ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ስኬታማ እንዲሆን ክልሎች የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የገንዘብ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ትናንት ሲካሄድ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ እንዳሉት፤ ክልሎች በምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ሚና ስላላቸው ያላቸውን የተፈጥሮና የሰው ሀብት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በማቀናጀት ማሻሻያውን በሃሳብ በማዳበርና ተግባራዊ በማድረግ ኢኮኖሚውን ማሳደግና አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር እቅድን ማሳካት ይጠበቅባቸዋል፡፡
እንደሚኒስትሩ ገለፃ፣ ክልሎች በኢኮኖሚው ውስጥ ያሉትን ችግሮች በቅርበትና በዝርዝር የሚያውቋቸው በመሆኑ፣ ሊተገበር የተዘጋጀው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ምን ዓይነት ግብዓቶች እንደሚያስፈልጉት ለማወቅ ይረዳቸዋል፤ ይህ ደግሞ ለመርሃ ግብሩ ስኬት የራሱ የሆነ አወንታዊ ሚና ይኖረዋል፡፡
አቶ አህመድ እንዳሉት፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ዋና ዓላማ የማክሮ ኢኮኖሚውን መዛባት በማስተካከል መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ማምጣትና የመንግሥትን አገልግሎት ቀልጣፋ በማድረግ የምርታማነት ማነቆዎችን መፍታት ነው፡ ፡ በመሆኑም እስካሁን በተመዘገቡ ስኬቶች ላይ በመንተራስ ያጋጠሙ ችግሮችን በማረምና በመደመር መርህ ፈርጀ ብዙ እድገት በማስመዝገብ የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ምስረታን ማፋጠንና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ወደ ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት ይገባል፡፡
‹‹መርሃ ግብሩ በኢኮኖሚው ውስጥ ያሉ የሥራ፣ የገበያና የሥርዓት ጉድለቶችን በማረም አገሪቱ ያላትን የሕዝብ ብዛት፣ የተፈጥሮ ሀብትና ቀጣናዊ የስትራቴጂ አቅም በመጠቀም በኢኮኖሚው ላይ ወሳኝ ሚና የመጫወት ዓላማ ያለው ነው›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ ባለፉት 15 ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች የመንግሥትን የማስፈፀም አቅም ለማሳደግ በተደረጉ ጥረቶች የተገኙ መልካም ውጤቶችን እንደትልቅ ሀብት በመጠቀም ኢኮኖሚን በማሳደግና ምርታማነትን በማሻሻል ላይ ያተኮረ በመሆኑ ክልሎችም ይህንኑ አቅጣጫ መሰረት በማድረግ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መርሃ ግብሩ ከተለመዱት ዘርፎች በተጨማሪ ሌሎች አማራጭ የኢኮኖሚ ዘርፎችን የእድገት ምንጭ አድርጎ ለመጠቀም የሚያስችል በመሆኑ ክልሎችም ያላቸውን አቅም በመጠቀም ለመርሃ ግብሩ ስኬት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
አንተነህ ቸሬ