መሠረታዊ እሳቤ
ፍልስፍና በየዘመናቱ ዓይኑን ከሚጥልባቸው ትላልቅ ሥነ ምግባራዊ ሐሳብና ተግባራት አንዱ በጎ ፈቃደኝነት ነው። ፍልስፍና ሲነሳ ስሙ ሳይጠቀስ የማይታለፈው የግሪኩ ሰው አርስቶትል ከ2300 ዓመታት በፊት “What is the essence of life? To serve others and to do good፤ የሕይወት ትርጉም /ባህርይ/ ይዞታ ምንድነው?›› ብሎ ከጠየቀ በኋላ የደመደምው ‹‹ሌሎችን ማገልግልና መልካምን ማድረግ ነው።›› ብሎ ነበር። ለዚህም የሕይወትን ባህርይ ይዘረዝራል።
ሕይወት ያላቸውን ነገሮችም ባላቸው ችሎታ ከፋፍሏቸዋል፤ ዕፅዋት፣ እንስሳት፣ ሰው እና አምላክ እያለ። እንስሳት አድገው ኃይልን ተጠቅመውም ዳግም ይራባሉ። ሕይወታቸውን ይከፍላሉ። ለሚፈልጋቸው ራሳቸውን የሚጋሯቸው የሚጠቀሙባቸው አድርገው ባህርያቸውን ያዘጋጃሉ። ቅጠላ ቅጠል፣ አበቦችንና ፍሬዎችን ይሰጣሉ። በእንስሳት ህይወትም ይህ ሁሉ ያለ ሆኖ በእንቅስቃሴ ችሎታቸው ደግሞ ከዕፅዋት በተሻለ ባገኙት የእንቅስቃሴ ችሎታ ተጠቅመው የበለጠ ለምድርና ምድራውያን የሚሰጡት ነገር አላቸው። ሰው ግን ከዚህ በተሻለ ችሎታ/አቅም ላይ ይገኛል። እንደ አርስቶትል ገለጻ ሰው ያለው የማሰብ፣ ቋንቋን የመጠቀም፣ የበለጠ የመረዳት ችሎታው የበለጠ የሚሰጥና ብርቱ ማኅበራዊ ፍጥረት እንዲሆን አድርጎታል። ፖለቲካዊ አካሔድን የሚያውቅ፣ የነገን አቅዶ የሚሰራ፣ ምኞትና ፍላጎቱን የመቆጣጠር/ራሱን የመግዛት/፣ ታናናሾቹን የማስተማር፣ የመጠበብ፣ ዓለምን የመመርመር / የመፈላሰፍ/ ችሎታ ያለው በመሆኑ ብዙ የማድረግ አቅም አለው። ብዙ የመስጠት ዕድልም አለው። ስለዚህ በፈቃዱ በጎ የማድረግ አቅም እንዳለው ሁሉ ክፉውን የማስቀረት/የመከልከልም አቅም አለው። ለዚህም ነው አርስቶትል የሕይወትን ትርጉም ሌሎችን ከማገልግልና በጎውን ከማድረግ ጋር ያገናኘው።
በእርግጥም የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ቁልፍ ትርጉም ለሌሎች ለአገልግሎቱ ተቀባዮች፣ ለማኅበረሰቡ፣ ለራሳቸውም ለበጎ ፈቃደኞቹ የሚሰጠው ጥቅም /benefits it offers/ መኖሩ ነው።
ስለዚህም በአካባቢም ሆነ ድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚሰጡ ወገኖች ሁሉ ለማኅብረሰቡ የሚሰጡት ድጋፍ ይኖራል። ድጋፉም የሚፈልገውን ለይቶ የሚሰጥ ድጋፍ ነው። በዚህ ወቅት አገር አቋርጠው የሚሄዱ በጎ ፈቃደኞች የማኅብረሰቡንም ባህልና ማንነት የማወቅ ዕድል ያገኛሉ።
ሌላው ወደር የለሽ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መምህር፣ ፈላስፋ፣ የፖለቲካ መሪና የመልካም እሴቶች አፍላቂ የሕንዱ ማህተመ ጋንዲ ነው። ማህተመ ጋንዲ “The best way to find yourself is to lose yourself in the service of others ፤ ራስህን ፈልገህ የምታገኝበት እጅግ ተመራጩ መንገድ ሌሎችን በማገልገል ውስጥ ራስህን በመስጠት/በመሰዋት/ ነው።›› ብሏል።
በዚህ ሳንገደብ እጅግ መሳጭ በሆነው በነጻነት ታጋዩ ማርቲን ሉተር ኪንግ ወርቃማ ቃልም እንደመም። ማርቲን ሉተር ኪንግ “Life’s most persistent and urgent question is, What are you doing for others?፤ የሕይወት የማያባራና እጅግ ወሳኝ የሆነው ጥያቄ ‹ለሌሎች ምን አደረግህ?› የሚለው ነው›› ይለናል።
