የዛሬ ሦስት ዓመት በዚህ ወቅት በቢሾፍቱ- ሆራ ሀርሰዴ በከፍተኛ የጸጥታ ኃይሎች ተከቦ የተከበረው የኢሬቻ በዓል፣ ታሪክ የሚዘክረው ክስተት አስተናገደ። በዚህ ክስተት የበርካቶች አካል ጎደለ፤ የበርካታ ንጹሃን ዜጎችም ህይወት ተቀጠፈ። በዛን ወቅት የኦሮሞ ወጣቶች ‹‹ህዝባዊ መንግሥት ይቋቋም›› በሚል የጭቆና ትግላቸው ሁለት እጆቻቸውን አጣምረው ከፍ በማድረግ ለነጻነታቸው የሰላማዊ ትግል ድምጻቸውን በህብረት አሰሙ።
ምንም እንኳን ኢሬቻ ከፖለቲካ እሳቤ በጸዳ መልኩ የሚከበር የሰላም በዓል ቢሆንም፤ እነዚህ ብሶት የወለዳቸው ወጣቶች አጋጣሚውን ተጠቅመው ድምጻቸውን ከማሰማት ወደኋላ አላሉም። ይህ ድምጽና ድርጊት ግን ቸል አልተባለም፤ በጸጥታ ኃይሎችና ወጣቶች መካከል በነበረው ግርግር በርካቶች የገደል ሲሳይ ሆኑ። ይህ ድርጊት ከፍተኛ የኀዘን ጠባሳን አሳርፎ ያለፈ ቢሆንም፤ በርካቶችን ለላቀ ትግል ያነሳሳ ነበር። ከወራት በኋላም ትግሉ ፍሬ አፈራ። የወጣቶች ጥያቄም በአብዛኛው ተመለሰ። የሰላም ጸር ተብሎ በጦር መሳሪያ እየተጠበቀ በዓል ያከብር የነበረው ወጣትም ዛሬ ራሱ የሰላሙ ባለቤትና ጠበቃ ሆነ።
ዛሬ ከሶስት ዓመት በኋላ በቢሾፍቱው ሆራ ሀርሰዴ ታሪክ ተቀይሯል። የጸጥታ ኃይሎች ሥራ በአባገዳ ፎሌዎችና ቄሬዎች ተተክቶ ለህዝቡ ሰላምና ደህንነት እጅ ለእጅ ተያይዘው ደፋ ቀና ይላሉ።ጥቂት የጸጥታ ኃይሎች አለፍ አለፍ ብለው የወጣቶቹን ተግባር ሲያግዙና ሲመሩ ከመታየታቸው በቀር ሥራ አልበዛባቸውም። ይህን ሁነት የተመለከቱ የተለያዩ የበዓሉ ተሳታፊዎችም ኢሬቻ የመተባበርና የሰላም በዓል ስለመሆኑ መታዘባቸውን፤ በተለይ ከሦስት ዓመት በፊት በቦታው ተከስቶ ከነበረው ሁነት ጋር አያይዘው የሰላምና ትብብርን ዋጋ ይገልጻሉ። ህዝቦችም ተባብረው ሊሰሩ፤ ለሰላማቸውም ዘብ ሊቆሙ ከቻሉ የዕለቱ ሁነት እማኝ ነውና ሁሉም በዚሁ አግባብ ሊሰራ እንደሚገባም የአደራ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
ለዛሬው ዕለት በመብቃታቸው ፈጣሪን በማመስገን ሀሳባቸውን ያጋሩን፣ ሀደ ሲንቄ በቀለች ባረና እና ሀደ ሲንቄ ሀሊማ ወዳጆ እንደሚሉት፤ የዛሬ ሦስት ዓመት በቢሾፍቱ ሆራ ሀርሰዴ ኢሬቻን ለማክበር በስፍራው ተገኝተው ነበር። በወቅቱ በተከሰተው ችግር በርካቶች ሲሞቱ እነርሱ ከሞት የተረፉ ቢሆንም፤ የዛን ጊዜው ሁነት ግን ከአእምሯቸው አልጠፋም። የዛን ወቅት እንደ ጸረ ሰላም ይታይና በወታደሮችም ተከቦ በዓሉን ሲያከብር የነበረው ወጣት፤ ዛሬ ላይ የጸጥታ ኃይሉን ቦታ ተክቶ የሰላም ባለቤትነቱን በተግባር ሲያሳይ ማየታቸው እጅጉን አስደስቷቸዋል።
ይህ ደግሞ ኢሬቻ የሰላምና አንድነት፣ በጋራ ቆሞ ፈጣሪን የማመስገኛ በዓል እንጂ፤ የግጭትና የመጠላላት አለመሆኑ የታየበት ነው። በዕለቱ የታየው የደስታ፣ ሁሉም ህዝብ በፍቅር በአንድነት ቆሞ ሲጨፍርና ምስጋናውን ሲያቀርብ መመልከቱ ህዝቦች በጋራ ከቆሙና ሰላማቸውን ካስጠበቁ ሁሉንም ማድረግ እንደሚችሉ ያመላከተ ሆኗል። በቀጣይም በዓሉ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሀብት እንዲሆን መስራት፤ ህዝቦችም ለሰላማቸውም ሊተባበሩ ይገባል።
