ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቦሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር ‹‹ያልተገባ›› የስልክ ውይይት አድርገዋል መባላቸውን ተከትሎ ከእስከዛሬዎቹ ሁሉ በከፋ መልኩ ውጥረት ውስጥ መግባታቸው በስፋት እየተዘገበ ይገኛል።
ክስተቱም በዲሞክራቶቹና በእርሳቸው አስተዳደር መካከል ከፍተኛ ፍጥጫን በመከሰት መንበረ ስልጣናቸውን ከመነቅነቅ ባሻገር ሊፈነግልቸው እንደሚቸልም አስገምቷል። ፕሬዚዳንቱ በአንድ የስልክ ልውውጥ ፈፅመውታል የተባለው ይህ ስህተትም ለተቀናቃኛቸው ምቹ ዕድል ስለመፍጠሩ እየተነገረ ነው።
‹‹የአገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥልና አስደንጋጭ ነበር›› የተባለውና በሐምሌ ወር የተካሄደው ይህ የስልክ ልውውጥ፣ ፕሬዚዳንቱ በመጪው ምርጫ ተቀናቃኛቸው እንደሚሆኑ የሚጠበቁትን የቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንትና የወቅቱ ዋነኛ ተቀናቃኝ ጆ ባይደንን ጠልፎ ለመጣል ለዩክሬኑ አቻቸው በውለታ መልክ ሲጠይቋቸው እንደሚሰማ ተመላክቷል።
ከካፓኒው ጋር በሙስና ቅሌት ስሙ መነሳቱን ተከትሎ ዩክሬን አባትን ልጅ ላይ ምርመር እንድታካሂድ ጠይቀዋል፣ ተፎካካሪያቸውን ነጥብ ለማስጣል ለጠነሰሱት ለዚህ ዕቅድም ወታደራዊ ድጋፍ በመደራደሪያነት አቅርበዋል ተብሏል።
ትራምፕም ቢሆኑ ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር የጆ ባይደንን ስም አንስተው መወያየታቸውን አልካዱም። ይሁንና ውይይታቸው የአገር ሉአላዊነትን አደጋ ላይ የሚጥል አለመሆኑንና ውንጀላውንም ‹‹ነገር ፍለጋና እርባና ቢስ›› ሲሉ አጣጥለውታል። የስልክ ምልልሱን ሙሉ ቃልም ሳይቀነስና ሳይደለዝ ሙሉውን በይፋ እንደሚያወጡም ቃል ገብተዋል።
ሰውየው በአንድ የስልክ ልውውጥ ፈፅመውታል የተባለው ስህተት ግን ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ለሆኑት ዲሞክራቶች ታላቅ ብስራት ሆኖላቸዋል። ወትሮም ቢሆን ፕሬዚዳንቱን በቀለበት ውስጥ ለማስገባት ሲጠባበቁ እንደመቆታቸውም ፍላጎታቸውን ለማሳካት ምቹ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
በተለይ ‹‹እ.ኤ.አ በ2016 ፕሬዚዳንቱ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ብቃታቸው አብዛኞችን አሳምኖ ሳይሆን የሩሲያን እገዛ ተመርኮዞ ነው› ሲሉ የሚማገቱት ዲሞክራቶቹ፣ የሰሞኑን የስልክ ልውውጥ ካለፈው ምርጫ ጋር በማስተሳሰር የትናንቱ ሴራ ዛሬ እንዳይደገም ጉዳዩን አጥብቀው የያዙት መስለዋል። ፕሬዚዳንቱን ለሁለተኛ ጊዜ ከመመረጥ የሚያስናክላቸውን ጉዱጋድ ቁፋሮ ለመጀመርም ጊዜ አላባከኑም።
የታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ናንሲ ፒሎሲ ‹‹ዶናልድ ትራምፕ አገራቸውን በሀቅ ለማገልገል የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ እምነት የሚጣልባቸው ሰው አይደሉም› ሲሉ ወንጅለዋቸዋል። ፕሬዚዳንቱ በመጭው ምርጫ ውስጥ የውጭ እጅ እንዲገባ ጋብዘዋልም፣ አድራጎታቸው ሕገ መንግሥቱን በብርቱ ይፃረራል፤ የሚል ምርመራ እንዲካሄድባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ይሁንና ለዚህ የዲሞክራቶቹ መሻት እውን መሆን ትራምፕ ከዩክሬን አቻቸው ጋር ‹‹ያልተገባ›› የስልክ ውይይት አድርገዋል የሚለው መረጃ ብቻውን በቂና አሳማኝ አይደለም። ይልቅስ የስልክ ልውውጡ ስለያዛቸው ጭብጦች ተጨባጥ መረጃ ማቅረብ ግድ ይላቸዋል።