ከእነዚህ ብርቱዎች አንደበት የወጣው የቃላት ኃይል የሕይወትን ትርጉም፣ የሕይወትን ጣዕም፣ የሕይወትንም ደስታ አቅጣጫ አመላካች ነው። ሌሎችን ለማገልገል በመፍቀድ ውስጥ የምንሰጠው መልካም ነገር የራስን ሕይወት እና ዓለማችንን ምን ያህል መልካም እንደሚያደርጋት ማሰብ ይቻላል።
ስለዚህም ዓለማችንን እጅግ ተመራጭና ተስማሚ ዓለም የማድረግ ዕድልም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቋጠሮ ውስጥ ይገኛል። በምንኖርበት ዘመን ውስጥ ታይተው በቅርቡ በሕይወት የተለዩን የዓለማችን መሪ የነበሩት ኮፊ አናና ይሄን ሲያረጋግጡልን “If our hopes of building a better and safer world are to become more than wishful thinking, we will need the engagement of volunteers more than ever፤ የተሻለና ደህንነቷ የተጠበቀ ዓለም የመገንባት ተስፋችን ከምኞት ያለፈ ሊሆን ከተገባው ከመቼውም ጊዜ በላይ የበጎ ፈቃደኞችን ተሳትፎ እንሻለን›› ብለው ነበር። ዓለማችን በጎ ፈቃደኞችን የሚፈልጉ እጅግ በርካታ ጉዳዮች ያሉባት ሆናለችና።
የበጎ ፈቃደኞችን አገልግሎት የሚሹ ወሳኝ የዓለማችን ጉዳዮች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሚያወጣቸው መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው ዓለማችን በየቀኑ ለመኖር የማትመች እያደረጓት ያሉ ፈተናዎቿ በቁጥር እየጨመሩ ነው። እነዚህም ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ደግሞ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከሚያደርጓቸው ተረቶች በተጨማሪ የእያንዳንዱን የምድራችንን ነዋሪ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት የሚሹ ሆነዋል።
የአየር ንብረት መዛባት የዓለማችን ግዙፍ ችግር ሆኗል። የዓለም ሙቀት መጠን በእጅጉ እየጨመረ ነው። አሁን አለ የሚባለው 2.6 ዲግሪ ሴሊሺየስ የደረሰው የዓለማችን የሙቀት መጠን በ2100 ዓ.ም ላይ ወደ 4.8 ዲግሪ ሴሊሺየስ ይደርሳል የሚል ስጋት አለ። ዓለማችን ለመኖር የማትመች እየሆነች ነው። ከዚያም ጋር ተያይዘው የሚመጡ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች አሉ፤ ቃጠሎ፣ ጎርፍ፣ ተላላፊ በሽታ ወዘተ ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎችን የተጠሙ ጉዳዮች ናቸው።
የአካባቢ ብክለት ሌላው ወሳኝ ችግር ነው። በአካባቢያችን ውስጥ ውቅያኖሶች እየተበከሉ ነው። በፋብሪካዎች ተወጋጅ ፍሳሽ፣ በቆሻሻ፣ በመርዛማ ንጥረ ነገሮች፣ የማዳበሪያ ኬሚካሎች፣ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች የውሃ አካላት እየበከሉ ነው። በዓለማችን እስከ አንድ ቢሊዮን የሚሆን ሕዝብ ለንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት የተጋለጠ ነው። በተጨማሪም የአየር ብክለት፣ የብርሃንንና ድምጽ ብክለት የዓለማችን ራስ ምታቶች ናቸው። እነዚህ ችግሮች በፍጥነት እንዲቀረፉ ከተፈለገ የበጎ ፈቃደኞችን ትጋት የተራቡ ጉዳዮች መሆናቸውን መረዳት አስፈላጊ ነው።
ሌላው ችግር ከኢኮኖሚ፣ ከማኅበራዊ፣ ከፖለቲካዊ፣ ባህላዊ ጉዳዮቻችን የመነጩ ግጭቶችን ፍጥጫዎችን በዓለማችን ማንገሣቸው ነው። በዓለማችን ጓዳ ጎድጓዳዎች ውስጥ የሰው ልጆች ደህንነት ስጋት ላይ እየወደቀ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ሽብር ለዓለማችን አደገኛው የደህንነት ስጋት ሆኗል።
