በግብጽ ያልተለመዱ የጸረ መንግሥት ተቃውሞዎች በአለፈው አርብ በበርካታ ከተሞች የተቀሰቀሰ ሲሆን ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት አብደልፋታህ አልሲሲ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ መጠየቃቸውን አሶሽየትድ ፕሬስ ከካይሮ ዘግቧል፡፡ በተለያዩ የግብጽ ከተሞች ውስጥ የተካሄዱትን የተቃውሞ ሰልፎች አድማ በታኝ ፖሊሶች አስለቃሽ ጋዝ በመተኮስ እንዲበተን ቢሞክሩም ለማስቆም አልተቻላቸውም፡፡
የግብጽ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ መብት ማዕከል በርካታ ሰዎች ቢያንስ ሁለት ጋዜጠኞችን ጨምሮ ታስረዋል፤ ጉዳት ግን አልደረሰም ሲል ገልጿል። ፕሬዚዳንት አልሲሲ የቀድሞ የግብጽ ሠራዊት ጀነራል የነበሩ ሲሆን ያልተጠበቀ የፖለቲካ መፈረካከስ በመፍጠር ተቺዎችን ጸጥ ያሰኙ በሺዎች የሚቆጠሩትን ወደ እስር ቤት ያጋዙ መሆናቸውን የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ ይገልጻል፡፡
አብደልፋታህ አልሲሲ መከላከያ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ሠራዊቱን አስተባብረው በመምራት በምርጫ ሥልጣን ላይ ይዞ የነበረውን የመሀመድ ሙርሲ መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥት በማውረድ ነበር በ2013 (እኤአ) ሥልጣን የያዙት፡፡ በምርጫ የተመረጠውና ከፋፋይ የነበሩት ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ሙርሲ በአጭር ቆይታቸውም ቢሆን ከፍተኛ ተቃውሞ ሲደርስበት እንደነበር አሶሽየትድ ፕሬስ ገልጿል፡፡
አልሲሲ ሥልጣን ከያዙ በኋላ እስላሚስቶች በመንገድ ላይ የመቀመጥ የተቃውሞ አድማ አድርገው ነበር፡፡ የግብጽ የደሕንነት ኃይሎች ባካሄዱት ዘመቻ ተቃውሞውን አክሽፈዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሞተዋል፡፡ በዚያኑ ዓመት ምንም ዓይነት ሕዝባዊ ተቃውሞ እንዳይደረግ የደነገገ ሕግ ወጥቷል፡፡ ከሕጉ መውጣት በኋላ ብዙ ርቀት ያልሄዱ ጥቂት የተበታተኑ ተቃውሞች ነበሩ፡፡
አርብ ምሽት በግብጽ ዋና መዲና ካይሮ በታዋቂው የታህሪር አደባባይ በርካታ ተቃዋሚዎች ተሰብስበው ነበር፡፡ ግብጽን ለረዥም ጊዜ የመሩት ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ በ2011 (እኤአ) በአረቡ አብዮት አመጽ ከሥልጣን እንዲወርዱ ያደረገው ሕዝባዊ ተቃውሞና አመጽ ዋና ማዕከሉን ያደረገው በታህሪር አደባባይ ነበር፡፡
የካይሮ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንቲስት ሙስጠፋ ከማል ኤልሰይድ ይህ አሁን የታየው የሕዝብ ተቃውሞ በጣም ጠቃሚ እድገት ነው፤ በአልሲሲ አስተዳደር ላይ የተደረገ የመጀመሪያው ተቃውሞ ሲሆን ወደፊት ወደ በለጡ ተቃውሞዎች ይመራል ብሏል፡፡ በሌሎች የግብጽ ከተሞች አነስተኛ ተቃውሞዎችም ነበሩ። የሜድትሬንያን ከተማ በሆነችው ኤሌክሳንደርያ ጭምር፡፡
የተቃውሞ ሰልፉ የተነሳው በካይሮ የግብጹ ትልቅ የእግር ኳስ ቡድን የሆነው አልሀሌይ እና ተቀናቃኙ ዛማሌክ ግጥሚያ ካደረጉ በኋላ ነው፡፡ የተቃውሞ ሰልፉ መነሻ መሀመድ አሊ በግሉ የተሰደደ የንግድ ሰው ምንም ማስረጃ ሳያቀርብ በሠራዊቱና በመንግሥት ውስጥ ሙስና አለ በሚል በቪድዮ አስደግፎ በሶሻል ሚዲያ ላስተላለፈው ጥሪ የተሰጠ ምላሽ ነው፡፡
መሀመድ ባለፈው ሳምንት በሶሻል ሚዲያ ባሰራጨው ቪዲዮ ግብጽ ውስጥ ኮንትራት የያዛቸው የግንባታ ሥራዎች ቅንጡ ሆቴሎችንና የፕሬዚዳንቱን ቤተመንግሥት በአዲስ መልክ በመስራት እንዲሁም በ2014 የሞቱትን የአልሲሲን እናት መቃብር በማስገንባት ረገድ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ሀብት ብክነትና ሙስና እንዳለ ገልጿል፡፡
