የጃፓኗ ሙኒክ ከተማ የተለያዩ አይነት ቡና ለገበያ በማቅረብ ትታወቃለች፡፡ አብዛኞቹ የአንድ ስኒ ቡና አይነቶቸም ዋጋቸው ከ10 እስከ 20 ዶላር ቢደርስ ነው።
በሙኒክ ኦሳካ ትንሽ የምትገኘው የቡና ቤት ግን ከእነዚህ ትለያለች፡፡ ቡና ቤቷ በዓለም አንድ ስኒ ቡና በውድ ዋጋ የሚሸጥባት ናት፡፡ በዚህ ብቻ አይደለም የምትታወቀው:: ከዓለም 22 ዓመታትን ያስቆጠረ ቡና የሚሸጥባት ብቸኛዋ ቡና ቤት ሳትሆንም የማትቀር በመሆኗም ነው፡፡ አንዱ ስኒ ቡና ምን ያህል የሚሸጥ ይመስላችሁዋል፡፡ አመናችሁም አላመናችሁም 914 ዶላር እንደሚሸጥ የኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ አስነብቧል።
ይህ የዓለም ውዱ አንድ ስኒ ቡና የሚሸጥበት ስፍራ የታወቀው ከአስር ዓመት በፊት ሲሆን፣ የተገኘውም ባጋጣሚ ነው፡፡ ካንጂ ታንካ ደግሞ የቡና ቤቷ ባለቤት ሲሆን፣ ብቸኛው የቡና ቤቷ ሠራተኛም እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡
በአንድ ወቅት በፍሪጅ ውስጥ ለስድስት ወራት ተረስቶ የቆየ ቡና ነው ቡና እንዲህም ሊፈላ ይችላልን ያሰኘው፡፡ ካንጂ ታንካ ይህን ተረስቶ የቆየ ቡና ለደንበኞቹ ሊያቀርብላቸውም ፈልጎ ነበር፤ ቡናውን ሊጥለው አስቦም ነበር፡፡ ኋላ ላይ ግን ከፍለው ለሚጠጡ
ደንበኞቹ ቡናውን ከማቅረብ ይቆጠባል፡፡ ሊጥለው ያስብናም በቅድሚያ ግን ለምን አልቀምሰውም ይላል። ቃናውንም ሲያጣጥም ቡናው ግሩም ሆኖ ያገኘዋል፡፡
ካንጂ ታንካ በእዚህ ግኝቱ ብቻ አላበቃም፡፡ ቡናውን በተመሳሳይ መልኩ ለወራት ፍሪጅ ውስጥ እያስቀመጠ ሲቀምሰውም የቡናው ቃና እያማረ መሄዱን ይገነዘባል፡፡ ከእንጨት የተሠሩ በርሜሎችን ጃፓን ውስጥ እዚህም እዚያም ይመለከታል፡፡ በርሜሎቹ የትኛውንም አይነት አልከሆል የተሻለ ጣእም እንዲኖረው እንደሚያደርጉም ይገነዘባል፡፡ በርሜሎቹን ለእሱ ቡና ሊጠቀምባቸው ያስባል፡፡
ፍሪጅ ውስጥ የቆየውን ቡናውን ያስቀምጥባቸዋል። ለአስር ዓመታትም በበርሜሎቹ ውስጥ እንዲቆዩ ያደርጋል፡፡ ከአስር ዓመታት በኋላም ቡናውን ሲቀምሰው ልክ እንደ ሽሮፕ በጣም የሚገርም ጣእም ይዞም ያገኘዋል፤ ከዚህ በኋላም ታንካ በራሱ መንገድ ለ20 ዓመታት ያቆየውን ቡና እየቆላ እየፈጨ በማፍላት ለገበያ ማቅረብ ይጀምራል፡፡
ቡናው ማፍያ ውስጥ ከተደረገ በሁዋላ ውሃ ቀስ እያለ እንዲገባበት ያደርጋል፤ የመጀመሪያው ውሃ ወደ በርሜሉ የሚገባው በ30 ደቂቃ ውስጥ በጠብታ መልኩ ነው፡፡ ይህን የሚያደርገው ውሃው በአንዴ ቢገባ የቡናው ቃና ሊበላሽ እና ተፈላጊነቱ ሊቀንስ ይችላል ከሚል ሥጋት ነው፡፡ በዚህ አይነት መልኩ የተዘጋጀው ቡና በእንጨት በርሜል ውስጥ እንዲቀመጥ ያደረጋል። ቡናው ለደንበኞች የሚቀርበውም ከዚህ ከእንጨት በርሜል እየተቀዳ ነው፡፡
ይህን ሂደት እና የቡናውን ዋጋ ያስተዋሉ ጋዜጠኞች ቡናው በእርግጥም ቡኒ፣ ጣፋጭ፣ የቸኮላት አይነት መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ቡናውን ከወይን ጋር እስከ ማመሳሰል የደረሱም ነበሩ፡፡ ሌሎች ግን በአድናቆት ብቻ አላቆሙም፡፡ ልታቃጥለው ያስብከው ገንዘብ ካለህ ወይም በቡና የተለከፍክ ካልሆንክ በስተቀር አንድ ስኒ ቡና በ100 ሺ ወይም በ914 ዶላር ለመጠጣት እግርህን ወደ ቡና ቤቷ ማንሳት አይገባህም ሲሉ ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2012
አስናቀ ፀጋዬ
ዘካርያስ