የመጽሐፉ ስም፡- 666 ሳይንሳዊ ምስጢራት
ግብረሶዶማዊነት፣ዕፅ…
ደራሲ፡- ዐብይ ይልማ
የገጽ ብዛት፡- 212
ዋጋ፡- 180 ብር
መጽሐፉ እንደዋና ሃሳብ አድርጎ የሚያወሳው ምዕራባውያኑ በዚህ ዘመን የሚታዩትን ሁሉ ከሰው ልጅ የማይጠበቁና አውሬያዊ ተግባራትን ሊከውኑ እንደሚገባ ዓላማ ይዞ የተነሳ ነው።
ዋነኛ ዓላማቸው በሰይጣናዊ ኃይማኖት የሚመራውን አዲሱን የዓለም መንግስታዊ ስርዓት (The New world order)በመመስረት ዓለምን ጠቅልለው “ለሉሲፈር” ለማስገዛት መሆኑን እንዳንረሳ መጽሐፍ ያሳስባል።
ይህ መጽሐፍ የተለያዩ ጸሐፍትን ዋቢ ያደረገ ነው። የ666 ምስጢራዊ ቡድን አባላት ይህንን ለማሳካት ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች ዋነኞቹ ከዓለም አቀፍ እስከ አፍሪካ ሲልም እስከ ኢትዮጵያ ድረስ የሚያከናውኑዋቸው ሚስጥራዊ ስራ ናቸው። ቀጣዩ ወጥ የዓለም መንግስት (የ seiguchi Masashi) “መንግስትና ፖለቲካ” የሚለው የ2016 ዓ.ም መጽሐፍት እንደሚናገረው ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ የሚቀረጽ ስለመሆኑ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በብዙ ትንታኔ ቀርቧል።
ፈላጭ ቆራጭ የዓለማችን ወጥ መንግስት መሀከለኛው አካል እጅግ ጠንካራና የተወሳሰበ ነገር ግን ብዙም የፖለቲካ ነጻነት የማይኖራቸው ቅርንጫፎች ያሉት ነው። የግለሰቦችም ነጻነት መሀከለኛው የዓለም መንግስት በፈቀደው አጥር ዙሪያ የሚያሽከረክር ነው።
እንደዚህ ዓይነቱን ፈላጭ ቆራጭ ዓለምን የሚጠቀልል አስተዳደራዊ ዘዴን የሉላዊነት መጨረሻ (The Final Stage of Globalazation) በሚል የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ጆሴፍ ኒዬ ሰይመውታል። ይህንን አካሄድ ሮማዎች ለምሳሌ በአንደኛው እና በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ይጠቀሙበት ነበር። ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ ግሪኮች ዓለምን ያስተዳድሩበት የነበረው ሔለናይዜሽን የተሰኘው ስልት በዚህ ዘመን ደግሞ ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ በግሎባላይዜሽን ቅርጽ ተመልሶ መምጣቱን መጽሐፉ ያስነብበናል። ይሁን እንጂ ግሎባሊዝም ለ666 መንግስት መንገድ ጠራጊ እንጂ ፈጻሜው እንዳልሆነ የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ማብራራታቸውን ያስነብባል።
ሉተር ኤች ማርቲን በ2003 ዓ.ም በጻፈው መጽሐፍ ጠቅሶ እንዳስነበበው ግሎባላዜሽን ዓለምን ለሰይጣናዊ መንግስት አሳልፎ ለመስጠት የሚሰራበት አካሄድ ከሄለናይዜሽን ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ለማሳመን እንደ አመክንዮ ያቀርበዋል።
ለዚያ ነው የጥንቱ old world order ይሄኛው ደግሞ The New World Order የተባለው። ይህ የምራባውያን አዲሱ ስልት የ666 ማለትም የቁጥር ስልት ነው። እንደየተባበሩት መንግስታትና እንደ የአውሮፓ ህብረት ያሉ ተቋማት የዚህ ሰንሰለት አካላት እና መንገድ ጠራጊዎች መሆናቸውን ይኸው አሜሪካ የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ይተነትኑታል።
“የተባበሩት መንግስታት በአዲስ የዓለም ስርዓት ውስጥ (The UN in a new world order) የተሰኘው የያሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ብሩስ ሩሴት የጻፉት መጽሐፍ እንደሚነግረን፣ ይህንን ወጥ መረብ በመረብ የተቆላለፈ የ666 የዓለም መንግስትን ለመመስረት በየጊዜው የተለያዩ ተግባራት እየተፈጸሙ ይገኛሉ።
ከእነዚህ መካከል ከ1950ዎቹ የኮሪያ ጦርነትና ከ1990ዎቹ የፋርስ ባህረ ሰላጤው ጦርነት አንስቶ ያሉ ትላልቅ አጀንዳዎች በመንግስታት ደረጃ እንዲሁም አሁን በኢትዮጵያና በሌሎች አፍሪካ አገራት ውስጥ የሚተገበሩ እንደ ግብረ ሶዶማዊነት ያሉ ልቅ ተግባራት ደግሞ በግለሰቦችና ማህበራሰቦች ደረጃ ማስፋፋትና የመሳሰሉት የ666 ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።
