ኢትዮጵያን ለረጅም ዓመታት በተለያየ ሙያና የሃላፊነት ስፍራ ካገለገሏት ትልቅ የሀገር ባለውለታዎች አንዱ የሆኑት የቀድሞው ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ታህሳስ 5 ቀን 2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ትናንት አስክሬናቸው በሚሊኒየም አዳራሽ የክብር ሽኝት ከተደረገለት በኋላ፤ ዘላቂ ማረፊያቸው ወደሆነው ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን በማምራት ስርዓተ ቀብራቸው ተካሂዷል፡፡
ቤተሰቦቻቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እንዲሁም በርካታ የፌዴራልና የክልል አመራሮች፣ አምባሳደሮች፣ የእምነት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ወጣቶች በስፍራው ተገኝተው ነበር፡፡
በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ የተነበበው የህይወት ታሪካቸው እንደሚያመለክተው፤ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ታህሣስ 19 ቀን 1917 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ከአባታቸው ከግራዝማች ወልደጊዮርጊስ ሉጫ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ወሰንየሽ መኩሪያ ተወልደዋል፡፡ በልጅነታቸው በአዲስ አበባ አማኑኤል ቤተክርስቲያን የቤተክህነት ትምህርት ከተማሩ በኋላ፤ በ1926 ዓ.ም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ ዘመናዊ ትምህርት ቀስመዋል፡፡
የሰላም አምባሳደር፣ የአረንጓዴ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ አርበኛው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ለተፈጥሮ ያላቸው ክብር ከሰው ልጆች የማይተናነስ ነበር፡፡ በዚህ የተነሣ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በ1956 ዓ.ም አካባቢ የደን ሕግ በአገሪቱ እንዲወጣ ማድረግ ችለው ነበር፡፡ ሰብዓዊ በሆኑ ድርጊቶች እና ለሕብረተሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በተግባር በማስተማር አርዓያ የነበሩ መሆናቸው በህይወት ታሪካቸው ተገልጿል፡፡ በእርሳቸው የዓይን ብርሃን የሌሎችን አይን ሊያበሩ በአገሪቱ ለሚገኘው የዓይን ባንክ ብሌናቸውን ከሞቱ በኋላ እንዲለገስ ቃል ሲገቡ የቀደማቸው አልነበረም፡፡
ጃንሜዳ አካባቢ ተወልደው በማደጋቸው በልጅነታቸው በአቬሽን ሥራ ላይ ለመሰማራት በር እንደከፈተላቸው ይነገራል፡፡ ምክንያቱም ‹‹ጃንሜዳ የቀድሞው አውሮፕላን ማረፊያ ሥለነበረ ነው›› ተብሏል በተነበበው የህይወት ታሪካቸው፡፡
በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ግርማ ከተራ ሠራተኛነት ጀምረው እስከ አገሪቱ ርዕሰ ብሔርነት የደረሱ ናቸው፡፡ በዚህም የጠንካራ ሥራ ወዳድ ዜጋ ተምሳሌት መሆናቸው በህይወት ታሪካቸው የተጠቀሰ ሲሆን ሥራን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት የቤት ወለል ፕላስቲክ በማንጠፍ ሥራ ነው፡፡ በእርሳቸው ድንቅ ሥራም ነባሮቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለት ሕንጻዎች የወለል ንጣፍ እንደተዋበ ተነግሯል፡፡
በሚሊኒየም አዳራሽ በነበረው አሸኛኘት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደገለጹት ‹‹ዛሬ እዚህ ቦታ የተሰባሰብነው አንድ ቀን የሀገራችን ታሪክ በሚጻፍበት ጊዜ በዘመናችን አሉን ከምንላቸው የሀገራችን ታላቅ መሪዎች አንዱ ሆነው የሚወሱትን ፕሬዚዳንት ግርም ወልደ ጊዮርጊስን ለመሰናበት ነው፡፡ ክቡር ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በእነዚህ ዓመታት ሁሉ የኢትዮጵያን ጥሪ ተቀብለው አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደረጉ እንዲሁም በተግባር ያሳዩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡››
ፕሬዚዳንት ግርማ በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ በመሳተፍና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን በማገዝ ያከናወኑት ተግባር ሁላችንም የምንኮራበት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ‹‹የመልካም ዜጋ ምሳሌነ ታቸውንም አሳይተውናል፡፡ ሰላምን ሰብከው ስለሰላም ደክመዋል፤ ይቅርታና ምህረት ያላቸውን ዋጋ አስተምረውናል፡፡ እነዚህ ሁሉ የፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ተግባራት ለእኛ ኩራት ለእርሳቸው ደግሞ የዘለዓለም መታሰቢያዎቻቸው ሆነው ከእኛ ጋር እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነን›› ብለዋል፡፡
‹‹ዛሬ እዚህ ተሰባስበን ለመጨረሻ ጊዜ ታላቅና ልባዊ አክብሮታችንን በመግለጽ ስንሰናበታቸው ይህንን ከእርሳቸው የተማርነውን የሀገር ፍቅር ቅንነት በንጹህነትና በታማኝነት ማገልገልን ፤ ምንም እንሁን ፤ ከየትም እንምጣ የአንድ ሀገር ልጆች መሆናችንን በማሰላሰል ሊሆን ይገባል›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ከመቃብር በላይ የሚቀረው ስም ነው እንዲሉ፤ ክቡር ፕሬዚዳንት ግርማ በአነጋገራቸው፣ በቁም ነገራቸው፣ በለዛ አንደበታቸው በሀገራቸው ህዝቦች ዘንድ ያተረፉት ፍቅርና ከበሬታ ለዘለዓለም የሚታወስ ይሆናል በማለት ገልጸዋል፡፡
የክቡር ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን ህልፈት አስመልክቶ ወጣት ብርሀኑ መገርሳ፤ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ሀገራቸውን ለአስራ ሁለት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉና በተለይም የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በመሥራት ለአዲሱ ትውልድ ምሳሌ መሆን የቻሉ ታላቅ ባለታሪክ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከወጣትነት እድሜያቸው ጀምረው እየተመናመነ የመጣው የሀገራችን ደን ስላሳሰባቸው በአረንጓዴ ልማት ላይም ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆነው በመሥራት ለኢትዮጵያና ለህዝባቸው የማይረሳ ታሪክ ጥለው ማለፋቸውን በሀዘን ስሜት ገልጿል፡፡ በመጨረሻም መልካምነታቸውን ስንቃችን አድርገን እኛም የበኩላችንን መልካም ሥራ ሠርተን እንለፍ ሲል ሀሳብ ሠጥቷል፡፡
የተከበሩ የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን እንደገለጹት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል ጽኑ እምነት ያላቸው ነበሩ፡፡ ለሕዝባዊ አገልግሎት ከእርሳቸው በላይ ምሳሌ የሚሆን ሰው ማግኘት ላሳር ነው ብለዋል፡፡
ልጃቸው አቶ ሰለሞን ግርማ በበኩሉ፤ አባታቸው መልካም አርዓያ እንደነበሩ ገልጾ፤ በህይወት ዘመኑ በርካታ ቁም ነገር ለአገራቸው የሰሩ ባለውለታ መሪ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2011
በሙሀመድ ሁሴን