
አውነት ነው የፌዴራሊዝም ስርዓት በኢትዮጵያ መተግበር ከጀመረ 28 ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ የትግበራ ዓመታትም በልማቱና በሰላሙ መስክ ለሀገራችን በጎ ውጤትን አስገኝቷል። ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ እንዲማሩና እንዲዳኙ በማንነታቸው እንዲኮሩና በህላቸውን እንዲያጎለብቱም ምቹ መደላድል ፈጥሯል።
ይሁንና በተለይም ከለውጡ በፊት በነበሩ 27 የኢህአዴግ ዘመናትና ዛሬ ራሳቸውን የፌዴራሊዝም ጠበቃ ነን ባዮች የአመራር ዘመን ፌዴራሊዝሙ ለፖለቲካ መነገጃነት ከመዋሉም በላይ ከልብ ሳይሆን ከአንገት በሆነ ሁኔታ ለይስሙላ ይተገበር የነበረ መሆኑም የአደባባይ ሀቅ ነው።
የፌዴራሊዝም መሠረተ ሃሳብ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ባህልና ቋንቋቸውን የሚያሳድጉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው። በሌላ አነጋገር ፌዴራሊዝም ማለት ከአውቅልሃለሁ ባዮች ነጻ ሆኖ ራሰን በራስ የማስተዳደር ሙሉ መብትን መጎናጸፍ ማለት ነው።
ከዚህ መሠረታዊ ሁኔታ ተነሰተን በተለይም ከለውጡ በፊት በነበሩ 27 ዓመታት የነበረውን የኢትዮጵያን የፌዴራሊዝም አተገባበር ብንመለከት ለይስሙላ ክልሎች ቢቋቋሙም አመራር ይሰጣቸውና ይታዘዙ የነበረው በማዕከላዊነት ከተያዘ አመራር ነበር።
ክልሎች ራሳቸው ሊወስኑበት በሚገባ ጉዳይ ሌላ አካል ወስኖ በግልባጭ ያሳውቃቸው እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታና የአደባባይ ሀቅ ነው። የክልል አመራሮች ሹመት ይሰጥ የነበረውም በክልሉ ህዝብና አስተዳደር ምርጫና ይሁንታ ሳይሆን በሌላ አካል መልካም ፈቃድ አንደነበር ብዙዎች የሚመሰክሩት ሀቅ ነው።
ዝርፊያን ታሳቢ ያደረጉ ትልልቅ ጣልቃ ገብነቶች በክልሎች እንደነበሩም በተጨባጭ ማስረጃ የተረጋገጠ እውነታ ነው። በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ክልሎች የተደረጉ የመሬትና የማዕድን ሀብቶች ቅርምትን በማስረጃነት ማንሳት ይቻላል። የቤኒሻንጉል ክልል ፕሬዚዳንት በአንድ ወቅት ከጋዜጣችን ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ በክልሉ በነበረው የመሬት ክፍፍል የክልሉ ሃላፊዎች ምንም ዓይነት ስልጣን እንዳልነበራቸው ያወሱበት ሁኔታ ከላይ ያነሳነውን ሀሳብ እውነታነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በሶማሌ ክልል በህዝብ ላይ ለመስማት የሚከብድ ግፍና መንግሥታዊ ውንብድና ሲፈጽም የቆየው አመራርም የዚሁ ህገወጥ ጣልቃ ገብነት ውጤት መሆኑም አይዘነጋም።
በስመ ተቆርቋሪነትና እኔ አውቅልሃለሁ ባይነት የክልሎችን መሬት የፌዴራል መንግሥቱ እንዲያስተዳድር የተደረገበት ሁኔታም ሲተገበር የቆየው ፌዴራሊዝም ለፖለቲካ ንግድና ለዝርፊያ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ያልዘለለ መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳየናል። በዚህም መነሻነት ሰፋፊና ጥብቅ ደኖች እንዲወድሙ፣ በህገ ወጥ ኢንቨስትመንት ዜጎች እንዲፈናቀሉና አንዳችም ፋይዳ ለሌለው ኢንቨስትመንት የአዲስ አበባን አምስት እጥፍ የሚሆን መሬት ያለ ክልሎች ይሁንታ ኢንቨስተሮች እንዲሰጥ የተደረገበት ሁኔታ እንደነበርም አይዘነጋም።
በቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ፣ ኤጄቶና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ይደረጉ የነበሩ የለውጥ ትግሎች ዋነኛ ማጠንጠኛ ጥያቄ እውነተኛ ፌዴራሊዝም ይተግበር፣ ጣልቃ ገብነት ይወገድ፣ ዝርፊያ ይቁም የሚል እንዲሆን ያደረገውም ፌዴራሊዝሙ መርሁን ለቆ ለዝርፊያና ለህገወጥ ጣልቃ ገብነት በመዋሉ ነበር። ስለሆነም ከለውጡ በፊት ሲተገበር የቆየው ፌዴራሊዝም በአውነት ለዜጎች መብትን ለማጎናጸፍ ሳይሆን የራስን ጥቅም ለማስጠበቅና ለዘርፊያ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እንደነበር አያጠራጥርም።
በመራር የህዝቦች ትግልና ለህይወታቸው ሳይሳሱ ለህዝብ ጥቅምና መብት መከበር ሲሉ መስዋዕት መሆንን በመረጡ አመራሮች ቁርጠኝነት የለውጥ አመራሩ ሥልጣኑን ከያዘ በኋላ ግን ይህ ሁኔታ ከመሰረቱ ተቀይሮ ፌዴራሊዝም ከፖለቲካ መነገጃነት ወደ እውነተኛ ትግበራ ተሸጋግሯል።
በዚህም ክልሎች ያለምንም ጣልቃ ገብነት ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትና የራሳቸውን ጉዳይ በነጻነት የሚወስኑበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። አሁን ላይ ማንም ኃይል በክልሎች ጉዳይ እንደፈለገው ገብቶ የሚፈተፍትበትና እኔ አውቅልሃልሁ የሚልበት ሁኔታ ላይመለስ ተቀብሯል።
ይሁንና ለውጡ ይህን መሰል መብት ባጎናጸፈበት፣ ራሰን በራስ ለማስተዳደር ምቹ ሁኔታ በተፈጠረበትና ፌዴራሊዝሙ በትክክለኛ መንገድ እየተተገበረ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የተለያዩ ኃይሎች ሰባራና ስንጣራ ምክንያቶችን እየመዘዙ ለውጡን ለማደናቀፍ ሌት ተቀን ሲረባረቡ እየተስተዋለ ነው።
ይህንን ጉዳይ የበለጠ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ ቀድሞ ፌዴራሊዝሙን ለጣልቃ ገብነትና ለዝርፊያ አመቻችተው ሲጠቀሙበት የነበሩ ሃይሎች የፌዴራሊዝም ጠበቃ ሆነው መታየታቸው ነው። እውነት ለመናገር እነዚህ ኃይሎች የለውጥ አመራሩ ፌዴራሊዝሙን እየናደ ነው የሚሉት እውነቱ ጠፍቷቸው ሳይሆን ይህ ጉዳይ ህዘብን በለውጥ ሃይሉ ላይ ለማነሳሳትና በዚህም መነሻነት ለውጡን ለማደናቀፍ ምቹ ዕድል መሆኑን አጢነው ነው።
ለማንም ግልጽ እንደሆነው የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦችና ሀዝቦች መናኅሪያና የብዝሃነት ማዕከል ለሆነችው ኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አዋጭና ተመራጭ የሆነ የአስተዳደር መንገድ ነው። የለውጥ አመራሩም ይህንን እውነታ ተቀብሎ እንደበፊቱ ለይስሙላ ሳይሆን የአውነት ለመተግበር በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል።
ስለሆነም ህዝባችን ፌዴራሊዝምን ለፖለቲካ ቁማርና ለጣልቃገብነት መጠቀሚያ ሊያደርጉ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን እኩይ ሴራ በመገንዘብ ነቅተንባችኋል አንቀበልም ሊላቸውና ለአገራችን ሰላምና ዕድገት አማራጭ የሌለውን የለውጥ አመራር በሙሉ ልብ መደገፉን ሊቀጥልበት ይገባል።
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2012