Bloodlines of illuminati ከተሰኘው የፍሪትዝ ስፕሪግሜር እ.አ.አ የ1995 መጽሐፍ እንደምንረዳው የ666 ምስጢራዊ ምዕራባዊ ቡድን አካላት ዋነኛ ዓላማቸው የአለም ሕዝብ በአንድነት ሰይጣናዊ መናፍስቶችን እንዲያመልክ አሳልፎ በመስጠት በምትኩ እነርሱ የገንዘብ ስልጣንና ኃይልን ከሉሲፈር መንግስት ተቀብለው ዓለምን መግዛት ነው።
ይህንን የሚያደርጉት ግን ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ጥንትም በዚህ ለሰይጣን አሳልፎ የመስጠት ዘዴ ዓለምን መግዛት የምራባውያኑ ግለኛ ባህል ነበር። የሚገርመው ግን አንድም ጊዜ ይህ ስልታቸው እስከ ቀኝ ግዛት ዘመናቸው ድረስ ኢትዮጵያ ላይ አለመስራቱ ነው። በቅኝ ግዛት ዘመን አገራትን ተቀራመቱ እንጂ ተስማምተው በአንድነት መግዛት ግን አልቻሉም ነበር። የጥንቱ በአንድ ወጥነት የመግዛት ስልታቸው የመጨረሻው ከሮማ ስርወ መንግስታዊ ስርዓት ማብቃት ጋር አክትሞ የነበረ ነው። ከዚያም ከ1 ሺ 700 እስከ 2000 ለሚጠጉ ዓመታት ግን የኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ በክርስትና እንዲሁም ከአንድ ሺ 400 ዓመታት በላይ ደግሞ የነብዩ ሙሐመድ አስላማዊ ትዕዛዛት ትምህርቶች በእስልምና ዓለም ላይ ተጽዕኖ ፈጥረው ቆይተዋል።
ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ To End all wars የሚለው የቶማስ ጄ ኖክ መጽሐፍ እንዳሰፈረው ጸረ-ክርስትና የሆኑ ተቋማት በይፋ መደራጀት ጀመሩ። ከዚያ በፊት በተለይ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሚስጥር ይንቀሳቀሱ ነበር። እነዚህ አካላት በእስልምና ስለተቀመጡትም ሆነ በክርስትና ውስጥ ስላሉት አስተምሮዎች እንዲሁም ስለማናቸውም ስነ ምግባር ግብረ ገብን ስለሚያስተምሩ ሀሳቦች መስማት አይፈልጉም። ይልቅ ይላል መጽሐፉ ሰው እንደፈለገው ልቅ ሆኖ በአደንዛዥ ዕፅ፣ ግብረ ሶዶማዊነት፣ ሱሰኝነት፣ ፆታን ማቀያየር፣ ገንዘብን እስከ ማስመለክ፣ ከእንስሳት ጋር እስከሚደረግ ፍትወት በሚያደርሱና በመሳሰሉ አስተምህሮቶች የሚመራውን የሉሲፈር ሰይጣናዊ ሐይማኖትን መስበክ ዓላማቸው ነው። በዚህም ስልት ዓለምን ወደ አንድ ወጥ ስርዓት የማምጣት ስራ መከወን፣ በስተመጨረሻ ሰይጣንን ማስመለክ ዋነኛ ግባቸው ነው። ይህንንም ከሮማዎች Old World Order ከአሮጌው የቀጠለውን The new World Order አዲሱ የዓለም ስርዓት ብለው ሰይመውታል።
የመጽሐፉ ዓላማ የአስተምሮ እና የመረጃ አሰጣጥ ስልቱ 666 የሚለውን ቁጥር እንደሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ በእጃችን እየተከናወነብን እንዳለ አንዳች ነገር ቀምሰን መርምረን እንድንረዳው ማድረግ ነው። እንጂ የ666 የሚለውን ቁጥር ስታነቡ ገና የዛሬ ምናምን ዓመት እንደሚገለጥና ፊት ለፊት ወደኛ እንደሚመጣ ቀንዳም ሰይጣን እና አውሬ እያሰብን ዛሬን እንዳንታለል ማድረግ መሆኑን መጽሐፉ በግልጽ አስቀምጧል። ምክንያቱም 666 አሁን እየተታለልን፣ ብዙሐን እየሞቱ፣ አዕምሮዋቸውን እያጡበት፣ እየተሰቃዩበት ያሉበት የቁጥር ኮድ ነው።
እርግጥ ነው “666” ሰይጣናዊ ቁጥር ነው። ይህንን 666 ቁጥር በመልካም ጎኑ የሚያስተዋውቅ፣ የሚሰብክ ማንኛውንም አካል አጋንንታዊ ዓለማቱን የተቀበለና በዚያ ለመኖር የተወሰነ መሆኑን እንዳንዘጋ የሚያነቃ መጽሐፍ ነው።
ይህ ሙያዊ አስተያየት ሳይሆን አስተውሎት ነው። በዚህ መጽሐፍ ላይ ውብ የሆነ የቋንቋ አጠቃቀም፣ ጥልቅ የሆኑ ትውልድን የማዳን ሃሳቦች፣ የነብስ ጩኽት፣ ቅስቀሳ እና የስሜት ትስስሮሽ፣ ከፍ ባለ የስነ ጽሑፍ ይዘት የተጻፈ መጽሐፍ ነው። ስለዚህ ማለት የሚቻለው መጽሐፉ በተከሸኑ ገላጭ ቃላት የተጻፈ ነው፤ ስለዚህን መጽሐፉን እንዲያነቡት እጋብዛለው!። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2012
አብርሃም ተወልደ