ተወልደው ያደጉት ከጋምቤላ ብሄራዊ ክልል ዋና ከተማ 182 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ጎክ በሚባል ወረዳ ነው፡፡ ከ1ኛ አስከ 6ኛ ክፍል በቀዬአቸው የተማሩ ሲሆን፤ ቀጣይ ህይወታቸውን ከሀገር ውጪ በመውጣት አሳልፈዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት መኖሪያቸውን በአሜሪካን ሀገር ያደረጉ ሲሆን፤ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የሚል ስያሜ ያለው ተቋም መስርተው በትውልድ አገራቸው የሰብዓዊ መብት እንዲከበር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ የዓለም አገራት በመዘዋወርም ስለ ኢትዮጵያውያን የዜግነት ክብር ተሟግተዋል፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መስራች ከሆኑት እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪነታቸው ከበሬታ ከሚቸራቸው አቶ ኦባንግ ሜቶ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው ያቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ለመሆን ያነሳሳዎት ምንድን ነው?
አቶ ኦባንግ፡- በሰብዓዊ መብት ላይ እሠራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ የገጠመኝ ጉዳይ ነው የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ እንድሆን የገፋፋኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምን ነበር ያጋጠሞት ጉዳይ?
አቶ ኦባንግ፡- እንደ እ.አ.አ በ2003 ጋምቤላ ውስጥ ግጭት ተፈጥሮ ነበር፡፡ እናም በዚህ ግጭት ከ400 በላይ የሚሆኑ የአኝዋክ ብሄር ተወላጆች ተገደሉ፤ 44 የሚሆኑ የክልሉ አመራሮች ታሰሩ፡፡ እንግዲህ ይህ ሁኔታ ነው ውስጤን ነክቶኝ ግፍና በደል ስለሚፈጸምባቸው ሰዎች ተቆርቋሪ መሆን አለብኝ ብዬ እንድወስን መነሻ የሆነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግጭቱ በምን ምክንያት ነበር የተፈጠረው?
አቶ ኦባንግ፡- በወቅቱ አንድ የነዳጅ ዘይት የሚያስስ የማሌዢያ ኩባንያ በክልሉ ተሰማርቶ ሳለ በክልሉ መንግሥትና በፌዴራል መንግሥት መካከል መግባባት ባለመፈጠሩ ነበር ግጭቱ የተቀሰቀሰው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እና በወቅቱ የጀመሩትን ትግል ዳር አድርሰው ነበር?
አቶ ኦባንግ፡- አዎን በመጠኑም ቢሆን መንግሥት ጥፋቱን እንዲያምን አድርጌያለሁ፡፡ በአቶ ከማል በድሪ የሚመራ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ተቋቁሞ ውጤቱን ይፋ እንዲደረግ ጫና ፈጥሬያለሁ፡፡ በውጤቱም ምንም እንኳን የሞቱት ሰዎች ቁጥር አንሶ ቢገለጽም መንግሥት በመከላከያ አማካኝነት የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ማመን ችሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ተግባር ተሰማርቼ ውጤታማ ሆኛለሁ ብለው ያምናሉ?
አቶ ኦባንግ፡- ከሞላ ጎደል ውጤታማ የሆንኩባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ያሳካኋቸውን ጉዳዮች ሳስብ ደስ ይለኛል፡፡ በሌላ በኩል እዚህ ሀገር ላይ ይፈጸሙ የነበሩት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሁሉ እልባት እንዲያገኙ ባለማድረጌ ቅር ይለኛል፡፡ አሁንም በየአካባቢው በብሔራቸው ምክንያት ጥቃት የሚደርስባቸውን ዜጎች ሳስብ ብዙ መሥራት እንደሚገባኝ ይሰማኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በውጭ ሀገር በነበሩበት ጊዜ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከእስር የማስፈታት ሥራ ሠርተዋል ይባላል፤ እውነት ነው ?