ይህን መረጃ ማግኘት ደግሞ ቀላል አይደለም። እ.ኤ.አ በ1961 እንደተሠራ የሚነገርለት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ስልክ የሚደውሉትና እጅግ ሚስጢራዊ ውይይቶች የሚያካሄዱበት ‹‹ሲቺዌሽን ሩም››፣ የሚሰኘው ክፍል ፈቃድ ካላቸው ባለሥልጣናት በስተቀር ማንም ዝር የማይልበት ሚስጥሩም በጣት ከሚቆጠሩ ግለሰቦች የማይወጣ ነው።
ይህ በሆነበት ዶናልድ ትራምፕ ያደረጉት የስልክ ልውውጥ እንዴት ከዚህ ክፍል ሾልኮ ሊወጣ ቻለ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው። በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን የሚገልፁ ግለሰቦች፣ ምናልባትም ከፕሬዚዳንቱ ቅርብ ሰዎች መካከል አንዱ የድምጽ ልውውጡን አሾልኮታል አልያም የነጩ ቤተ መንግሥት ሠራተኞች መረጃ ያቀበሉት ባልደረባ ሳይኖር አይቀርም ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በእርግጥ አሁንም ቢሆን የድምጽ ልውውጥ ይዘትን አሳልፈው የሰጠው ሰው ማንነት እስካሁን አልተገለፀም። ይሁንና የስልክ ልውውጥ አጠናቅሮ ለሚመለከተው አካል እንዲሾልክ ያደረገው አንድ የሲአይኤ መኮንን መሆኑን የሚጠቁሙም በርካቶች ናቸው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖንፒዮም ባልተለመደ መልኩ በዕለቱ በቦታው ነበሩ በሚል የኤን ቢሲ እና ዎል እስትሬት ጆርናል ፀሐፊዎች ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎም፣ ሚኒስትሩም በቦታው እንደነበሩ ምልልሱን እንዳደመጡ አምነዋል። ይዘቱ ምን እንደነበር ተጠይቀው ለመመለስ አለመፈለጋቸውም ጉዳዩን ይበልጥ አነጋጋሪ አድርጎታል።
ይህንና ሌሎች መረጃዎችን ዋቢ ያደረጉት ዲሞክራቶችም ‹ያልተገባ›› በተባለው የስልክ ውይይት ላይ የሚያደርጉትን ምርመራ በፕሬዚዳንቱ ብቻ ሳይወሰኑ በአስተዳደር ሠራተኞጎች ላይ ሳይቀር ለማዝመት ወስነዋል። ይህ ምን ያህል ተቀናቃኛቸውን ዶናልድ ትራምፕን አንገት ለማስጎንበስ እንደቆረጡ ማሳያ እንደሚሆን በርካቶች ተማምነውበታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖንፒዮ በበኩላቸው፣ የዲሞክራቶቹ አካሄድ ፈፅሞ የተሳሳተ መሆኑን በማስገንዘብ፣ እርሳቸው ከሚመሩት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከሚሠሩ ሠራተኞች መካከል ለክስተቱ ቅርብ ነበሩ በሚል ቢያንስ አምስት የሚሆኑ ግለሰቦችን ለማነጋገር ለምርመራ መጠየቃቸውንም በእጅጉ ተቃውመውታል።
ዲሞክራቶቹ ግን ይህን አይነት ተቃውሞ አስፈላጊና አግባብም አለመሆኑን በማስገንዘብ የፕሬዚዳንቱ አስተዳደር ሰዎች ለምርመራው ተባባሪ መሆን ግዴታቸው ሰለመሆኑ፣ ለቃለ መጠይቅ የፈለጉትን ግለሰብ ማግኘት የሚቸገሩ ከሆነ መልስ ለመስጠት አለመፈለጋቸውን እንደ መረጃ እንደሚያቀርቡት አስታውቀዋል። ፕሬዚዳንቱ በአንድ ስልክ ልውውጥ ፈፅመውታል ከተባለው ስህተት ተጠቃሚ ለመሆን የስልክ ልውውጡን መረጃ አሳልፎ ከሚሰጣቸው ሚስጥረኛቸው ጋር በሚስጥር ለመገናኘት ወስነዋል።
