት የትምህርት ተቋምት ብቻ ሳይሆኑ ተማሪዎች፣ ኤጀንሲውንና መንግስትም ጭምር ነው›› ያሉት አቶ አብይ፤ ‹‹ችግሩም ውስብስብና ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የመጣ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ግብታዊ ሆኖ እርምጃ መውሰድ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊና በማህበራዊ ዘርፍ የሚደርስ ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት በጥንቃቄ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት።
ከዚህ በኋላ እንዳይደገም መስራት እንደተጠበቀ ሆኖ ያለፈው ችግር ታይቶ እንዲፈታ መወሰን አለበት። በፖለቲካና በተለያየ ችግር ምክንያት ሥራቸው ካልተሳካላቸው ተቋማት ውስጥ ኤጄንሲያችን አንዱ ነው። ኤጀንሲውን ካለበት ችግር ለማውጣት የተለያዩ ስራዎችንም እያከናወንን ነው›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