ይህ የመሀመድ አሊ ክስና ተቃውሞ የተሰማው ግብጽ የኢኮኖሚ ተሀድሶ በምታደርግበት የኑሮ ውድነቱ የግብጽን የታችኛውን መደብ ክፉኛ ባዳሸቀበት ወቅት ነው፡፡ አልሲሲ ሰሞኑን ተበሳጭተውና በንዴት ጦዘው ለሕዝቡ ባደረጉት ንግግር የቀረበባቸውን የሙስና ክስና ውንጀላ ‹‹የለየለት ውሸት ነው›› ሲሉ አጣጥለውታል። ለግብጽ ሲሉ አዲስ ፕሬዚዳንታዊ ቤተመንግሥት መስራቱን እንደሚቀጥሉ ገልጸው አዲስ ሀገር እየገነባሁ ነው ብለዋል፡፡
አልሲሲ የግንባታ ኮንትራክተሩ መሀመድ አሊ በሶሻል ሚዲያ የለቀቀውን ሙስና አለ የሚል የቪዲዮ ውንጀላ ግብጽን ለማዳከምና ሕዝቡ በሠራዊቱ ላይ እምነት እንዳይኖረው ለማድረግ ሲባል የተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ግብጽ በአሁኑ ሰዓት አራት ዓመታት የዘለቀ በሰሜን ሲናይ ከሚንቀሳቀሰው የእስላሚክ መንግሥት (አይኤስ) ተባባሪ ከሆነው ቡድን ጋር እየተዋጋች ትገኛለች፡፡ የአልሲሲ መንግሥት በአሜሪካና በሌሎችም የአካባቢው ታላላቅ ተጽእኖ ፈጣሪ ኃይሎች ሳኡዲ አረቢያ፤ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችና እስራኤልን በመሳሰሉት ይረዳል፡፡
በግብጽ ያልተጠበቀውና አስደንጋጭ የሆነው አልሲሲ ከሥልጣን ይውረዱ የሚለው የተቃውሞ ሰልፍ ከተካሄደ በኋላ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ (ሂዩመንራይትዎች) የግብጽ ባለሥልጣናት የሰላማዊ ተቃዋሚዎችን መብት እንዲጠብቁ ጥሪ አድርጓል፡፡ የፕሬዚዳንት አልሲሲ መንግሥት የደህንነት ኤጀንሲዎች ሰላማዊ ሰልፈኞቹን ለመበታተን ሲሉ በጭካኔ የተሞላ የኃይል እርምጃ ወስደዋል ሲል የመካከለኛውና ሰሜን አፍሪካ የሂዩማን ራይትዎች ምክትል ኃላፊ ገልጿል፡፡ ባለሥልጣናቱ ማወቅ ያለባቸው ያለፈው ዓይነት ጥፋት እንዳይደገም ዓለም ሁኔታውን በቅርብ እየተከታተለ ሲሆን አስፈላጊ እርምጃዎችን ይወስዳል ብለዋል፡፡
የግብጽ ባለሥልጣናት በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ወዲያው አስተያየት አልሰጡም፡፡ ምክንያቱም አልሲሲ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ስብሰባ ለመሳተፍ ኒውዮርክ እንደነበሩ መንግሥታዊው የዜና ወኪል ሜና ገልጿል፡፡
አልሲሲ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት በ2014 (እኤአ) ነው፡፡ እንደገናም ባለፈው ዓመት አደገኛ ተቀናቃኞችን በማሰር ወይንም ከውድድሩ እንዲወጡ በማድረግ ዳግም ተመርጠዋል ይላል አሶስየትድ ፕሬስ፡፡
ሥልጣን ከያዙ በኋላ በሀገሪቱ ሕገመንግሥት ላይ የተደረገው ለውጥ አልሲሲን እስከ 2030(እኤአ) ድረስ በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ቀደም ሲል በዓመቱ መጀመሪያ በተደረገው ብሔራዊ ሪፈረንደም የተደረጉት ለውጦች ወታደሩ በፖለቲካው ውስጥ ያለውን ሚና ያጎላል፡፡ ተቺዎች እነዚህ እርምጃዎች ወደ አምባገነንነት የሚደረግ ጉዞ ነው ይላሉ፡፡ ቅዳሜ ዕለት ፖሊሱን የሚመራው የግብጽ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የጸጥታ ኃይሎች የሀሳም ንቅናቄ መሪ የሆነ ተጠርጣሪን ገድለዋል ሲል አስታውቋል፡፡ በሰሜን ካይሮ ኤልማታሪያ አቅራቢያ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሁለት የፖሊስ መኮንኖች መቁሰላቸውን ገልጿል፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ በበኩሉ የግብጹ የተቃውሞ ሰልፍ አጠቃላይ መሸበርን ፈጥሯል፤ ከበስተጀርባ ያለው ሰው ድንገተኛና አስደንጋጭ ነው ሲሉ የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባዎች ቪቪያን እና ናዳራሽዋን ከካይሮ ዘግበዋል፡፡
