. ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ የቤት እጣ መውረስ አይችሉም የሚለው ተሻሽሏል
አዲስ አበባ ፦ በስራ ላይ ያለው የፌዴራል ጥቅል ዓላማ ያለው ድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ተግባር ላይ የሚውልበት ጊዜ እስከ 2014 ዓ.ም እንዲራዘምና ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው አዲሱ የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ዝግጅት ከተያዘው በጀት ዓመት አንስቶ እንዲጀመር የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ወሰነ፡፡
ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው 5ኛው የፓርላማ ዘመን አምስተኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባው ከተመለከታቸው አጀንዳዎች መካከል በስራ ላይ ያለው የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ተግባር ላይ የሚውልበት ጊዜ በሁለት ዓመት እንዲራዘም የሚል ሲሆን፤ የምክር ቤቱን አባላት በስፋት አከራክሯል፡፡
ለመራዘሙ በምክንያትነት የቀረቡት ጉዳዮች አሳማኝና ተጨባጭ ያልሆኑ፣ ተቀባይነት የሌላቸው፣ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታም ያላገናዘቡ በመሆኑ የውሳኔ ሃሳብ ሊታለፍ ይገባል የሚል አቋም ይዘው ተከራክረዋል፡፡
የበጀት ድጎማና የጋራ ገቢዎች ድልድል ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከዚህ በፊት የነበሩት ሁለት ቀመሮች ለአምስት ዓመታት ቢያገለግሉም አሁን በስራ ላይ ያለው ቀመር ግን በ2010 ዓ.ም የሕዝብና ቤት ቆጠራ እንደሚካሄድ በማሰብና ለሶስት ዓመታት ብቻ እንዲያገለግል የተወሰነ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይትም ከህዝብ ብዛት ጋር ተያያዥነት ያላቸውና ለቀመሩ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች አለመጠናታቸውን መረዳታቸውን አብራርተዋል፡፡ ከየክልል የገቢዎች፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊዎች ባለሙያዎች እንዲሁም የበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ጋር በተደረገው ውይይት እንዲሸጋገር ሃሳብ መቅረቡ ተነስቷል፡፡
ዘንድሮ አገራዊ ምርጫ የሚካሄድ በመሆኑም ካለው አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የፌዴራልና የክልል አመራሮችን አግኝቶ ቀመሩን አሳታፊ በሆነ መንገድ ለማዘጋጀት አስቸጋሪ እንደሚሆን ተብራርቷል፡፡
በየአምስት አመቱ የሚደረገው ስሌትና ትግበራ ወደ ሶስት ዓመት እንዲሆን የተወሰነበት ዋና መንስኤ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ በ2011 ዓ.ም ቆጠራው ይካሄድ ስለነበረ ቀመሩ እስከ 2012 ዓ.ም ተሰርቶ ቆጠራው ከተከናወነ በኋላ ሙሉ መረጃ ስለሚገኝ በመረጃው መሰረት ቀመሩ ይሰራል በሚል እሳቤ እንደነበረ ተነስቷል፡፡ ባጋጠመው አገራዊ ሁኔታ ቆጠራው በመራዘሙ እንጂ አዲስ አሰራርና ውሳኔ እንዳልመጣ በቋሚ ኮሚቴ አባላት ተነስቷል፡፡ በመሆኑም እስከ 2014 ዓ.ም ተራዝሞ አዲሱ በ2015 ዓ.ም ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ ተብራርቷል፡፡ በ10 ተቃውሞ በሁለት ድምጸ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ እንዲራዘም የሚለው ጸድቋል፡፡
የህገ መንግስት ትርጉምና ማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ የቀረቡ የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በተባሉና አያስፈልጋቸውም ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ምክር ቤቱ በይግባኝ የቀረቡ አቤቱታዎችን ኮሚቴው በሰጠው ውሳኔ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል፡፡
ትርጉም እንዲሰጥባቸው ከቀረቡት 13 ጉዳዮች መካከልም ስምንቱን በዝርዝር ተመልክቶ፤ በስድስቱ ላይ የህገ መንግስት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በማለት ውሳኔያቸውን አጽንቷል፡፡ በሁለቱ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ አድርጓል፡፡
ማሻሻያ ከተደረገበት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለማስተላለፍ ያወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2008 አንቀጽ 44(ሐ) እና(ሠ) የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት ጉባኤው በአብላጫ ድምጽ አቅርቧል፡፡ በመመሪያው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ የሟች ልጆች እጣውን መውረስ አይችሉም የሚል ሲሆን፤ መመሪያው ከ18 ዓመት በታች እና በላይ የሚል ልዩነት መፈጠሩ ምክንያታዊ አለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በቤት ምዝገባ ወቅት ያልተመዘገቡ የቤት እጣ መውረስ አይችሉም የሚለው አቋም አግባብነት የለውም ተብሏል፡፡ በቤት ፈላጊነት ባይመዘገቡም ቤት የሌላቸው ግለሰቦች በውርስ መልክ ሊያገኙ ከሚችሉት የቤት ባለቤትነት መብት መነፈጋቸው በህገ መንግስቱ የተከበረላቸውን የንብረት ባለቤትነት መብት የሚጣረስ መሆኑ ተቀምጧል፡፡ በሟች ወራሾች መካከል ልዩነት መፍጠር በህገ መንግስት የተሰጣቸውን በህግ እኩል ጥበቃ የማግኘት መብት የሚሸራርፍ እንደሆነም ተቀምጧል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሁን በስራ ላይ ያለው ጥቅል ዓላማ ያለው ድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ያጸደቀው ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ሲሆን፤ ከ2010 እስከ 2012 እንዲያገለግል በማሰብ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
ዘላለም ግዛው