አቶ ኦባንግ፡- አዎን በየቦታው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እየደወሉልኝ ችግራቸውን ሲነግሩኝ ቢያንስ ከ20 ሀገሮች በላይ በመሄድ ልደርስላቸው ችያለሁኝ፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ሜክሲኮ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ግብፅ፣ ኖርዌይ፣ ስውዲን በመሳሰሉት አገሮች በመሄድ ስለኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ድምፄን አሰምቻለሁ፡፡ ብዙዎቹንም ከሚደርስባቸው ሰብዓዊ መብት ጥሰት ታድጌያቸዋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በማን የተቋቋመ ድርጅት ነው? ዓላማውስ ምንድነው?
አቶ ኦባንግ፡- ሰው መብቱ መከበር አለበት፤ ሰው በሰውነቱ እንጂ በብሔሩ መታየት የለበትም በሚል እሳቤ የተደራጀ ነው፡፡ ለዚህ መነሻ የሆነን ደግሞ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሀገር አንድነት ሳይሆን በብሔር ላይ የተመሰረተ ስብሰባና መቀራረብ ሲያደርጉ በመመልከታችን እኔና ጓደኞቼ ተነጋግረን የመሰረትነው ድርጅት ነው፡፡ ድርጅታችን ሰዎች በፍቅር፣ በሰላምና በአንድነት መንፈስ ተሳስረው እንዲኖሩ ለማድረግ የሚሠራና ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚያይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ቀና አስተሳሰቦችን የሚያበረታታና የሚያስረጽ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ድርጅቱ ከተመሰረተ ስንት ዓመት ሆነው? ምን ምን ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል?
አቶ ኦባንግ፡- ከተመሰረተ 11 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ጋር በመሆን በሀገራችንና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እየተገናኘን መክረናል፡፡ በርካታ ሥራዎችንም ሠርተናል፡፡ አሁንም ለውጡን ለማገዝ ጥረት እያደረግን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለለውጡ ምን ዓይነት እገዛ እያደረጋችሁ ነው?
አቶ ኦባንግ፡- በተለያዩ ክልሎች እየተዟዟርን ስለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትከአመራሮች፣ ከወጣቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ሃሳብ ተለዋውጠናል፡፡ አማራ፣ ሀረሪ፣ ጋምቤላ ክልል እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሄደናል፡፡ በቀጣይም ወደ አስራ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ሄደን ከተማሪዎችና ከመምህራን ጋር ለመነጋገር ዕቅድ ይዘናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ትግራይ ክልል አልሄዳችሁም? አቶ ኦባንግ፡- አልሄድንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለምን?
አቶ ኦባንግ፡- ስልክ ደውለን ፕሮግራም እንዲይዙልን አድርገናል፤ እናም ወደፊት እንሄዳለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ ኢትዮጵያ ከስንት ዓመት በኋላ ተመለሱ?
አቶ ኦባንግ፡- ከአስራ ስድስት ዓመት በኋላ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምን ምን ለውጥ አዩ?
አቶ ኦባንግ፡- ሁለት ዋና ዋና ለውጦችን አይቻለው፡፡ አንደኛው የህዝብ ብዛት ነው፤ ሌላው ህዝቡ ላይ ያየሁት ተስፋ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያን መምራት ከጀመሩ ወዲህ አብዛኛው ሰው በተስፋ እየኖረ እንዳለ ካነጋገርኳቸው ሰዎች ተረድቻለሁ፡፡ ውጭ ሀገር በነበርኩበት ወቅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አድጓል ሲባል እስማ ነበር፡፡ ከኤርፖርት ወደ ከተማ ሳመራ አዳዲስ ሕንፃዎች ተገንብተው አይቻለው፡፡ አንዳንዶቹ በጅምር የቀሩ ናቸው፡፡ በሰዎች መካከልም ልዩነት እንዳለ ታዝቤያለሁ ጥቂት ባለሀብቶች እና ብዛት ያላቸው በድህነት ያሉ ሰዎች እንዳሉ ተገንዝቤአለሁ፡፡ እንደተባለው የባቡር አገልግሎትና ሕንፃዎች ስለተገነቡ እድገት አለ ማለት አይቻልም፡፡ አበዛኛው ህዝብ አኗኗሩ ዝቅተኛ ነው፡፡ ህዝቦች ጥሩ ምግብ መመገብ ሲችሉ ፣ ጥሩ ቤት ውስጥ መኖር ሲችሉና ህይወታቸውን ማሻሻል ሲቻል ነው እድገት አለ የሚባለው፡፡ ይህን ግን አላየሁም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዶክተር ዐቢይን አመራርና የለውጡን ሂደትስ እንዴት ገመገሙት?
