አዲስ አበባ፡- አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያው የተዛባውን የማክሮ ኢኮኖሚ ለማስተ ካከልና ዜጎችን እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደ ሚረዳ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
አቶ ደመቀ በምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሀ ግብሩ ረቂቅ ሰነድ ላይ ትናንት በሸራተን ሆቴል ውይይት በተደረገበት ወቅት ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ባለፉት ዓመታት የታየው ዕድገት ፈጣንና ሁሉን አቀፍ ሆኖ እንዳይቀጥል ያደረጉ በርካታ የማክሮ ኢኮኖሚ፣ መዋቅራዊ እና የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ደካማ የኤክስፖርት አፈፃፀም፣ በግብርናም ሆነ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዝቅተኛ ምርታማነት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት በመንግሥት የመዋዕለ ንዋይ አካሄድ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል ብለዋል።
የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ደካማ አፈፃፀም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የመንግሥት ገቢ የመሰብሰብ ችግሮች የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ እንዲቀዘቅዝ ማድረጉን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ችግሮችን ለመቅረፍና የተዛቡትን ለማቃናት ባለፈው አንድ ዓመት የማሻሻያ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል፡፡
የዚሁ እርምጃ አካል የሆነው አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ የተዛባውን የማክሮ ኢኮኖሚ በማስተካከል ሁሉም ዜጎች ሊሳተፉበትና ከሚገኘው ትሩፋትም ሊቋደሱለት የሚችሉበትን አሠራር በመዘርጋት መዘጋጀቱን አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡
ማሻሻያው የሁሉንም አመለካከት ያካተተ እና የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰበት እንዲሆን በረቂቅ ሰነዱ ላይ ግልጽና ሁሉን ያሳተፈ ውይይት መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፤ መርሀ ግብሩ የምጣኔ ሀብት እድገትን በማረጋገጥ ለዜጎች በተለይም ለወጣቶች ብቁ የሥራ እድሎችን በመዘርጋት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጠንሳሽነት መዘጋጀቱንና የገንዘብ ሚኒስትር እያስተባበረው በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በሚመራ የማክሮ ኢኮኖሚክ ሪፎረም ፕሮግራም የበላይ ኮሚቴ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የማሻሻያ መርሀ ግብሩን በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ መዋቅራዊና የዘርፍ ማሻሻያ በተሰኙ ሦስት ምሰሶዎች መዋቀሩን ገልጸው፤ በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው የተረጋጋ የምጣኔ ሀብት እድገትን በማስቀጠል የፋይናንስና መሰረተ ልማትን እንደሚያሰፋና የመንግሥት ፋይናንስን በማጠናከር የኢንቨስትመንት ውጤታማነትን እንደሚያረጋግጥም ተናግረዋል፡፡
ዶክተር እዮብ በገለጻቸው በመዋቅራዊ ማሻሻያው በኩልም ቢሮክራሲው የሚደግፈው ቢዝነስን በማጠናከር፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማሻሻል፣ የንግድ እይታዎችን በማሳደግ እና መሰል ጉዳዮችን ተመርኩዞ እንደሚሠራ አብራርተው በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት የግብርና አቅርቦትን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ማህበራት ማዘመን፣ የግሉ ዘርፍ በግብርና ሥራዎች እንዲሳተፍ ማድረግ፣ ከገቢ ንግዱ ጋር የሚፎካከሩ እንዱስትሪዎችን ማበረታታትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሥራዎች እንደሚሠሩ አብራርተዋል፡፡
ለአስር ዓመታት እንዲያገለግል ሆኖ የተዘጋጀው ማሻሻያው ተግባራዊ ሲደረግ ፈጣንና ቀጣይ የምጣኔ ሀብት እድገት ማምጣት፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ፣ የዋጋ ግሽበትን በነጠላ አሀዝ የተገደበ እንዲሆን ማድረግና ዘመናዊ የፋይናንስ ስርዓትን መዘርጋትን ጨምሮ በርካታ ለውጦችን እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2011
ድልነሳ ምንውየለት