የትምህርት ተደራሽነት ችግር ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው። በዓለማችን 72 ሚሊዮን ሕፃናት ዕድሜያቸው ለትምህርት ቢደርስም የትምህርት እድል ተጠቃሚ መሆን ግን አልቻሉም። በአንድ በኩል ለሥራ ዕድል ፈጠራ አመቺ ባልሆኑ ትምህርቶች ላይ በመሠማራት በሌላም በኩል ከኢኮኖሚ ድቀት የተነሳ የዓለማችን ወጣቶች ለሥራ አጥነት እየተዳረጉ ያሉበትም ምጣኔ እየጨመረ ነው። ይህ ደግሞ በቂ ምግብና መጠለያ በቂ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንዳያሳልፉ እያደረገ ነው። ከዚህ አልፎ ደግሞ በርካታ ወጣቶች ለሱሰኝነት ተዳርገዋል። በተለይም የአደንዛዥ ዕጾች ተጠቃሚነት ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ በሆኑ 185 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ታይቷል።
በሌላም በኩል 790 ሚሊዮን የዓለማችን ሕዝብ በቂ ምግብ ማግኘት የማይችል ነው። በቂ ምግብ አለማግኘት ብቻም ሳይሆን በረሃብ እየተቆሉ ያሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
ስለዚህ የሰው ልጆች ተዘርዝረው ለማያልቁት ለአካባቢያችን እና ለዓለማችን ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ‹‹ከእጄ የማዋጣው ምን አለ?›› ብሎ እንዲያስብ ይገደዳል። እንግሊዛዊው ጸሐፌ ተውኔት ዊሊያም ሼክስፒር ይህን የሚያደርገው “The meaning of life is to find your gift. The purpose of life is to give it away/ የሕይወት ትርጉም የተሰጠንን/ያለንን ጸጋ/ ማወቅ ነው፤ የሕይወት ዓላማ ደግሞ ያለንን መስጠት ነው›› እንዳለው ሕይወት ለራሳችንም ሆነ ለሌላው ትርጉምና ዓላማ ያላት በዚህ ለሌሎች በጎውን የማድረግ እርምጃ ውስጥ ሲገባ ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያም በዚሁ መከራው ሞልቶ በተረፈባት ምድር ላይ የምትገኝ ይልቁንም የችግር ቅራቅንቦ በተከማቸባት አህጉራችን አፍሪካ ውስጥ ያለች በመሆኗ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በጥብቅ ከሚሹ ሀገራት አንዷ ነች።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመስጠት ባህል የነበራትና በፍጹም ወንድማማችነት ዜጎች የሚኖሩባት ችግራቸውን በጋራ በመተባባር የሚያሳልፉባት ሀገር ነች። ይህ በመስጠት የሚገለጸው በጎ ፈቃደኝነት የሀገሩ ባህል ነው። ልዩ ልዩ ዓይነት ልማድና ወግም ነበር። ሲወልድ የግምዶ፣ ሲያዝን የዝን ብሎ ከመስጠት ጀምሮ ሲዘምት የስንቅ፣ ሲመለስ የደስታ፣ ሲሻር የሹመት አይደንግጥ፣ ሲሾም የምስራች፣ ለሠርግ ሲጠራ ለጽም…. ብሎ እስከመስጠትም የረቀቀ ነው። ከምንም በላይ ግን ወርቃማ የነበረው ሲታመሙ የመጠየቂያ ብሎ ከመስጠት ጀምሮ ሲወረስ፣ ሲክስ፣ ሲቃጠልበት፣ ሲቀማ… እርጥባን ብሎ መስጠት የተለመደ ነበር።/ፍኖተ አእምሮ፤ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ፤ 1953 ዓ.ም/
