ተማሪ ኤልሳቤጥ ኃይለማርያም የመስከረም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ናት። ዛሬ ትምህርት ለመጀመር ዝግጁ ናት። ያገኘናትም በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ መጽሐፍ ለመውሰድ እንደመጣች ነው። ተማሪ ኤልሳቤጥ ሁለት ደርዘን ደብተር፣ ስክርቢቶና የደንብ ልብስ ከትምህርት ቤቱ መውሰዷን ነግራናለች። የትምህርት ቁሳቁሶችን መንግሥት ለተማሪዎች ድጋፍ በማድረጉ እሷም ሆነ ቤተሰቦቿ ደስተኞች መሆናቸውን ገልጻለች።እሷና ጓደኞቿ በብሩህ ተስፋና በአማረ ትምህርት ቤት መማራቸው የደስታ ስሜት የሚፈጥርባቸው መሆኑን ገልጻልናለች።
ለትምህርት አስፈላጊ የሚባሉ ቁሳቁሶች ሁሉ ተማሪዎች ስላገኙ አሁን የሚጠበቅብን ትምህርታችንን በአግባቡ መማር ነው የምትለዋ ተማሪ ኤልሳቤጥ በአዲስ መንፈስና በተዋበ ትምህርት ቤት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ትምህርቷን በትጋት ማጥናትና በአግባቡ መከታተል ያስፈልጋል ብላለች።
ተማሪ ቢኒያም ጫላ የሚማርበት ትምህርት ቤት መታደሱ ብሩህ ተስፋ እንደፈነጠቀበት ገልጾ ደብተር፣የደንብ ልብስና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ ስለተደረገልን ከአሁን በኋላ የእኛ ሥራ ትምህርት በትጋት መማር ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። ዛሬ ለሚጀመረው ትምህርትም በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጾ ውጤታማ የትምህርት ዘመን እንዲሆንም ትምህርቱን በትጋት ለመማር መዘጋጀቱን ነግሮናል።
የሶስተኛ ክፍል ተማሪና የሰባተኛ ክፍል ሁለት ልጆቻቸውን በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እያስተማሩ ያሉት የወረዳ 28 ነዋሪ መጋቢ እሸቱ ምትኩ ‹‹ልብስ ሲያረጅ የግድ መቀየር እንዳለበት ሁሉ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት ትምህርት ቤቶችም መታደስ ተገቢ ነው ።መንግሥት በራሱ ወጪና ተባባሪ ድርጅቶችን በማስተባበር ትምህርት ቤቶችን የማደስ ሥራ የሚያስደስትና ተማሪዎች በማራኪ ክፍሎች እንዲማሩ የሚያደርግ ነው›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
ወላጆች ለልጆቻቸው፣ ደብተር፣ ስክርቢቶ፣ የደንብ ልብስና ምግብ ለማሟላት ከፍተኛ ጫና የሚፈጥር እንደነበር አውስተው እነዚህ ሁሉ በመንግ ሥት መሸፈናቸው የወላጆችን ጫና የሚያቃልልና እፎይታን የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል። መንግሥት ለከተማው ትምህርት ቤቶች ያደረገው የሚያበረታታና ይህ በጎ ሥራ ወደ ገጠር አካባቢዎችም ቢሰፋ መልካም መሆኑንም ጠቁመዋል። እነሱም በረከቱ ይድረሳቸው ሲሉ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል መጋቢ እሸቱ።
ትምህርት ቤቱ መስከረም 26 ቀን 2012ዓ.ም ትምህርት ለመጀመር አስፈላጊውን ዝግጅት እንደአጠናቀቀ የሚገልጹት የመስከረም አጸደ ህጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ጸጋዬ ቀዲዳ ፤ እስካሁን ድረስ ከአጸደ ህጻናት እስከ
ስምንተኛ ክፍል ድረስ 667 ተማሪዎች መመዝገባቸውንና ለሁሉም ተማሪዎች የደንብ ልብስ እና የመፃፊያ ቁሳቁስ የተሰጣቸው መሆኑን ገልጸው ለተወሰኑት ተማሪዎች የደንብ ልብሱ ልኬት ችግር በማጋጠሙ በምትኩ ሌላ ተቀያሪ የደንብ ልብስ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።
እንደ አቶ ጸጋዬ ገለጻ ደብተር፣ስክርቢቶ፣የደንብ ልብስና የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራሙ በተለይ በአብዛኛው አነስተኛ ገቢ ለሚያገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ።ሌላው ትምህርት ቤቱ ከተሰራ ጀምሮ አልታደሰም፤አሁን ትምህርት ቤቱ ታድሶ ተማሪዎች አምሮ ሲያዩት በጣም ደስ ይላቸዋል። ለትምህርት አቀባበልም አወንታዊ ሚና ይኖረዋል።
ትምህርት ቤቱ ከ2009 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በረድኤት ድርጅቶችና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ድጋፍ 100 የሚደርሱ ሴት ተማሪዎችን ትምህርት እንዳያቋርጡ ደብተር፣የደንብ ልብስ፣ስክርቢቶ ፣ቅባትና ሳሙና ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚማሩ መሆናቸውን አውስተው ዘንድሮም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶበት ምግብ፣የደንብ ልብስና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረጉ የትምህርት መቋረጥን የሚቀንስና የወላጆችን ጫና የሚያቃልል ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ በመማር ማስተማሩ ላይ እፎይታን ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል።
የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ለመጀመርም አዲስ የመመገቢያ አዳራሽ መሰራቱን አመልክተው ተጨማሪ የማብሰያ ቦታ ገና እስከሚሰራ እየተጠባበቅን ነው ሲሉ ገልፀዋል። የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራሙ ጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚጀመር ነግረውናል ።
ሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መስከረም 26 ቀን 2012ዓ.ም ትምህርት እንደሚጀምሩ የሚጠበቅ ሲሆን ለዚህም ተማሪዎቻቸውን እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። የ488ቱ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ዕድሳት የተጠናቀቀ ሲሆን ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ›› እንደሚባለው ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ተደስተውና ጓጉተው ትምህርት ቤት እንዲመጡ ያደርጋቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው ዓመት 240 ሚሊዮን ብር በሚገመት ወጪ 600ሺ ለሚጠጉ ተማሪዎች የደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁሶች ማለትም ደብተር፣ስክርቢቶና እርሳስ በነጻ የተሰጠ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2012
ጌትነት ምህረቴ