ልዩነት ማለት አንድ አለመሆን አይደለም፤ አንድነት ሲባልም አንድ አይነትነት ማለት አይደለም። ልዩነት ያለ አንድነት፤ አንድነትም ያለ ህብር ሃይልም ድምቀትም የላቸውም። ይህ በአንድነት ውስጥ የሚገለጽ ህብር ሃይል፣ ድምቀትና ውበት ደግሞ ልክ እንደ ጥበብ ሸማ የሚገለፅ፤ በአንዱ ውስጥ ብዙ፣ ብዙውም በአንድ የሚገለጽበት እውነት ነው። የኦሮሞ ህዝብም አንድ ህዝብ ሆኖ ሳለ፤ በሕብር ያጌጠ፣ በአንድነት ድር ተጋምዶም በፍቅር ጸንቶ የቆመ፣ ለብዝሃነቱም ክብር ሰጥቶ ብዙሃንን አቅፎ የያዘ ነው።
በአዲስ አበባ ትናንት የተከናወነው የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል አከባበርም የዚህ ሃቅ አንድ ማሳያ ሲሆን፤ ለበዓሉ በአራቱም አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ የገባው የኦሮሞ ህዝብ አንድ ሆኖ ብዙ፣ ብዙም ሆኖ በፍቅር አንድ መሆኑን በተግባር የገለጸበት ትዕይንት ነበር። በዓሉን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ ከዋዜማው ጀምሮ በመስቀል አደባባይ ደምቆ ያመሸውና በዛው ድባብ ውስጥ ያደረው የአዲስ አበባው ሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል አከባበር ሥነስርዓት፤ ትናንትም ገና ጨለማው ለብርሃን በወጉ ስፍራውን ሳይለቅ ነበር የምስጋና ስነስርዓት ወደሚከናወንበት መልካ በአባገዳዎች መሪነት የተኬደው።
ለኦሮሞ ህዝቦች ብሎም ለኢትዮጵያውያን ሰላምና አንድነትን በመለመን በአባገዳዎች ምርቃት የተጀመረው መርሃ ግብርም፤ ዘመኑ የተወለዱ የሚያድጉበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ ያጡ የሚያገኙበትና ያገኙም የማያጡበት፣ ክፋት የሚርቅበትና ፍቅር የሚጸናበት፣ የህዝቦች መተሳሰብና በጋራ መቆም በተግባር የሚገለጽበት እንዲሆን የተመኙበትም ነበር። አባ ገዳዎች በምርቃትና ምስጋናቸው ውስጥ ለኦሮሞ ብሎም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የአደራ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ በመልዕታቸው እንዳመለከቱትም፤ ህዝቦች ለዘመናት በጭቆናና መገፋት ውስጥ ኖረዋል። ለነጻነታቸው በጋራ ታግለውም ድል አድርገዋል።
በሆራ ፊንፊኔ የተከበረው የኢሬቻ በዓልም የህዝቦች ድል አንድ ማሳያ ሲሆን፤ በዓሉም ለዓመታት ተራርቀው የነበሩ ነገር ግን በፍቅር ሲፈላለጉ የነበሩ አንድ ህዝቦችን ያገናኘ ድልድይ ሆኗል። የኦሮሞ ህዝቦች የአንድነት፣ ህብረ ብሔራዊነት፣ ፍቅርና አቃፊነት ብሎም ሰላማዊነት ተገልጾበታል። በመሆኑም ይሄንና መሰል የድል ውጤቶችን ጠብቆ ማቆየት፣ የጋራ እሴት አድርጎ መጠቀም፣ ብሎም በህዝቦች መካከል ፍቅርና አንድነት ማጽኛ ማድረግ ይገባል።
የኦሮሞ ህዝብ ለ150 ዓመታት ርቆ ከነበረበት የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል አከባበር ዳግም በመመለሱ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ፤ በዓሉ በዚህ መልኩ መከበሩ የኦሮሞ ህዝቦች በአንድ ቦታ ተገኝተው ምስጋናቸውን ለማቅረብ፣ ባህልና እሴታቸውንም ለማሳየት እድል የሚፈጥርላቸው ስለመሆኑ የሚናገሩት ከጎለልቻ ወረዳ የበዓሉ ተሳታፊ የሆኑት አባገዳ ሁሴን ከድር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ አዲስ አበባ ለመላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ማዕከል እንደመሆኗ፤ በዓሉ በዚህ መልኩ መከበሩ የኦሮሞ ህዝብ ከህዝቦች ጋር ያለውን አንድነትና መተሳሰብ የሚያጠናክርለት ነው።
