ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። በሀገር መኖር፤ የሚቻለው ወጥቶ መግባት፤ ተምሮ እራስንና ቤተሰብን መርዳት፤ ሰርቶ መክበር፤ ወልዶ መሳም፤ ዘርቶ መቃም የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። ሰላም በሌለበት ሁሉም ነገር ከንቱ ነው። እንኳንስ ለሌላው ለራስም መሆን አይቻልም።
በሰላሟና በጸጥታዋ የምትታወቀው ሀገራችን ዛሬ ሰላሟ ላይ ጥላ እያጠላ ነው። በብሔር፤ በሃይማኖት፤ በጎሳ ተቧድነን የሰላም አየሩን አደፍርሰነዋል። ለራሳችንም ሰላማችንን አጥተን ሌሎችንም ሰላም እየነሳን እንገኛለን። በማያልቅና አታካች በሆነው እሰጥ አገባችን ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅን መርጠናል። ከመወያየት ይልቅ መዘላለፍን አስቀድመናል። ከመደማመጥ ይልቅ መጯጯህን ልምድ አድርገነዋል።
እናም ይህን አለመረጋጋት እና የሰላም ዕጦትን ወደ ቀድሞ መቻቻል እና የተረጋጋ የማህበረሰብ ሰላምን ለመመለስ ሁሉም የየድረሻውን ሊወጣ ይገባል። ሙዚቀኛ በሙዚቃው፣ ሰዓሊው ብሩሹ እና ቀሉሙን ከሸራው ጋር በማዋደድ፣ ደራሲው በየትኛውም የጽሑፍ ውጤቱ፣ ቲያትረኛው… በአጠቃላይ ማንኛውም ግለስብ እንዲሁም የኪነ ጥበብ ባለሙያው በተሰጠው መክሊት ስለ ሰላም ሊዘምር ይገባል።
ታዲያ እኛ ለዛሬ ስለሰላም በስዕል እየዘመሩ ማህበረሰቡን እንዴት ወደ ተረጋጋ ኑሮው እና ወደ ቀደመው ጉርብትናውና አንድነቱ መመለስ ይቻላል የሚለውን ከዘረፉ ባለሙያዎች ጋር ለመምከር ወደድን።
ሰዓሊ ብሩክ ውቤ ከስዕል ምንነት ተነስቶ ነገሩን እንዲህ ያስረዳል። ስዕል በስሌዳ ላይ በቀለም ይሁን በጠመኔ አለዚያም በእርሳስና በሌላ ነገር ተሰርቶ በዓይን በማየት የሚገነዘቡት ጥበብ ነው። ለዓይንና ለመንፈስ ከሚሰጠው አርካታ ሌላ የአንድን ህብረተስብ ብሎም የኪነ ጥበቡን ስው አመለካከት ይጠቁማል ተብሎ ስለሚታመን በዘመናዊ ዓለም የተለየ እንክብካቤ የተሰጠው የሰው ልጅ ጥበባዊ ተግባር መሆኑን ወጣቱ ሰዓሊ ያስረዳል። የዚህ አይነት ጥበብ የሚሰራው ደግሞ ሰዓሊ ይባላል።
የተፈሪ መኮንን የስነጥበብ ትምህርት ክፍል ፍሬ እንደሆነ የሚናገው ሰዓሊ ብሩክ «የስዕል ትምህርት የሰውን፣ የእንስሳን፣ ያገርን፣ የደመናን በጠቅላላው የሥነ ፍጥረትን መልክና ባሕርይ አጥኝ ሆኖ የራሱን ስሜት በግሉ እየፈጠረ በቀለምና በልዩ ልዩ መሳሪያዎች በጠፍጣፋ ነገር ላይ ስርቶ ማውጣትን፤ በቅርጻ ቅርጽ ትምህርት ደግሞ አንደ ስዕሉ የተዘረዘረውን ሀሳብ ከጠፍጣፋ ነገር ላይ በመስራት ፈንታ ጠንካራ ከሆነ አካል ላይ ከድንጋይ፣ ከእንጨት፣ ከዝሆን ጥርስ ወይም ከነሐስ ቅርጽና መልክ ቀርጾ ማውጣት ነው።» በማለት ያስረዳል።
ሰዓሊ ብሩክ ከስመጥር ገብረ ክርስቶስ ደስታ እንደተዋሰ በጠቀሰው ሀሳብ ደግሞ «በዘመናዊ አቅድ ስዕል ራሱ ሐሳብ ነው። የአንድ ነገር ሁኔታ የአንድ ነገር ትርጉምና ስሜት ነው…። ዛሬ ስው ራሱን ብቻ መመልከት ትቶ ዓለም ከብዙ ርቀት ከብዙ በኩል ሲታይ ምን ዓይነት ስሜት እንደሚስጥ አለም አቀፋዊና ዘላለማዊ የሆነውን ነገር በመተርጎም በዓይን የሚታይ የቀለም፣ የመስመርና የቅርጽ ሙዚቃ ለመፍጠር ይጥራል።»
