ለጥቁሮች ነፃነት ቆርጠው በመታገል፤ በማታገላቸው፤ ለፍትሕና ነፃነት በመፋለማቸው በነጮች ተወንጅለው ወሕኒ መወርወራቸው ከደቡብ አፍሪካዊው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ጋር ያመሳስላቸዋል። ነገርግን እንደ ማንዴላ አሳሪ-አሰቃዮቻቸውን ይቅር ባይ ግን አይደሉም። ሥልጣን በቃኝንም አያውቁም።
እንደ ክዋሚ ንኩሩማ የጥቁር ብሔረተኝነትን አራማጅ ናቸው። እንዲያውም የሕይወት ታሪካቸው ፀሐፊዎች እንደሚሉት የፖለቲካ ሥልት፤ የታጋይነት-ስሜት ጥቁር ብሔረተኝነትን የተማሩት ከክዋሚ ንኩሩማ እና ከንኩርማዋ ጋና ነው። እኚህ ሰው የምዕራባውያንን መርሕ መቃወምና ማውገዛቸው እስከህልፈተ ህይወታቸው ድረስ የዘለቀ ሲሆን፤ የ95 ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ፣ ለ37 ዓመታት ዝምባብዌን የመሯት ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ ጳጉሜን 1/2011 ዓ.ም ምድራዊ ተልዕኳቸውን አጠናቅቀው ይህችን ዓለም ከተሰናበቷት ዛሬ ድፍን አንድ ሳምንት ሞላቸው፡፡
በአወዛጋቢነታቸው እና በቆራጥ መሪነታቸው ይታወቃሉ። የቀድሞው የዝምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ፤ ሙጋቤ በዝምባብዌ የነፃነት ታሪክ ውስጥ ከነፃነት በኋላ የመጡ የመጀመሪያው መሪ ብቻ አይደሉም። የነፃነቱ ጉዞ ጠንሳሽ ጭምር እንጂ፤ “የውጪ አልጋ የውስጥ ቀጋ” የሚለውን የአፍሪካውያን የወል ካባ ያወለቁ ሳይሆኑ ከጅምሩም ያልለበሱ መሪ ነበሩ፤ ሮበርት ሙጋቤ፤
እውቁ ፖለቲከኛ ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ የዛሬ ሳምንት የህክምና ርዳታ እየተደረገላቸው በነበረበት በሴንጋፖር ህይወታቸው ማለፉን የወቅቱ የአገሪቱ መሪ እና የትግል አጋራቸው ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ አርድተዋል፡፡ “የዝምባብዌ የነፃነት አባት እና ታጋይ ማለፋቸውን ስንናገር በከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ወድቀን ነው” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በቲዩተር ገፃቸው በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ለዝምባቡያውያን አረዱ፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ “ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ ለአገራችን እና ለመላው ጥቁር አፍሪካውያን ነፃነት ያበረከተውን አስተዋፅኦ ታሪክ አይዘነጋውም” ሲሉም የዚያን የነፃነት ታጋይ አይረሴ እና አይበገሬ የትግል ገድል በአጭሩ አስፍረዋል፡፡ ሁሌም የጥቁር የበታችነትና መረገጥ የእግር እሳት የሆነባቸው ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር የካቲት 21 ቀን 1924 ከርዕሰ መዲናዋ ሀራሬ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው ኩታማ አካባቢ ነበር ይህችን ም ድር የተቀላቀሉት፤
በወጣትነት እድሜያቸው ጫካ ውስጥ በመቀመጥ አብዝተው ማንበብን የታደሉ “የመፅሃፍ ቀበኛ” እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ ከተማሪነት ህይወት በኋላ መምህር የመሆን ፅኑ ፍላጎት የነበራቸው ሙጋቤ፤ መምህር የሚያደርጋቸውን መንገድ የተከተሉት ገና በ17 ዓመት የወጣትነት እድሜያቸው ነበር፡፡ በመምህርነት ሙያ ሰልጥ ነውም ተመረቁ፡፡
ከአጭር ጊዜ የአስተማሪነት ህይወት በኋላ በወቅቱ በአገራቸው የነበረው የነጮች የበላይነት ያምማቸው የነበሩት መምህሩ ሙጋቤ፤ “የማርክሲዝም” ርዕዮተ ዓለም የነፍሳቸው ጥሪ ሆነና እርሱን ለመማር ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንተው በፎርት ሃሬ ዩኒቨርሲቲ የመፃኢዎቹን አፍሪካውያን ብሔርተኞች ጎራ ተቀላቀሉ፡፡
ከደቡብ አፍሪካ ቆይታቸው በኋላ ወደ ጋና ያቀኑት ሙጋቤ አንድ የጋናውያን የነፃነት ታጋይ ታሪክ ለሀገራቸው ነፃነት ይታገሉ ዘንድ አርአያ ሆናቸው፡፡ በፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና አቀንቃኙ እና የጋናውያን የነፃነት አባት በክዋሜ ንክሩማህ የቀደመ እንቅስቃሴ የተደመሙት ወጣቱ ሙጋቤ ያነበበው እና የኖረበት የጋናውያን ገድል በዝምባብዌ ይፈፅም ዘንድ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡
ወደ አገሩ ተመልሶ ያደርገው የነበረው የነፃነት እንቅስቃሴ በሮዲዥያን መንግስታት ያልተወደደለት ሙጋቤ እ.አ.አ በ1964 ወደ እስር ግዞት ተወረወረ። በዚያም ድፍን 10 ዓመታትን አሳለፈ። በእስር ላይ እያለም መማር ያላቆመው ሙጋቤ በርቀት ትምህርት ሦስት ዲግሪዎች እንዳገኘ ይነገራል፡፡ በወቅቱ ከጋናዊቷ የመጀመሪያ ሚስታቸው የወለዱት የአራት ዓመት ልጃቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለያቸው በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመገኘት እና የልጃቸውን አስከሬን አፈር ለማልበስ ለሮዲዥያ መንግስት መሪው ኢያን ስሚዝ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ተደርጎባቸው ልጃቸውን ሳይቀብሩ ቀርተዋል፡፡
በመሠረቱት የዝምባብዌ አፍሪካ ናሽናል ዩኔን (ዛኑ-ፒኤፍ) የፖለቲካ ፓርቲ አማካኝነት በርካታ ውጣ ውረድ የበዛበት የነፃነት ትግል ካደረጉ በኋላ እ.አ.አ በ1980 በድህረ ነፃነት የተካሄደውን ምርጫ አሸንፈው ወደ መንበረ ንግስና ብቅ አሉ፡፡ ከምርጫ በኋላ 16 ዓመታትን በተለያዩ የህይወት ምዕራፎች አሳለፉና ከስልጣን የመውረዳቸው ምክንያት እንደሆኑ የሚነገርላቸውን ግሬስ ማሩፋ ሙጋቤን አገቡ፡፡
በስልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ ዓመታት ላይ በሀገራቸው የሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ከነጮች እጅ እየነጠቁ ለጥቁሮች ማደላቸው ያልተወደደላቸውና በምዕራባውያን ጥርስ ውስጥ ያስገባቸው ፕሬዝዳንት ሙጋቤ አውሮፓውያን ውድቀታቸውን ይመኙ ስለነበር እ.አ.አ በ2000 ሙጋቤን የሚጠሉትን ተቃዋሚዎች ሁሉ አሰባስበው ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ማድረግ ቢችሉም ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡
እ.ኤ.አ በ2008 ላይም ተመሳሳይ ጥቃት በደጋፊዎቻቸው ላይ ተካሂዶ ነበር፡፡ ሀገሪቱ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ድቀት በደረሰባት እ.አ.አ በ2009 ምርጫውን በማሸነፍ ለአራት ዓመታት ሀገሪቱን ለመምራት ቃለ መሃላ ፈፀሙ፡፡ “የሙጋቤ የመሪነት ዘመን መቼ ይጠናቀቃል?” የሚለው ጥያቄም የማይተነበይ አይነት ሆነ፡፡
እንዲያውም በአንድ ወቅት 100 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ሀገራቸውን እንደሚመሩ የተናገሩት የያኔው ፕሬዝዳንት ሙጋቤ፤ ብዙዎቹ ሞታቸው በቢሯቸው ውስጥ እንደሚሆን ይጠብቁም ነበር፡፡ ዳሩ ሳይታሰብ ፕሬዝዳንቱ ለባለቤታቸው ስልጣን ለማስረከብ እየሰሩ ነው በሚል እ.አ.አ በ2017 በትግል አጋራቸው፣ በምክትላቸው እና በአሁኑ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ አስተባባሪነት በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ከስልጣናቸው ገለል እንዲሉ ተደረጉ፡፡
ከስልጣን ከተነሱ በኋላም ከሀገሬው ሕዝብ ፍቅርና ክብር፤ ከመንግስታት ፕሮቶኮል እንዳልተቀነሰባቸው የሚነገርላቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙጋቤ በግል ባህሪያቸው ሽንፈትን አጥብቀው ይጠላሉና ቂም እንደቋጠሩና ጥላቻ እንዳዘሉ የሚያሳብቁ አስተያየቶችን ከመሰንዘር አልተቆጠቡም ነበር፡፡ በቅርቡ እንኳን አሁን ህይዎታቸው ባለፈበት ሲንጋፖር በህክምና ላይ እያሉ የሰጡት አስተያየት በርካቶችን አስደንግጦ ነበር፡፡ “ስሞት በብሔራዊ የጀግና ክብር እንዳትቀብሩኝ፤ ግብዓተ መሬቴም ሃራሪ ሳይሆን በተወለድኩባት አካባቢ በቤተሰቦቼ መካነ መቃብር ጎን ይፈጸም” የሚለው ኑዛዜያቸው የዙባቡዌ ባለስልጣናትን ያስደነገጠና የዓለምን ህዝብ ያነጋገረ ነበር፡፡
በአጠቃላይ በዚህች ምድር ለ95 ዓመታት ኖረው እና ሀገራቸውን ለ37 ዓመታት በመሪነት አገልግለው ግዳጃቸውን የፈፀሙት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ፤ በጥቁርነታቸው ኩራት የሚሰማቸውና ለነጮች አላጎበድድም በማለታቸው በተሸረበባቸው የነጮች ሴራ ያልተንበረከኩ በመሆናቸው መላው የጥቁር ህዝብ ገድላቸውን ሲዘክረው ይኖራል።
በአንጻሩ እኚህ
የጥቁር ፈርጥ ሙጋቤ ከአፄ ኃይለ ስላሴ እስከ ሞቡቱ ሴሴኮ፤ ከዚያድ ባሬ እስከ ጋዳፊ፤ ከቤን ዓሊ እስከ ሙባረክ በህዝብ ዘንድ
እንደተከበሩ፤ እንደተፈቀሩ፤ እንደተደነቁ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ አሻፈረኝ በማለታቸው የውርደትን ጽዋ ተከናንበው ከስልጣናቸው ሲወርዱ
በአይናቸው አይተዋል። በመሆኑም፤ እርሳቸው ከነዚህ ነገስታት ትምህርት ወስደው ስልጣን በቃኝ ብለው በክብር ባለመውረዳቸውና ወደ
ጨቋኝ መሪነት በመለወጣቸው ይተቻሉ። አገሪቷንም ወደ ባሰ ድህነት እንዳሸጋገሯትም ይነገራል። በመሆኑም አሁን ላይ በስልጣን ያሉ
የአፍሪካ መሪዎች ከነዚህ መሪዎች ይማሩ ይሆን?
አዲስ ዘመን መስከረም 2/2011
ሶሎሞን በየነ