ኢሬቻ በአንድነት የሚከበር ሰላማዊ በዓል ሆኖ ሳለ የዛሬ ሦስት ዓመት በሆራ አርሰዴ እንዲሆን የተደረገው ጉዳይ ያልተገባ፤ የበርካታ ወገኖችን ሕይወት የቀጠፈ መሆኑ እጅጉን አሳዛኝ ተግባር መሆኑን የሚያነሱት ደግሞ ወጣት ምንዱ ቸሩ እና ወጣት ገመቹ ደጉ ከቢሾፍቱ፣ እንዲሁም ወጣት ብርቄ ኤጄታ ከአዲስ አበባ ናቸው። ወጣቶቹ እንደሚሉት፤ የኦሮሞ ወጣት ከገዳ ስርዓቱ የተማረው የሰላምና የመተባበር ባህል እንጂ ሌሎችን የሚገፋና ሰላምንም የሚያደፈርስ አይደለም። በወቅቱ የተከሰተውም የወጣቱን ጥያቄ ያለመገንዘብ ካልሆነም ለማፈን ሲባል እንጂ ወጣቱ የሰላም ፀር ሆኖ አልነበረም።
በዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ላይ የሰላሙን ሥራ በኃላፊነት መወጣት መቻሉ ደግሞ የዚህ ማሳያ ሲሆን፤ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ተባብሮ መስራት መቻሉም በዓሉ ያለችግር እንዲጠናቀቅ አድርጎታል። በቀጣይም በዓሉ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የሁሉም መሆኑን ማሳየት፤ ይሄን ትብብሩን በማጠናከር የሰላም ባለቤትነቱን ማረጋገጥ ይገባዋል።
ከምዕራብ ጉጂ የመጡት አቶ ታደሰ ሀዳማ እንደሚሉት ደግሞ፤ በዓሉ በህዝቦች መካከል አንድነት የነበረ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ህዝቡ የበለጠ ወደ አንድነት እየመጣ ስለመሆኑ ማሳያ ሆኗል። ገዳ ደግሞ ማቀፍንና ጉዲፈቻን እንጂ ሰውን መለየትና ማግለልን አያውቅም። መገፋትና ጭቆናም ምን ውጤት እንዳለው ከሦስት ዓመት በፊት በሆራ ሀርሰዴ የተፈጠረው አሳዛኝና የበርካታ ወገኖችን ሕይወት የቀጠፈው ክስተት ምስክር ነው። በመሆኑም ኦሮሞ የአቃፊነት የገዳ እሴቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ወጣቱን የበለጠ ማስተማርና በማሳወቅ የኦሮሞን ህዝብ የበለጠ የአቃፊነትና የህዝቦችን አንድነት ፈላጊነት መሆን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ምክንያቱም አንድ ሰው አንድ እግሩን ቢያጣ መራመድ እንደማይችል ሁሉ፤ የኢትዮጵያ ህዝቦችም ቢነጣጠሉ ኢትዮጵያን መገንባት አይችሉም። ስለዚህ ኢሬቻን በመሳሰሉ ህዝባዊ በዓላት ላይ የሚታዩ የአንድነትና በፍቅር አብሮ የመቆም ክዋኔዎች በቀጣይም በህዝቦች ግንኙነት ሁሉ በዚሁ የትብብር መንፈስ ሊቀጥል ይገባል። ትብብሮች ፍሬያማ የሚሆኑት ደግሞ ሰላም ሲኖር እንደመሆኑም፤ ሁሉም ህዝብ ባህልና በዓሎቹን አብሮ በድምቀት እንደሚያከብረው ሁሉ ለጋራ ሰላሙም በጋራ መቆም ይገባዋል።