ታዲያ እንዲህ እና እንዲያ የተባለለት ስነ ስዕል ለአገር ግንባታ፣ ሰላም እና የቀደመውን አድነት ለመመለስ መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ያስታወሰው ሰዓሊ ብሩክ “ስዕል የትናንት ታሪክን የምታጠናበት፣ ዛሬን የምትገልጽበት፣ ወደ ፊት የምትገምትበትና በስራዎችህ የምታወጣበት ነው” የሚውለው ሰዓሊው፤ ስዕል የማህበረሰቡ የታሪክ ማስተላለፊያ፣ እሴቱን ለትውልድ ማሻገሪያ ነው ብሏል።
በዚህ ረገድ እኔንም ጨምሮ ኢትዮጵያዊያን ሰዓሊያን የጥንቶችም ሆኑ የዛሬዎች አብሮነትን፣ ታሪክን፣ ባህልን፣ በቀለማት ቅርጾች ቀምረው በአንድ የስዕል ሰሌዳ ላይ ለእይታ እንዲመች አድርገው ሃሳቦችን እንደሚያስቀምጡ እመክራለሁ። አገራዊ ሰላምና አንድነት ለማምጣትም ለኪነ ጥበቡ ዘርፍ በመንግስትም በኩል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጿል።
ሌላው በተለያዩ አገራት እንዲሁም በአገር ውስጥ የስዕል ስራዎቹን በማቅረብ የሚታወቀው እና ስለ ሰላም አውርቶ የማይጠግበው አገር ወዳዱ የስዕል ባለሙያ ሰዓሊ እያዩ ጌትነት አንዱ ነው። ሰዓሊ እያዩ እንደሚለው ስለሰላም ዋጋ ስናስብ ከፈረሱ አገራት ልንማር ይገባል። ስለስዕል ከማውራታችን በፊት በሰላም አጦት ከፈረሱት አገራት ልንማር ይገባናል፤ በአካል ከአየሁት በመገናኛ ብዙሃን ከሰማሁት ለአንባቢው ይጠቅም ዘንድ ይህንን ልበል።
ቀድሞ በታሪካቸው ታላቅ በፖለቲካም ማህበራዊ እንዲሁም በኢኮኖሚያቸው ጠንካራ የነበሩ አገራት አሁን እንደ አጽም የቆሙ ህንፃዎች መገበያያዎች፣ መዝናኛዎች፣ ያምልኮ ስፍራዎች፣ መንግስታዊም የግሉም ተቋማትና ቢሮዎች የሚገለገሉባቸውና አገልግሎት ሰጪ ስንመለከታቸው በሆኑ ሰዎች ሁሌም ሞቅ ደመቅ ያሉ መሽቶ እስኪነጋ ባዶ የማይሆኑ በህያዋን ድባባቸው ዘመናትን የዘለቁ ቤት፣ ሰፈር መንደርና ሀገር እንደነበሩ የሚናገረው ሰዓሊ እያዩ፤ ሰዎቹ ሀገራቸው ሀገር እንድትሆን ሰላምና ፀጥታ የሕግ የበላይነትም ተከብሮባት ታድግ ዘንድ መንግስታቸውም ለሰብአዊ ደህንነታቸው ጥበቃን ለማድረግ ጊዜው የሚጠይቃቸውንም እድገቶች ለማምጣት አቅም እንዳያንሰው ጥረው ግረዋል። ካፈሩት ሀብት ግብር እና ታክስ በመክፈል ኃላፊነታቸውን ከመወጣት በተጨማሪ ጉልበትንም ሆነ እውቀት ባለመሰሰት ከቀደሙት ቤተሰቦቻቸው የተረከቧትን ሀገር ለልጆቻቸው የተሻለች አድርገው ለማስተላለፍ በማሰብ የሚፈለጉበት ቦታ ሁሉ ጥረታቸው ሳይቋረጥ ሲቀጥል ነበር።
ሀብትና ዜጋውም ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጥፋትን እንዲሁም የጥፋት ድርጊት አድራጊን ለመጠበቅና ለመከላከል የጦር ኃይል መገንባት የጦር መሳሪያ ማስታጠቅ የሀገርና የመንግስቶች ግዴታ ነው። ለዚህም ህዝብ ተጠቃሚነቱን በማሰብ ሀብት ብቻ ሳይሆን የሰራዊቱ አካልና ጠባቂዎቹ እንዲሆኑ ልጆቹን ወዶ ልኳል።
ሰዓሊ እያዩ ይናገራል ህፃናት፣ እናቶች አጠቃላይ የሀገሪቷ ዜጎች ሰላማዊ የሆነ ዘወትር የለመዱትን እንቅስቃሴና አኗኗር ለሰከንድ እንኳ ማንም አያደናቅፍብኝም ብለው በማመናቸው በየእለት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ይታትራሉ። ጭራሽ የራሳቸው የሆኑ ሰዎች እዚህና እዚያ የሚባል ጎራ ፈጥረው እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ሁሉን ነገር የሚያርድ የቦንብ እሩምታ፣ ድምፁን አጥፍቶ ከወዴት እንደመጣ ሳይታወቅ መላ አካላቸውን ቆራርጦ የሚጥላቸውን፣ የመተንፈሻ ጡንቻዎቻቸውን በመመረዝ እያፈነ ከመኖር ወደ አለመኖር የቀየራቸውን ሰቅጣጭ የስቃይና ሞት መሳሪያ እየተሸከሙ አምጥተው ቁልቁል የለቀቁባቸውን አይተናል። ከርቀትም ያሶነጨፉባቸውን አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች ከአደጋ እንደሚጠብቋቸው እንጂ ለአፍታም የሆነውን በህዝባቸው ላይ ያደርጉታል ብለው አስበውትም አያውቁ። ግን ያላሰቡት ሆኖ በምድር ሳይቀር ታስቦበት በተወነጨፈ ከሰማይም በወረደ እሳት አረሩ በተአምር የተረፉ በደመ ነብስ እግራቸው ወደመራቸው በመሸሽ ስደት ብቸኛ አማራጫቸው ሆነ።
ሰዓሊ እያዩ አሁንም ይናገራል በሶሪያ የተለያዩ ትንንሽ መንደሮች ሳይቀር የህንፃዎች አፅም የውስጣቸው ችግርን እንደመነሻ ተጠቅመውና እረዳታችሁ ነን በማለት እጃቸውን ያስገቡ የውጪ ሀገራት እንዴት የጦር መሳሪያዎቻቸውን ሞክረውባቸዋል። ታሪካዊ ቅርሶቻቸውን ጨምሮ ሀብታቸውን በጭካኔ እንደሰበሰቡባቸው የሚታወቅ ነው።
ሰላም ላፍታ ከእጃቸው የወጣ ሀገሮች የተከበረውንና ከምንም በፊት ተመራጭ የሆነውን መቻቻል፣ ትብብርና፣ ትእግስት ሲጠፋባቸው ምን ያክል ዋጋ ቢከፈል እንኳ በቀላሉ መረጋጋትና ሰላምን መመለስ አለመቻልን በአሁኑ ጊዜ ለአለም የምታስተምረው ሶሪያና ህዝቦቿ ቀዳሚ ሆነዋል∷ ከዚህ መከራና ቁጣ የሚጠብቃቸው እስከ አሁኗ ሰከንድና ደቂቃ እንዴት ይጠፋል ብሎ መጠየቅም የዋህነት ነው።
ሶሪያን ከአይናቸው ስር አውሎ ንፋስ እንዳገኘው ጭድ ብትንትኗ ሲወጣና ውሀ ውስጥ እንደገባ ጨው ስትጠፋ የሚመለከቱ ሌሎች አገሮችስ በየቀኑ ቤንዚን እና እሳት የማገናኘታቸውን ልክፍት የሚያረክስ መድህን እንዳይገኝ የሚያደርገው የሀገራት የሀብትም ሆነ ኃይል ሚዛንን ለማስጠበቅ የሚደረግ ፉክክር መቼም ቢሆን ከዚች ምድር አይጠፋምና እራሱን አሳልፎ የሰጠ ህዝብና ሀገር እራሱን አጠፋ ከማለት ውጪ ሌላ ማለት አይቻልም ይላል ሰዓሊ እያዩ።
የእኛም ዕጣ ፋንታ ካልተጠነቀቅን እንዲሁ ነው የሚሆነው። ሰዓሊ እያዩ ይናገራል እኔም ባለሁበት ሙያ ለጊዜያዊ ጥቅም ብዬ ጠብ ጫሪ፣ ተንኳሽ፣ የህብረተሰቡን እሴት የሚያፈርሱ ስዕሎችን አልስልም። ይልቅ የትኛውንም ስዕል ስስል ከአገሬ ሰላም እና ከህዝቤ ጥቅም አንጻር እያየሁ ነው።
ከአገር የሚበልጥ የለም፤ ለሙያ አጋሮቼ እንዲሁም በየትኛውም የኪነ ጥበብ ሙያ ውስጥ ለተሰማሩ ሙያተኞች የምመክረው ይህንኑ ነው። የስዕልን ስራ ጨምሮ የትኛው የኪነ ጥበብ ስራ ሲሰራ አገር የአገርን ሰላም የህዝብን ተስፋ የሚጨምሩ ስራዎች መሆን አለባቸው። እኔም በተለያዩ ጊዜ ሰላምን የሚዘክሩ ስራዎች ሰርቻለው፤ አሁን እቀጥላለሁ፤ አላቆምም።
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ልዩነትን የማይፈጥር ሙዚቃ፣ ስዕል፣ ፊልምና ሌሎች የጥበብ አይነቶችን መስራት፣ አንድነት፣ ፍቅርና የጋራ ታሪክ ላይ ያተኮሩ ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው መልክት አስተላልፏል። እኛም የተሰጠንን መክሊት ለአገር አንድነት በማዋል የቀደመውን ጉርብትናና አንድነት ለመመለስ እንጠቀም እንላለን!! መልካም ዕለተ ሰንበት።
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2012
አብርሃም ተወልደ