አዲስ አበባ፡- የቅማንት የማንነትና የራስ ማስተዳደር ጥያቄ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ባከበረ መንገድ መመለሱ ተገለጸ፡፡ የተነሱት ግጭቶች በሶስት ቀበሌ ማስተዳደር ጥያቄ ላይ ተመርኩዞ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የቅማንት የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄን በተመለከተ ትናንት በተካሄደ ውይይት የአማራ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (አዴፓ) ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ንጉሡ ጥላሁን ፤ የአማራ ክልል የቅማንትን ጥያቄ በህጋዊና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ባከበረ መልኩ መመለሱን ተናግረው፤ ችግሮች የተነሱት በሶስቱ ቀበሌዎች ምክንያት ቢሆንም ግጭት እየተከሰተ ያለው ሌሎች የማይመለከታቸው ቦታዎች ላይ እንደሆነ፤ በአንዳንድ መገናኛ ብዙሀንና የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በሚሞክሩ ሀይሎች ግጭቱ እየተባባሰ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
አቶ ንጉሡ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህዝቦች ማንነት ተከብሮና ውክልና አግኝተው እንዲኖሩ በርካታ ስራዎች እንደተከናወኑ፤ ለአብነትም የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞንና የአርጎባ ልዩ ወረዳን በማንሳት የቅማንት ጥያቄ በአግባቡ ስለተመለሰ ወደ ግጭት የሚያስገባ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የህግ አማካሪ አቶ መርሃፅድቅ መኮንን፤ የቅማንት የማንነትና የራስ ማስተዳደር ጥያቄን ለመመለስ የዳሰሳ ጥናት እንደተካሄደና ጥያቄው ህገመንግስቱ ላይ የተዘረዘሩትን የጋራ ቋንቋ፣ ኩታ ገጠም ቀበሌዎች ብዛት እንዲሁም የጋራ ማንነት ላይ ማመን የሚሉትን መስፈርቶች ባያሟላም እንኳ የተነሳውን ጥያቄ ለመመለስ ካለው ፍላጎት አኳያ ጉዳዩ በፖለቲካዊ ውሳኔ እልባት እንዲያገኝ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
2007 ዓ.ም ላይ ለቅማንት ኩታ ገጠም ናቸው የተባሉ 42 ቀበሌዎች ተመርጠው ልዩ ወረዳ እንዲሆን በአዋጅ መፅደቁን ያስረዱት አቶ መርሃፅድቅ ፤ ኮሚቴው የተሰጡኝ ቀበሌዎች አንሰውኛል በሚል ጥያቄ በማንሳቱ 2010 ዓ.ም ላይ 69 ቀበሌዎችን ይዞ የቅማንት ብሄረሰብ አስተዳደር እንዲባል ምክር ቤቱ በአዋጅ ማፅደቁን አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ መርሃ ፅድቅ ገለፃ፤ ኮሚቴው በድጋሚ 12 ቀበሌዎች ይገቡኛል በማለቱ ህዝበ ውሳኔ ተደርጓል:: በህዝበ ውሳኔው አራቱ ቀበሌዎች በነባር አስተዳደር እንቆያለን በማለታቸው በስምንቱ ቀበሌ ላይ ብቻ ህዝበ ውሳኔ ተካሂዶ በውሳኔው አንድ ቀበሌ ብቻ ወደ ቅማንት ለመጠቃለል ድምፅ ሰጥቷል፡፡ የአማራ ክልል የቅማንትን ጥያቄ ለመመለስ ህጋዊ መንገድ ተጉዟል፡፡ ነገር ግን ኮሚቴው መቃ፣ ጉባኤ ጀጀቢት እና ሌንጫ የሚባሉ ቀበሌዎች በቅማንት ብሄረሰብ አስተዳደር ስር መሆን አለባቸው በሚል ምክንያት ግጭቶች ተቀስቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜግነት ማህበራዊ ፓርቲ(ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው፤ የቅማንት ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በውይይት ሊፈታ እንደሚገባ ገልጸው፤ በጉዳዩ ዙሪያ የአማራና የቅማንት ማህበረሰቦች ሰፊ ውይይት እንዲያደርጉ ፤ አንዳንድ መገናኛ ብዙሀንም የሚያስተላልፉትን ፕሮፓጋንዳ እንዲያቆሙ አሳስበዋል፡፡
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ‹‹ የቅማንት ጉዳይ ከመስፈርት ይልቅ በፖለቲካ ውሳኔ እልባት ለመስጠት በመሞከሩ ችግሮች ተከስተዋል:: የተፈጠሩትን ስህተቶች በሰከነ ውይይት እንጂ በሀይል ለማስተካከል መሞከር አያስፈልግም፡፡ አንዳንድ መገናኛ ብዙሀን በጉዳዩ ላይ አግባብ ካልሆነ ዘገባ መቆጠብ አለባቸው›› ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
መርድ ክፍሉ