ለችግረኞች፣ ለአረጋውያን፣ ለእጓለ ማውታ ተሰብስቦ በደቦ ማረስ፣ መውቃት፣ ሰብስቦ ከጎተራ መክተቱ በግብርና ኖሮ እዚህ ዘመን ድረስ ለዘለቀው ማኅብረሰብ እንግዳ ነገር አልነበረም። ካመረተው እህል ከፍሎ ከመስጠት ጀምሮ፣ በጉልበቱ፣ በሙያው ለችግረኞች መድረስን የሚያውቅ ሕዝብ ነው። ችግር ያጋጠማቸውን ሰዎች ቀስቃሽ ሳያስፈልግ ማገዝ የበጎ እሴቶቻችን አንድ አካል ነው። በተለይ በገጠር መንገድና ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ባልነበረበት ወቅት የታመሙ ሰዎችን በወሳንሳ ተሸክሞ ሩቅ አካባቢ ወስዶ ማሳከም የታማሚው ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆኑ የሀገሬው ድርሻ ነበር። ሙታንን መቅበርም እንደዚያው። ሕዝብ ተባብሮ የቀብር ጉድጓድ ቆፍሮ፣ አስከሬን ተሸክሞ የቀብር ሥነ ሥርአቱን ይፈጽማል። በኢትዮጵያ ሙታንን መቅበር እንደ ሌላው ዓለም የቤተሰብ እዳ ሆኖ አያውቅም። ማህብረሰቡ የጋራ ኃላፊነት የሚወስድባቸው እጅግ በርካታ ጉዳዮች ነበሩት። እንደ አሁኑ የአእምሮ ሕሙማን ማሰባሰቢያ ሳይደራጅ፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሳይገቡበት አካል ጉዳተኞችን እና የአእምሮ ህሙማንን መንከባከብ የጋራ ድርሻ ነበር።
ኢትዮጵያውያን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡት በችግር ወቅት ብቻ አይደለም። ከላይ አስቀድመን እንደጠቀስነው በምርት ስራ ላይም በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ይተጋገዛሉ። የደቦ ወይም ጂጊ ባህልን ለዚህ ማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። ከቤተሰብ አቅም በላይ የሆነ የምርት ስራ ለምሳሌ እርሻ፣ አጨዳ፣ ጎጆ ማዋቀር . . . ሲኖር መንደርተኛው በሙሉ የራሱን መሳሪያ ይዞ በስራ ይተባበራል። ለዚህ መልካም ግብር የሚያዘነበል ሥነ ልቦናም ኢትዮጵያውያን አላቸው።
በግላቸው ብቻ ሳይሆን ለበጎ ነገር በበጎ ፈቃድ በሀገር መሪዎች ጥሪ መዝመትንም ያውቁበታል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለይ በከፉ/በክፉ/ ቀናት እጅግ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ዘመን ተከስቶ በነበረው ክፉ ቀን በተባለው ብዙ እንስሳት ባለቁበት ዘመን አርሶ መብላት፣ ዘርቶ መቃም ጭንቅ ነበር። በዚህም ምክንያት ሰዎች በረሃብ ረገፉ። የከብቱ ማለቅ ለሰው ማለቅ ተረፈ። በዚህ ጊዜ መላ የዘየዱት ንጉሠ ነገሥቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በአርኣያነት ማሳየት ነበር። ማረሻ በሬ/ ከብት/ ባይኖርም እንኳን ራሳቸው ንጉሡ መጥረቢያ አስለው፣ መቆፈሪያ አዋደው የሚቆረጠውን መቁረጥ የሚቆፈረውን መቆፈር ጀመሩ። በሰው ጉልበት ችግርን መወጣት እንደሚቻል ለማሳየትና መኳንንቱም መሳፍንቱም እርሳቸውን አይተው ወርደው ሕዝቡን እንዲያገለግሉ ለማድረግ ጥረት አደረጉ። ንጉሡ እጅና እግራቸው በእሾህና ጋሬጣ እስኪደሙ እስኪቆስሉ ከእንጦጦ ማርያም በታች ያለውን የኤካን ዱር ሁሉ ለማልማት ጥረው ነበር። በእርግጥም ትልቅ ትንሽ፣ ቄስ መነኩሴ ሳይል ሁሉም ተሰልፎ የሚገባውን ያደረገበትን የዚያን የክፉ ቀን ዘመቻ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ በመጽሐፋቸው አውስተውታል።/ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ፤ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፤1901 ዓ.ም/