በፕሬዚዳንት አብደልፋታህ አልሲሲ በምትመራዋ ግብጽ ትንሽ ተቃውሞ ብቻ ነው የሚፈቀደው፡፡ ይሄም ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመላው ሀገሪቱ በተበታተኑ ሰልፎች አልሲሲ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ መጠየቃቸው አስደንጋጭና ያልተጠበቀ ሆኗል፡፡
መሀመድ አሊ የ45 ዓመት ዕድሜ ያለው የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮንትራክተርና በከፊል ሰዓቱም ተዋናይ ነው፡፡ ለግብጽ ሠራዊት የተለያዩ ግንባታዎች ሰፊ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ያገኘ ቢሆንም በሕዝብ ሀብት ከፍተኛ ሙስና ይካሄዳል የሚል ክስ በማሰማት በራሱ ጊዜ ስደትን መርጦ ስፔን ገብቷል። ስፔን ሆኖ በሶሻል ሚዲያ ቪዲዮዎችን በመልቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር አልሲሲን በሙስናና በአምባገነንነት በመክሰስ ላይ ይገኛል፡፡
ቪዲዮውን በለቀቀ በሦስት ሳምንት ውስጥ የአልሲሲ ተጻራሪና የተቃዋሚው ጎራ መሪና ዋነኛ ድምጽ ተደርጎ እየወሰደ ነው፡፡ ይህ ሰው ከዚህ ቀደም አይታወቅም፡፡ ምንም ዓይነት ቦታ ላይ ተጽእኖ አልነበረውም፡፡ የማይታወቀው ሰው ያሰራጨው ቪዲዮ ነው ሕዝቡ አልሲሲን ተቃውሞ አደባባይ እንዲወጣ ያደረገው፡፡ የተቃውሞው መነሻ የሆነው አሊ ሌሎች የተቃውሞ ሰልፎች እንዲቀጥሉ ያደርግ እንደሁ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ከምንም ተነስቶ ወደ ታላቅ ታዋቂነት ሽቅብ የተወነጨፈው ይህ ሰው በመንግሥት ውስጥና ከመንግሥት ውጭ ባሉ አቅም ባላቸው ክፍሎች ላይ ያሳደረው ተጽእኖ አብሮ የሚታይ ነው፡፡
በመካከለኛው ምሥራቅ ዴሞክራሲ ላይ ያለው የምርምር ተቋም ፕሮጀክት ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አሚሀውት ሆርኔ አስገራሚ ነው ብለውታል። ይህ ሰው ማነው? ከእነማን ጋር ነው የሚገናኘው? በአሁኑ ሰዓት ይህን ተቃውሞ ይዞ ለመነሳት ያበቃው ምክንያት ምንድነው? በትክክል ከውስጥ ሰዎች ጋር ቅርብ ግንኙነት እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ ከማን ጋር ነው በቀጥታ የሚገናኘው? ማነው ግለሰቡ? የሚለው ጥያቄ ገና ያልተመለሰና መመለስ ያለበት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ለተቃዋሚዎች መነሳሳትና ድምጽ ማሰማት መበረታታትን የፈጠረው ሚ/ር አሊ ነው፡፡ ፍርሀታቸውን የገፈፈ መነሳሳትን ያበረታታ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ አሊ መሀመድ በካይሮ ሠራተኞች በሚኖሩበት ብሎክ ሰፈር አካባቢ ነዋሪ ሲሆን የአሁኑ የመሀመድ አሊ ቪዲዮ አይደለም ዋናው የተቃውሞው እውነተኛ ምክንያት፤ ሕዝቡ አጋጣሚን ነበር የሚጠብቀው፤ እርምጃ መውሰድ ይፈልጋል ሲል ለአሶሽየትድ ፕሬስ ገልጿል፡፡
በአይን ማስረጃዎችና በሶሻል ሚዲያው ሪፖርት መሠረት ቅዳሜ ዕለት በቀይ ባሕሯ ከተማ ስዊዝ 200 የሚሆኑ ተቃዋሚዎች የላስቲክ ጥይት ከተኮሱ የፖሊስ መኮንኖች ጋር ተጋጭተዋል፡፡ መዲናዋ ካይሮ ላይ ምንም ዓይነት የተቃውሞ ሰልፉን የማስቀጠል ሁኔታ አልታየም፡፡ ፖሊስ የዕለቱ ዕለት የታህሪር አደባባይን ተቆጣጥሮታል፡፡ ከ8 ዓመታት በፊት በአረቡ ስፕሪንግን አብዮት የግብጽ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን ለማውረድ የተሰበሰበው በዚሁ የታህሪር አደባባይ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2012
ወንድወሰን መኮንን