ይህ ሚስጥረኛም ከፕሬዚዳንት ትራምፕ እይታ ውጭ መሆኑ የታመነበት ሲሆን እርሳቸውም ቢሆኑ ምስጢራቸውን አሳልፎ የሰጠውና በቀጣዩ ምርጫ ከባድ ራስ ምታት የሚሰጣቸውን መረጃ የያዘው ግለሰብ ማን እንደሆነ ለማወቅ ጓጉተዋል።
የስልክ ውይይታቸው የአገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል አለመሆኑና ውንጀላውንም እርባና ቢስ›› ሲሉ የሚገልፁት ትራምፕ፣ ይህን በመተማመንም ውንጀላው እውነት ከሆነ ‹‹ግለሰቡ ለምን ራሱን በአደባባይ አያሣይም፣ ዝነኛና ታዋቂ አይሆንም› ሲሉ ጠይቀዋል።
አወዛጋቢው መሪ ይልቅስ ‹‹ይህ ሰው ለሰላዮች ቅርብ መሆን አለበት፣ በአገሪቱ ላይ ስለላ የሚያደርግ ነው›፣ ይህ አይነት ተግባር በሞት ሊያስቀጣ ይችላል› ሲሉም መደመጣቸውም በርካቶችን አስደንግጧል። ይህን ተከትሎም የሚስጥረኛው ግለሰብ ጠበቃ አንድሪው ባጋጅ በበኩላቸው፣ የደንበኛዬ ደህንነት አሳስቦኛል ሲሉ ሥጋታቸውን ገልፀዋል።
የኮንግረስ ደህንነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አዳም ሺፍ በበኩላቸው፣ መረጃውን ይፋ የማድረጉ ተግባር በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚፈፀምና ለግለሰቡ ደህንነት ሲባል ቃል የመቀበሉ ሂደት ከመጋረጃው ጀርባ ተፈፃሚ እንደሚሆንም ገልጾአል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ቻይናና ዩክሬን በጆይ ባይደን ላይ ምርመራ እንዲያደርጉ መጠየቃቸው ደግሞ ጎዳዩን አወዛጋቢ አድርጎታል።
የፎክስ ኒውስ ስመጥር የሕግ ጉዳይ ተንታኙ አንድሪው ናፖሊታኖ አጠቃላይ ክስተቱንና ከነጩ ቤተ መንግሥት አካባቢ የሚወጡ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ሌላው ቢቀር ፕሬዚዳንቱ የምርጫ ቅስቀሳ ሕገ ደንብን ባልተከተለ መልኩ ሕገ ወጥ ተግባር በመፈፀም ጥፋተኛ መባል ይኖርባቸዋል›› ብሏል።
የፎክስ ኒውስ መርጥ የሕግ ጉዳይ ተንታኝ እንዳለውም ሆነ ዲሞክራቶች እንደሚያስቡት የስልክ ውይይቱ የአገር ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ሆኖ ከተገኘ ያለምንም ማወላዳት ፕሬዚዳንት ትራምፕን ፍርድ ቤቱ የሚገትራቸው ይሆናል።
በአጠቃላይ አሁን ላይ ‹‹ያልተገባ›› የተባለውን የስልክ ውይይት በሚመለከት በርካታ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎች ከየአቅጣጫው በመቅረብ ላይ ይገኛሉ። ፕሬዚዳንቱ ክስ ሊመሰረትባቸው ይገባል በሚል ምክር ቤቱ መቼ ድምፅ ይሰጥበታል፣ ካፈተለከው መረጃ ጀርባ ያለው ሰው ማነው፣ ፕሬዚዳንቱንስ ከዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ የከተታቸው የስልክ ልውውጥ የተለየ ምስጢር ከሌለው ለምን ይፋ ለማድረግ ዘገዩ የሚሉት ዋነኛ ከሆኑና ያልተመለሱ ጥያቄዎች መካከል ከፊት የተሰነዱ ናቸው።
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2012
ታምራት ተስፋዬ