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ዘመናዊ የሆነውን የበጎ ፈቃደኞች አገልግሎት የበለጠ ባህል ለማድረግ በስፋት የተንቀሳቀሰበት ጊዜ ነበር። ዓለም አቀፍ በጎ ፈቃደኛ ወገኖችም ሀገራችንን በመጎብኘት በህክምና እና በትምህርት መስክ ይሰጡ የነበረው አገልግሎት ለኢትዮጵያውያን ዘመናዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማደግ ብርቱ ተሞክሮዎች ነበሩ።
በወታደራዊው ደርግ የስልጣን ዘመን ደግሞ ምንም እንኳን የተወሰነ አስገዳጅነት ቢኖረውም በ1967 ዓ/ም የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የተሳተፉበት የእድገት በህብረት ዘመቻ እንደ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ልምምድ የሚታይ ነበር።
ላለፉት 16 ዓመታት በሀገራችን ይደረጉ የነበሩ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችም ልማታዊ ሥራዎችን ከማስፋፋት አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው። በአብዛኛው የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠትና በመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር ሥራዎች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ነበር።
ወቅታዊው ተሳትፎ
ከ2010 የክረምት ወራት ጀምሮ ግን እጅግ በተለየ መንገድ በፖሊሲ የሚመራ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲስፋፋ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አማካኝነት ሰፋፊ ዘመቻዎች ተጀምረዋል። የአረጋውያንን ቤቶች በመጠገን፣ ችግረኛ ተማሪዎችን በመርዳት፣ ደም በመለገስ ወዘተ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሯቸውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ሌሎች የማኅበረሰቡ ክፍሎችም ተከትለው ለማስፋፋት ጥረዋል።
በ2011 ዓ.ም የክረምት ወራት የሚካሄደው 17ኛው የክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ አዳማ ከተማ ላይ በይፋ ሲበሰር በዕለቱ ተገኝተው ያስጀመሩት የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ፀጋይ በመርሃ ግብሩ ላይ 12 ነጥብ 7 ሚሊየን በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጣ አገልግሎት በመስጠት ከ22 ሚሊየን በላይ ህዝብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም አመላክተዋል። በአካባቢም ከአካባቢም ራቅ ብሎ በድንበር ተሻጋሪነት በሚሰጡ አገልግሎቶች ዓላማቸው ዒላማ የተደረጉ የማኅብረሰብ ክፍሎችን መጥቀም ብቻ ሳይሆን ሃገራዊ አንድነትን ማጠናከር እና ማህበራዊ እሴቶችን ማጎልበት ነው። የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ ጤና አገልግሎት መስጠት፣ ችግኝ ተከላና ሌሎችም ትኩረት የሚሰጣቸው የአገልግሎቱ መስኮች ናቸው። በተለይ በዚህ ዓመት የተከናወነውና ዓለም አቀፍ ክብረ ወሰን የተሰበረበት በአንድ ጀምበር 200 ሚሊየን ችግኝ የመትከል ተግባርና በአጠቃላይ በክረምቱ በመላው ሀገሪቱ አራት ቢሊየን ችግኞች የመትከል ግብ በዚሁ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተመሠረተ አመርቂ ተግባር ሆኗል።
በዚህ ዓመት በሚደረገው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለይ በአዲስ አበባ ወጣቶች በስፋት እንዲሳተፉበት ለማድረግ ተብሎ ከክቡር ከንቲባው ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጀምሮ ታዋቂ ሰዎች እንዲሳተፉበት ተደርጓል። ከበጋው እንደ ቀጠለ የሚነገረው የአዲስ አበባ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ችግኝ ተካዮችን ጨምሮ እስከ አንድ ሚሊየን ሰዎች እየተሳተፉበት እንደሆነ ተመልክቷል።
በአዲስ አበባ በዘንድሮው መርሃ ግብር ከላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይካሄዳሉ ካልናቸው በተጨማሪ አረጋዊያንን መንከባከብና 500 ያረጁ ቤቶችን ማደስን፣ የቋንቋና የኮምፒዩተር ትምህርትን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ይሰጣሉ። ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን 7.2 ሚሊየን ደብተር በነፃ ማቅረብ፣ ለ600ሺ የተማሪዎች ደንብ ልብስ በነፃ ማቅረብ እና ለ300ሺ ህፃናትም ምገባ ፕሮግራም የማስጀመር ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት በቅርቡ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ ሲታይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሀገራችን በደመወዝ/በምንዳ/ ባለሙያዎችን ቀጥራ ልታቃልላቸው የማትችላቸው በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች አሉባት። ዜጎች የሀገራቸውን ክብር ለማስጠበቅ የራሳቸውንም ደህንነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ ባላቸው እውቀት፣ ክህሎት፣ ጉልበት፣ ገንዘብ፣ ጊዜ እና ሞራል በነጻ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ሊሰጡ ይገባል። በዚህ ውስጥ ታዲያ ደስታን ማጣጣም ይቻላል የሕይወትም ትርጉም ልዩ ይሆናል። ታዋቂዋ ሄለን ከለር ‹‹The unselfish effort to bring cheer to others will be the beginning of a happier life for ourselves፤ ለሌሎች ደስታን ለማምጣት ያለስስት የሚደረግ ጥረት ለእኛ የደስታ ሕይወት መጀመሪያ ይሆናል›› እንዳለች በተለይ ለሀገር የሚሰጥ ሁሉ ለራስ የሚሰጥም ነውና ደስታችንን ድርብ ድርብርብ ማድረግ ያስችላል። ከጉልበት ከእውቀት ከገንዘብ ከጊዜም በላይ የሆነውን ውድ ሕይወታቸውን ለወገን ለሀገር የሰጡ ምርጦቻችንን እያሰብን፣ ትጋት ይገባናል። በተለይ አሁን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሀገራዊ አንድነት፣ ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን የተረዳ መንግሥታዊ አስተዳደር ባለበት ጊዜ ሀገርና ወገን ፈልጎት፣ ተጠይቀን ሳለ ኖሮን ለመስጠት የምንቆጥበው ነገር አይኑር እንላላን።
ዘመን መፅሄት መስከረም 2012
ማለደ ዋሲሁን