በዓሉን በዚህ መልኩ ማክበሩም በእምነት፣ በባህል፣ በመልከዓ ምድር፣ በጾታና እድሜ፣ በማህበራዊ ደረጃና ሌላም ነገር የኦሮሞ ህዝብ ባህሉን ለመጠበቅ በጋራ እንደሚቆም የሚያሳይ ነው። በህብር ደምቆ መታየቱም አንድነት፣ ፍቅርና አቃፊነትን የመሳሰሉ የባህሉን እሴቶች በተግባር ማዋሉን የሚያመላክት ነው።
ሆኖም ዛሬም ይሄን ህዝብ አንድነቱን ለማናጋት በተለያየ መልኩ የሚንቀሳቀሱ መኖራቸውን ሳይዘነጋ ቀደም ሲል አያት ቅድመአያቶቹ ከሁሉም የኦሮሞ አካባቢዎች መጥቶ በዓሉን ሲያከብሩ የነበራቸውን ህብረት በማሰብ፤ በቀጣይም ኦሮሞ የባሌ፣ የአርሲ፣ የከረዩ፣ የሸዋ፣ የጉጂና ሌላም እያለ በወንዝና በአካባቢ ሳይከፋፈል አንድነቱን ሊያጠናክር፤ ፍቅሩንም ሊያጸና እና ሁሉን አቃፊነቱን የበለጠ ሊተገብር ያስፈልጋል። ኢሬቻ በሆራ ፊንፊኔ የመከበሩ አንዱ ዓላማም ይሄው በአንድነት ህብር ደምቆና ተባብሮ ወደፊት የመሄድን ጉዞ ማስጀመሪያ ሊሆን ይገባል።
አቶ ዮናስ ለገሰ፣ ከኢሉአባቦር ያዮ ወረዳ፣ እንዲሁም ወጣት ጣሂር አማን፣ ከአዳሚ ቱሉ ወረዳ፣ የዚሁ በዓል ተሳታፊዎች ናቸው። እነርሱ እንደሚሉት፤ በዓሉ፣ የኦሮሞን ህዝብ አንድነትም የባህል ብዝሃነትም በጉልህ የታየበትና እጅጉን የሚያስደስት ነው። የህዝቡ ፍቅርና አቃፊነትም አደባባይ የወጣበት፤ በህዝቦች መካከል በፍቅር ተሳስሮ መተባበርና መደጋገፍ ለመኖሩ ምስክር ነው።
ይሄው አንድነት ድምቀት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። የላቀ ፍቅርና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩም በተጀመረው አግባብ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችም ከኦሮሞ ህዝብ ጋር በጋራ ሊያከብሩት፤ የኦሮሞ ህዝብና ወጣትም በዚሁ ልክ አስቦ ሊያስቀጥለው የሚገባ ነው።
ሌላዋ የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ ሰፊያ ኢድሪስ፣ ከዶዶላ ወረዳ እና ወጣት ጠጄ ሶሩ፣ እንደሚሉት፤ ኢሬቻ አንድነት፣ ፍቅር፣ ሰላምና መተሳሰብ ነው። በሁሉም አካባቢ ያለው የኦሮሞ ህዝብ በዚህ ቦታ መገናኘቱም ይሄንኑ የሚያሳይ ነው። በሆራ ፊንፊኔ ማክበሩም በአንድነት ቆሞ የመታገሉና ጭቆናውን የማስወገዱ ውጤት ሲሆን፤ በዚህ መልኩ በሆራ ፊንፊኔ ተገናኝቶ ሲያከብርም ይሄንኑ አንድነት በመደማመጥና መከባበር ስሜት የበለጠ ለማጠናከር፤ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋርም በፍቅር ተባብሮ ለመኖርና ለመጓዝ ያለውን አቃፊነትም ለማጎልበት ራሱን የሚያዘጋጅበትም ሊሆን ይገባል።
ከአዲስ አበባ የበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል ደግሞ አቶ ገመቹ ገለታ እና አቶ በቀለ ከተማ እንደሚሉት፤ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ህዝቦች ማዕከል ናት። ኢሬቻ ከ150 ዓመታት በኋላ በአዲስ አበባ በቀድሞው ቦታው ሆራ ፊንፊኔ መከበሩ ለኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ድልና ደስታ ነው። በዓሉ የክረምቱ ክብደት፣ የወንዞችም ሙላት አራርቋቸው የነበሩ ህዝቦች በአንድ ተሰባስበው ለዚህ ያበቃቸውን ፈጣሪ የሚያመሰግኑበት እንደመሆኑ፤ በየአቅጣጫው ያለ ወንድማማች ህዝብ ያለልዩነት በፍቅርና በአንድነት የሚሳተፉበትም ነው።
አዲስ አበባም በዓሉ የሚከበርባት ሆና ለዘመናት ያገለገለች ቢሆንም፤ ላለፉት 150 ዓመታት ግን ይህ ተቋርጦ፤ ህዝቡም ለጭቆና ተጋልጦ ቆይቷል። አሁን ግን በድጋሚ ሆራ ፊንፊኔ የኦሮሞ ህዝቦች ብሎም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ ተሰባስበው የሚያከብሩበት የፍቅርና የአንድነት ቦታ ስለሆነ፤ በቀጣይም በዓሉ ሁሉን አቃፊነቱን አስጠብቆ ተጠናክሮ መጓዝ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2012
ወንድወሰን ሽመልስ