.የግብጽ አካሄድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጻረር ነው ተባለ
አዲስ አበባ፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ 40 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገለፀ፡፡ በግድቡ የውሃ አሞላል ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮች ላይ ግብፅ የምታቀርባቸው ሃሳቦች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚፃረሩ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ትናንት በፍሬንድሺፕ ሆቴል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ባካሄደበት ወቅት የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ፤ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ 99 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉንና ሥራውን ለማጠናቀቅ 40 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
ኢንጅነር ክፍሌ ‹‹ በአሁኑ ወቅት መንግስት በወሰዳቸው እርምጃዎች በርካታ ህፀፆች ተስተካክለዋል፡፡ በተለይም ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ተቋራጮች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉ ትልቅ ውሳኔ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ 68 ከመቶ በላይ ደርሷል፤ በ2013 ዓ.ም ሁለት ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይችላሉ ›› ብለዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክርቤት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በበኩላቸው፤ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ህዝባዊ ተሳትፎው ጠንካራ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ግድቡ ሲጀመር ለግንባታ 80 ቢሊዮን ብር እንደሚበቃ የተገመተ ሲሆን፤ ህዝቡ ከ15 እስከ 20 ከመቶ ያለውን ይሸፍናል ተብሎ እቅድ መውጣቱን አስታውሰዋል፡፡ በዚህም መሠረት እስካሁን ከህዝቡ 12ነጥብ9 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ወይዘሮ ሮማን ጠቁመዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ ፤ በ2012 በጀት ዓመት ከፍተኛ ህዝባዊ ንቅናቄዎችና ተሳትፎዎችን በማድረግ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የመሰብሰብ ውጥን መኖሩን ጠቅሰው፤ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አውታሮችና ቋንቋዎች ሰፊ የቅስቀሳ ሥራ እንደሚካሄድ፣ የላቀ የህዝብ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግና የመገኛኛ ብዙሃን አውታሮችም ግንዛቤ በመፍጠር ትክክለኛውን ገጽታ በማስተዋወቅ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ውሃዎች ጉዳይ አማካሪና የሦስትዮሽ ብሄራዊ ኮሚቴ ቡድን መሪ አቶ ተፈራ በየነ በበኩላቸው፤ ግብጽ በግድቡ የውሃ አሞላል ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮች ላይ የምታቀርባቸው ሃሳቦች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚነኩና ሉዓላዊነትን የሚፃረሩ ቢሆንም ፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህጎችንና ፍትሃዊ አካሄዶችን በመከተል ሥራዋን እያከናወነች መሆኑን በመጠቆም ይህንኑ መርህ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር