አዲስ አበባ፡- ደህንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ የባህላዊ ህክምና ሥርዓት በመዘርጋት ከመደበኛው የጤና አገልግሎት ጋር ማቀናጀት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ጤናና ሥነ ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት ገለፀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ ተስፋዬ ትናንት በተቋሙ መሰብሰቢያ አዳራሽ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ ባለሥልጣን በባህል መድኃኒት ሕክምና ረቂቅ ፖሊሲና ስትራቴጂ ዙሪያ በተዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ እንደተናገሩት፤ የባህላዊ ህክምና ሥርዓትን ለመደገፍና ለማደራጀት ምርምሮችንና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማሳደግና ከመደበኛ የጤና አገልግሎት ጋር እንዲቀናጅ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
‹‹ማንኛውም መመሪያ ይሁን አዋጅ የሚወጣው በፖሊሲ ተደግፎ ነው›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂው የባህል ህክምና ማነቆ የተባሉ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ እንደሚታሰብ ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር ኤባ ገለፃ፤ የባህል ህክምና ላይ ያተኮሩ ዕውቀቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የቆዩት በቃል ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የህክምና ሥርዓቱን የተመለከቱ መረጃዎች ተመዝግበውና ተጠብቀው እንዲቆዩ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኢንስቲትዩቱ፣ የባህል ህክምና መድኃኒቶች በላቦራቶሪ አጥንቶ አሥር መድኃኒቶችን ማግኘቱን ጠቅሰው፤ ይሁንና መድኃኒቶቹን ለተጠቃሚው ለማድረስ ግን በፋብሪካዎች የሚወጡበት መንገድ እንደሚቀር ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስፋው ደበላ በበኩላቸው፤ የባህል ህክምና ከግብርና እና ከአካባቢ ጥበቃ የተያያዙ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ደንና ዕፅዋትን ከመጠበቅ ጎን ለጎን እንደ ህክምና ግብዓት የሚጠቀምበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ አቶ መንግሥተአብ ወልደአረጋይ በበኩላቸው፤ የባህል መድሀኒትን በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች እየተጠቀሙበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የባህል መድኃኒቱም ከባህልና ከእምነት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ተቀባይነት እንዳለውም አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ መንግሰተአብ ገለጻ፤ የዓለም ጤና ድርጅት በባህል ህክምና ዙሪያ ሀገሮች ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና የሕግ ማዕቀፍ መንደፍ እንዳለባቸው ያዛል። በባህል ህክምና ዙሪያ ተቀናጅቶ መሥራትም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ እንደተገለፀው፤ ከአፍሪካውያን 80 በመቶው ያህሉ የባህል ህክምና ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያም በተመሳሳይ 80 በመቶ ህዝብ ተጠቃሚ ነው፡፡ እንደ ቻይና፣ ህንድና ጋና የመሳሰሉ ሀገራት ከዘመናዊ ህክምና ጎን ለጎን በባህላዊ ህክምና ባለሙያዎችና ግብአቶች እንዲሁም በሆስፒታል ደረጃ የህክምና ማዕከል እንዳላቸው በማሳያነት ተጠቅሷል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