አዲስ አበባ፡- ሰሞኑን የአዲስ አበባ መስተዳድር በህገወጥ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ በተወሰኑ ምርቶች ላይ መጠነኛ የዋጋ መረጋጋትና ቅናሽ እየታየ መሆኑ ተገለፀ።
የከተማው ነዋሪና የናሆም ምግብ ቤት ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ እቴነሽ ዘለቀ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ሰሞኑን በተወሰነ ደረጃ የዋጋ መረጋጋት እየታየ ይገ ኛል። ከዚህ አንጻር ለምሳሌ የዳቦ ዋጋ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ወደ ነበረበት አንድ ብር ከሰላሳ ሳንቲም የተመለሰ ሲሆን ግራሙም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ሽንኩርት ከነበረበት 35 ብር ወርዶ ከ10 እስከ 18 ብር እየተሸጠ ሲሆን ምስርም የአራት ብር ቅናሽ አሳይቷል።
ፈረንሳይ አካባቢ ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው ሸማቾችም የሰጡን ምላሽ ከዚሁ የራቀ አይደለም። የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳኜ ምትክ እንደነገሩን ከሆነ ወሳኝ የሆኑትና ዳቦን የመሳሰሉት ምርቶች ላይ ከፍተኛ ለውጥና መሻሻል አለ። አትክልት አካባቢም የዋጋ ቅናሾች እየታዩ ነው።
እንደ ወይዘሮ እቴነሽ ገለፃ ከሆነ ሰሞኑን ዋጋቸው ወርዶ የነበሩ ምርቶች በዚህ ሁለትና ሶስት ቀን ውስጥ በመጠኑ ከፍ ቢልም በአብዛኛው ግን እርምጃው ከተወሰደ በኋላ ያለው የገበያ ሁኔታ ጥሩ ለውጥ የታየበት ነው። ድንች በጥሩ ሁኔታ በመውረድ ስድስት ብር ደርሷል። ሆኖም ግን ባለፉት ሁለት ቀናት ወደ 10 ብር ከፍ ብሏል።
ቃሪያ፣ ዘይት፣ ጤፍ እና የመሳሰሉት አትክልትና ፍራፍሬዎችም አካባቢ ያለው ለውጥ የታየበት እንደሆነ የሚገልፁት ወይዘሮ እቴነሽ መንግሥት አሁንም ቀደም ሲል ያደረገውን ገበያን የማረጋጋት ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይናገራሉ።
“አንድ ደረቅ እንጀራ ስምንት ብር ደርሷል” የሚሉት ወይዘሮ እቴነሽ ዘለቀ በተለይ ጤፍ አካባቢ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ
አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ
ቢሮ ምክትል ኃላፊ
አቶ መስፍን አበራ
በቅርቡ ለአዲስ ዘመን
እንደገለፁት፣ በንግዱ ዘርፍ
ያሉትን ችግሮች
ለማስወገድ ህገ-ወጥ ደላላን ለማስቀረት፣ ፍትሀዊ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ህብረተሰቡም ጭምር ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ የሚችለውን ትብብር ሁሉ ሊያደርግና መንግሥትን ሊያግዝ ይገባል። በ8588 ነፃ የስልክ መስመርም ጥቆማዎችን ሊያደርስ ይገባል።
ቀደም ሲል የገበያውን ሁኔታ እየተከታተልን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን የከተማው መስተዳድር የሥራ ኃላፊዎችም የተለያዩ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሚወሰዱት እርምጃዎች መካከል የህገ-ወጥ ደላሎችንና አሰራሮችን መቆጣጠር እንደሚሆን፤ ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር እታች ድረስ ወርዶ እየሰራ እንደሚገኝ መግለፃችን ይታወሳል።
በከፍተኛ ደረጃ ህገ-ወጥ ደላላው የተሰማራባቸውን የእህል፣ አትክልትና ፍራፍሬ እና የቁም እንስሳት የንግድ ዘርፉን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ የገበያ ማእከላትን በየአካባቢው በመገንባት፣ ተደራሽነትን በማጠናከር፤ ሸማችና አምራቹ በቀጥታ የሚገናኙበትን መንገድ ማመቻትና የመሳሰሉት እርምጃዎች የሚወሰዱ መሆናቸውንም የከተማ አስተዳደሩ ገልፆ ነበር።
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2012
ግርማ መንግሥቴ