አቶ ኦባንግ፡- እንደአየሁት ሰዎች አሁን ነፃነት አግኝተዋል፡፡ ዶክተር ዐቢይ በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጡ ሰው ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት ሰዎች ፈርተው ነው የሚኖሩት አሁን ግን እንደልባቸው ይነጋገራሉ፤ እኔን ጨምሮ፡፡ እኔ እዚህ አገር ከመጣሁ በኋላ ልክ ወጭ ሀገር እያለሁ እንደምናገረው የልቤን ነው የማወራው፡፡ ምንም ፍራቻ የለብኝም፡፡ እናም ዶክርተር ዐቢይ ያመጡት ነገር ካለ ለሰዎች ነፃነትንና ጥሩ ተስፋን መስጠታቸው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እና ነፃነት አለ ነው የሚሉት?
አቶ ኦባንግ፡- በእውነት እልሃለው በጣም ነፃነት አለ፡፡ ኢንተርናሽናል ኦርጋናይዜሽን አጌነስት ጆርናሊዝም እንዳረጋገጠው በኢትዮጵያ ውስጥ ከባለፉት አስራ ሦስት ዓመታት ወዲህ አንድም ጋዜጠኛ ያልታሰረበት ዓመት ቢኖር ይህ ዓመት ነው የሚል መረጃ ማውጣቱ አንድ ማሳያ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከልክ በላይ ነፃነት መሰጠቱ ሰዎችን ልቅ እንዲሆኑ አድርጓል የሚሉ አካላት አሉ፤ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ኦባንግ፡- እውነት ነው ሰዎች በስሜታዊነት እየተገፋፉ ህግን የሚቃረን ሥራ ሲሠሩ ተመልክቻለሁ፡፡ ሰውን ገድሎ መስቀል፣ በእሳት ማቃጠል ፣ ማፈናቀል፣ ንብረት ማውደም… ወዘተ እነዚህ ሁሉ ግን የብሔር ፌዴራሊዝሙና የፀረ-ለውጥ ኃይሉ ውጤቶች እንጂ ነፃነት ያመጣቸው ሊሆኑ አይችሉም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት 27 ዓመታት በሀገሪቱ የነበረው የብሔር ፖለቲካ ሀገሪቱን ወደ መበታተን ጫፍ አድርሷታል የሚሉ አሉ፤ እርሶ ምን ይላሉ ?
አቶ ኦባንግ፡- እውነቴን ነው የምልህ እኔም በዚህ ሃሳብ እስማማለሁ፡፡ ለ27 ዓመታት ሀገርን የማፍረስ ሥራ ነው የተሠራው፡፡ ብሔርን ነፃ ለማውጣት የተደራጁ ቡድኖች ናቸው ሀገርን ሲመሩ የነበሩት፡፡ ዶክተር ዐቢይ ከመመረጣቸው በፊት እኮ ሀገሪቱ የመፈራረስ አደጋ ውስጥ ነበረች፡፡ ስርዓቱ ራሱ ሀገርን የሚከፋፍል ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይሄ ሁሉ ሰው የተፈናቀለው እኮ በብሔር ተኮር ፖለቲካ ምክንያት ነው፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ የመንግሥት ሠራተኞች በክልል ተወስነው የሚሠሩባት ሀገር ሆናለች፡፡ እኔ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት 17 መምህራን በትምህርት ቤቱ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የጋምቤላ ተወላጅ የነበረው አንድ መምህር ብቻ ነው፡፡ ሌሎቹ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ነበሩ፡፡ ከወለጋ፣ ከትግራይ፣ ከወላይታ፣ ከጎጃም፣ ከባሌ ሌላው ቀርቶ ኤርትራዊያኖችም ነበሩ፡፡ የብሔር ልዩነት አልነበረም፡፡ አንድ ህዝብ ሆነን ነው የኖርነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ግን ይህ መንፈስ ጠፍቷል፡፡ ልዩነትን በሚያጎላ መልኩ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እየተባለ ይከበራል፡፡ ተማሪዎች በትምህርት ቤት የኢትዮጵያን ሳይሆን የክልላቸውን መዝሙር እንዲዘምሩ ነው የተደረገው፡፡ ስለአንድነት ሳይሆን ስለመለያየት ሲሰበክ ነው የኖረው፡፡ መታወቂያ ላይ ሳይቀር የብሔር ጉዳይ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡
ስለኢትዮጵያዊነት፣ ስለሀገር ፍቅር፣ ስለአንድነትና ስለሰንደቅ ዓላማ አይሰበክም፡፡ ታድያ ይህ ሁሉ ተሠርቶ መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያን የመበታተን አደጋ ቢገጥማት ምን ያስገርማል? ይህ ሁሉ ሀገርን የመካድና የመናድ ድርጊት የተፈጸመው ለግል ጥቅም ከማሰብ ነው፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ ተሳስተናል ይቅርታ ይደረግልን ማለት ሲገባቸው ዛሬም ትክክል እንደነበሩ መናገራቸው ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ለውጡን ለማደናቀፍ እዚያና እዚህ እሳት እየለኮሱ ህገ-መንግሥቱ ይከበር እያሉ ቁማር ለመጫወት መፈለጋቸው ነው የሚገርመው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን በራስ ቋንቋ የመማር ፤የመሥራትና የመዳኘት ዕድል መፈጠሩ ይህ ሥርዓት ካመጣቸው መልካም ነገሮች አንዱ ተደርጎ ይታያል፤ እርሶ ምን ይላሉ?
አቶ ኦባንግ፡- እኔ መልካም ነው አልልም፡፡ ምክንያቱም ይህ አሠራር ኢትዮጵያን ሲበታትናት እንጂ ሲያጠናክራት አላየሁም፡፡ እኔ የምስማማው አንድ ወይም ሁለት ካልሆነም ሦስት ቋንቋዎችን ብሔራዊ ቋንቋ በማድረግ በህዝቦች መካከል ያለውን መራራቅ ማስወገድ በሚለው ነው፡፡ ህዝቡ የሚያግባባውን ቋንቋ መምረጥ አለበት፡፡ በአማርኛ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይግባባል፤ ኦሮምኛም ብዙ ሰዎችን ያግባባል፤ እነዚህ ቋንቋዎች ብሄራዊ ቋንቋ መሆን ይችላሉ፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ እንግሊዝኛንም ማካተት ይቻላል፡፡ ኦሮምኛ ለኦሮሞ ብቻ መሆን የለበትም። ለሁላችንንም የሚጠቅመን ቋንቋ ነው፡፡ ለምን መሰለህ ከብዙ ኢትዮጵያዊያን ጋር ያግባባሀል፡፡ ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር በአኗኗራቸው ይቀራረባሉ፡፡ ለምሳሌ ከጋምቤላ፣ ከሲዳማ ፣ ከአማራ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ከአፋር፣ ከሶማሌ ፣ ከጉራጌ ፣ ከሀረሪ … ወዘተ፡፡ ስለዚህ ይህ ቋንቋ ምን ያህል ለኢትዮጵያ ህዝብ ቅርብ እንደሆነ መመልከት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እና አሁን ያለው የብሔር ፌዴራሊዝም መቅረት አለበት ይላሉ?
አቶ ኦባንግ፡- እንግዲህ ይህን የብሔር ፌዴራሊዝም ያመጡት ነፃ አውጪዎች ናቸው፡፡ አሱንም እንኳን እንደሚሉት አይተገብሩትም፡፡ ለምሳሌ አናሳ፣ ታዳጊ ፣ አጋር የሚል አጠራር አላቸው፡፡ ይህ እራሱ ስድብ ነው፡፡ ከእነዚህ አካባቢ የሚበቅሉ ሰዎች የፈለገውን ያህል እውቀት ቢኖራቸው ሀገር የመምራት መብት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ፌዴራሊዝሙ እውቅና የሚሰጠው ኢህአዴግን ለመሰረቱት ዋና ዋና ድርጅቶች በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የሀገራችን ፌዴራሊዝም፡፡ እናም የአጋር ድርጅቶች ኢትዮጵያዊነት ከሌሎች ያንሳል ማለት ነው፡፡ መስፈርቱ ምን እንደሆነ እንኳን አይታወቅም፡፡ የሶማሌ ክልልን ያህል የቆዳ ስፋት ሳይኖራቸው የኢህአዴግ አባል የተባሉ አሉ፡፡ አሁን ግን ዶክተር ዐቢይ ይህን አሠራር የሚያስቀሩት ይመስለኛል፡፡ ለውጡ ብርሃን ነው የምለው አንዱ ለዚህ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጋምቤላ አካባቢ ውጥረት ከሚታይባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው? ለምን ይመስልዎታል?
አቶ ኦባንግ፡- ምክንያቱም ቀደም ሲል የነበረው አመራር በአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ላይ ያተኩራል እንጂ ስለህዝብ አይጨነቅም፡፡ እናትና አባት ልጆቹን በአንድ ዓይን ነው ማየት ያለበት፡፡ ፌዴራል መንግሥት ግን እንዲህ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ግጭቶች ሲፈጠሩ ፈጣን ምላሽ አይሰጥም፡፡ ጋምቤላ ለደቡብ ሱዳን አዋሳኝ እንደመሆኑ የዚያች ሀገር የሁከት ንፋስ ወደ ጋምቤላ ሊነፍስ ይችላል፡፡ ስለዚህ በውስጥም ሆነ በውጭ ተጽዕኖ ምክንያት ጋምቤላ አልፎ አልፎ ትታወክ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያዊነትን አጠንክረው እንደሚያቀነቅኑና በዚህም ጽኑ አቋም እንዳለዎት ይታይል፤ ይህ ከምን መነጨ?
አቶ ኦባንግ፡- ኢትዮጵያዊነት በልቤ ውስጥ የተተከለ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያውነቴን ከማንም ያገኘሁት አይደለም፡፡ የመሀል ሀገር ሰውም የዳር ሀገር ሰውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት መቶ በመቶና ዘጠና በመቶ አይባልም፡፡ ማንም ከማንም የተለየ ቦታ አይሰጠውም፡፡ ቁም ነገሩ ዳር እና መሀል መሆን ሳይሆን ቅን ልቦናን ይዞ ለወገንም ሆነ ለሀገር የሚበጅ ሥራ መሥራት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሰብዓዊ መብት ጥሰትን አስመልክቶ ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተላለፈውን ዘጋቢ ፊልም አይተውታል?
አቶ ኦባንግ፡- አይቼዋለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምን ተሰማዎት?
አቶ ኦባንግ፡- በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ልብ ይሰብራል፡፡ ወገን በወገኑ ላይ እንዲህ ዓይነት ግፍ ይፈጽማል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እኛ እኮ ቀደም ብለን ስንወተውት የነበረው ይህ መረጃ ስለነበረን ነው፡፡ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ አስደንጋጭና እንግዳ ነገር እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ እኛ ስለሰብዓዊ መብት ጥሰት ስናወራ መንግሥት ፀረ-ልማቶች ናቸው፤ አሸባሪዎች ናቸው ይለን ነበር፡፡ አሸባሪው ግን ማን እንደነበር ዛሬ ተገልጧል፡፡ ስማኝ ወንድሜ ብርሃንና እውነት አንድ ናቸው፡፡ ብርሃን ባለበት ጨለማ አይኖርም፡፡ ክፉዎች፣ ጨቃኞችና ግፈኞች የጨለማ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ምድር ብርሃን እየፈነጠቀ ነው፡፡ ስለዚህ ጨለማው ለብርሃን ቦታውን ሰጥቶ ሄዷል፡፡ ግን ጥሎ ያለፈው ጸያፍ ተግባር ዜጎችን የጎዳ ብቻ ሳይሆን የሀገርንም ገጽታ ያበላሸ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከምን አንጻር ነው የሀገርን ገጽታ የሚያበላሸው?
አቶ ኦባንግ፡- ምን መሰለህ ይህች ሀገር የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ብዙ ጥረት እያደረገች ነው፡፡ የውጭ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ደግሞ የሀገሪቱ ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ፈጣሪን ይፈራሉ በሚባሉ ህዝቦች ሀገር እንዲህ ዓይነቱ ዘግናኝ ድርጊት መፈጸሙ ወደዚህ ሀገር ለመምጣት በሚያስቡ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለማንኛውም በዜጎቻችን ላይ ከልክ ያለፈ ሰብዓዊ ጥሰት የተፈጸመ መሆኑ ቢያሳዝነንም በ27 ዓመት የዘረኝነት አገዛዝ ሲሰቃዩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ነፃ መውጣታቸው ግን ያስደስታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ‹‹ሰርቆ መንደላቀቅ – ግፍ ሠርቶ መደበቅ አይቻልም›› በሚል የሰጡት ወቅታዊ መግለጫ ምን ስሜት ፈጠረብዎ ?
አቶ ኦባንግ፡- መግለጫው ህዝቡ እያነሳ ላለው ጥያቄ መንግሥት ትክክለኛ መልስ የሰጠበት ነው፡፡ የመንግሥት አቋም በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ አካላት የትም ቢሰወሩ ለፍርድ እንደሚቀርቡ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቶናል፡፡ መግለጫው ጥቃት የተፈጸመባቸውን ዜጎቻችንንና መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያጽናናል ብዬ እገምታለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሌብነትና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ስለዋሉ ሰዎች ምን ይላሉ?
አቶ ኦባንግ፡- በህግ ጥላ ስር እስካሉ ድረስ ብቀላ ሳይፈጸምባቸው እንደ አንድ ታራሚ መብታቸው ሊጠበቅላቸው ይገባል ነው የምለው፡፡ ማረሚያ ቤት ሰው ከስህተቱ የሚማርበት እንጂ መከራና ስቃይ የሚያይበት ቦታ መሆን የለበትም፡፡ እነርሱ እኮ ዛሬ የታሰሩት ትናንት በንጹሐን ላይ በፈጸሙት ወንጀል ነው፡፡ ይህንን መድገም ደግሞ መልሶ እነርሱን መሆን ነውና ተምረው እንዲጸጸቱ ማድረግ ይገባል፡፡ አንድ ሰው ትልቅም ትንሽም ወንጀል ሊሠራ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት መጥፎ ወንጀል ሠርተሀል ተብሎ በተለየ መልክ ሊንገላታ አይገባውም፡፡ አንድ ሺ ሰው የገደለም አንድ ሰው የገደለም በማረሚያ ቤት ውስጥ መብታቸው እኩል ነው፡፡ የሚለያዩት ፍርድ ቤት በሚሰጣቸው ብያኔ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ አካላት በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ስም የማጥፋት ዘመቻና ጥቃት ነው ይላሉ፤ በዚህ አባባል ይስማማሉ?
አቶ ኦባንግ፡- በፍጹም አልስማማም፡፡ ይህ አባባል ያስገርመኛል፡፡ ማነው የአንበሳውን ድርሻ ይዞ የነበረው ካልን ህወሓት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በህወሓት ውስጥ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ተጠርጣሪዎች ሊኖሩ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ወንጀለኞች ግን በየትኛውም ክልል ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ተቋማት አሉ፡፡ ምርመራ እየተደረገባቸው ያሉት ተጠርጣሪዎችም ከተለያየ ብሔር የመጡ ናቸው፡፡ ቅድም እንዳልኩት ግን ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱ ከፍተኛ ተጠያቂነት ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ዕርምጃው ብሔር ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን ወንጀለኛ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ አሁን እኮ ለውጥ ላይ ነን፡፡ ለውጥ የመጣው ደግሞ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሰዎችን በዘር እየለዩ ለማጥቃት አይደለም፡፡ ‹የብሔር ጥቃት እየተፈጸመብን ነው› የሚለው ማደናገሪያ አባባል እኮ ተጠርጣሪዎች ከተጠያቂነት ለማምለጥ የዘየዱት ስልት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተልዕኮውን ፈጽሞ ነበር ብለው ያምናሉ?
አቶ ኦባንግ፡- በፍጹም አላምንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንዴት?
አቶ ኦባንግ፡- ይህ እኮ ግልጽ ነገር ነው፡፡ ሁሉም ወንጀሎች ሲፈጸሙ የነበረው በመንግሥት ተቋሞች እየተመሩ ነው፡፡ ማን ነው ግለሰቦችን እያደነ ይዞ ሲያሰቃያቸው የነበረው? የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እኮ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም የመንግሥት ጉዳይ አስፈጻሚ ከመሆን በዘለለ የንጹሐንን ድምፅ ሲያስተጋባ አልሰማሁም፡፡ ያ ቢሆንማ ኖሮ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝና አሳፋሪ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይፈጸምም ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን በፌስ ቡክ ገጽዎ የመጀመሪያው እርቅ በጋምቤላ አኝዋክ መንድር ይጀምራል ሲሉ አስፍረው ተመልክቻለሁ፤ ምን ለማለት ነው ?
አቶ ኦባንግ፡- ልክ ነው፤ እኔ መጀመሪያ አኝዋክ አካባቢው ካሉት ወንድሞቹ ጋር ልዩነቱን አስወግዶ በፍቅርና በሰላም መኖር ይገባዋል ያልኩት ከማውቀው አካባቢ ልነሳ ብዬ ነው፡፡ ለመላው ኢትዮጵያዊ ብሄራዊ እርቅ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብሄራዊ የእርቅ ኮሚሽን እየተቋቋመ መሆኑ እየተነገረ ነው፤ እርስዎ በኮሚቴ ውስጥ አሉበት እንዴ?
አቶ ኦባንግ፡- የለሁበትም ፤ ብጠየቅ ግን የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፡፡ ነገር ግን እኔ አሁን በየክልሉ እየሄድኩኝ የምሠራው ሥራ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ሌላስ ለውጡን በምን መርዳት ትፈልጋላችሁ?
አቶ ኦባንግ፡- ወንጀል ሠርተው ከሀገር የሚወጡ ሰዎችን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንዲጠየቁ እናደርጋለን ብለናል፡፡ ለዚህም ሰዎች ጥቆማ እንዲደርጉልን እንፈልጋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በኋላ ተመልስው ወደ ውጭ ይወጣሉ፤ ወይስ ኑሮዎን እዚሁ ያደርጋሉ?
አቶ ኦባንግ፡- ከዚህ በኋላ ውጭ ሀገር መኖር አልፈልግም፡፡ ለውጡን በማገዝ የኢትዮጵያን እና የህዝቦቿን ተስፋ ሊያለመልሙ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ እየሠራሁ የበኩሌን አስተዋጽኦ አበረክታለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አመሰግናለሁ !
አቶ ኦባንግ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
ኢያሱ መሰለ