በበዓሉ ተሳታፊ የነበሩና ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀት የሆኑ ብሔር ብሔረሰቦችም ይሄንኑ ሀሳብ ይጋራሉ። በበዓሉ ከተገኙት መካከል አቶ ሙራድ ረዲ ከአላባ ቁሊቶ፣ አቶ ቦካንሳ ጤቂሴ ደግሞ ከሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ በዓሉን ለመታደም የተገኙ ናቸው። እነሱ እንደሚናገሩት፤ ከሦስት ዓመት በፊት በዚህ ቦታ የነበረው ክስተት የንጹሃንን ሕይወት ከመቅጠፉም በላይ የዓለም ሚዲያ ትኩረት እስከመሆን የደረሰ ነው። በዚህ በአጭር ጊዜ ያ ታሪክ እንዲቀየርና ለውጥም መጥቶ ወጣቱ በዓሉን በሰላም ለማክበር ከፍተሻ እስከ ጥበቃ ያለውን ሥራ ሲያከናውን ማየትና በዓሉም በዚህ መልኩ ሰላማዊ ሆኖ መከበሩ እጅጉን የሚያስደስት ነው።
ከዚህ ባለፈም በዓሉም በትክክልም የአንድነት፣ የፍቅርና በይቅርታ አብሮ የመኖር መሆኑን የተረጋገጠበት ነው። በመሆኑም በዓሉ የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ሀብት መሆን የሚገባው ነው። ይህ ደግሞ ሰላምና ትብብር ሲኖር ብቻ እውን የሚሆን እንደመሆኑ፤ ይሄን አይነት በዓላት ሲከበሩ የሚፈጠረውን መነሳሳት መሰረት በማድረግ መተባበርና ሰላም የሁሉም ቋንቋ ሊሆን ያስፈልጋል። ቀጣይ በዓሉ ሲከበር የበለጠ ጎልቶ ሊወጣ እና ለጋራ ሰላም ተባብሮ መስራት የሚቻልበትን እድል ለመፍጠር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
በሦስት ዓመት በፊት በቦታው ኢሬቻን ሲያከብሩ በተፈጠረው ችግር ምክንያት በአካባቢው በነበረው ጭስ እርሳቸውም ለሶስት ሰዓታት ያክል ራሳቸውን ስተው እንደነበር በመግለጽ፤ ዕለቱ ትልቅ ጠባሳን ጥሎ ያለፈ ስለመሆኑ የሚናገሩት ደግሞ በባሌ ዞን የመዳወላቡ አባገዳ የሆኑት አባገዳ አደም ቲና ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነው። ኦሮሞ ደግሞ ሁለት የምስጋና ቀኖች አሉት፤ አንደኛው ክረምቱ አልፎ ጸደይ ሲመጣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የተሸጋገረበትን ወቅት ምክንያት በማድረግ በወንዝ ዳር፤ ሁለተኛው ከበጋ ወደ ክረምት ሲሸጋገር ክረምቱ ለሰብል የሚስማማ እንዲሆን ከፍ ባለ ተራራ ላይ ወጥቶ የሚለምንበት ነው።
ይህ የምስጋና ቃል የሚያሳየው ደግሞ ለአንድ ወይም ለሁለት ሰው ሳይሆን ለአገርና ህዝብ ማሰብን በውስጡ የያዘ ነው። ይሄን አይነት የምስጋና በዓል ደግሞ ሰላም፣ መተባበርንና በፍቅር አንድ ሆኖ መቆምን የሚጠይቅ በዛው ልክም የሚከወን ነው። ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት የተፈጠረ ያልተገባ የፖለቲካና የጠመንጃ የበላይነት እሳቤ ተግባር በርካታ ወገኖችን ሕይወት ቀጥፎ አልፏል። ዛሬ ግን ታሪክ ተቀይሮ የበዓሉ አቃፊነት፣ አሳታፊነትና በፍቅር አብሮ በሰላም የሚከበር መሆኑ ተገልጧል። በመሆኑም በጠመንጃ ከመግዛት ወጥቶ እንደ ኢሬቻ አይነት እሴቶችን በማጎልበት ወጣቱን የሰላም ባለቤት ማድረግ ይገባል፤ ህዝቡም ለዚህ ሥራ በፍቅር ተባብሮ ሊቆም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2012
ወንድወሰን ሽመልስ