የመጽሐፉ ርእስ የታሪክ ቅርስና ውርስ አበበ አረጋይ (ራስ)
አሰናጅ አጥናፍ ሰገድ ይልማ
የገጽ ብዛት 376
ዘመነ ኅትመት 2011 ዓ ም
ኅትመት በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት
የመጽሐፉ ዋጋ 250 ብር፤ በዶላር 20
መጠኑ ትልቅ መጽሐፍ ነው።
ደራሲና ጋዜጠኛ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ቀደም ሲል የበደል ካሳ (ልብ ወለድ)፤ የእንስሳት አመፅና ድርድር (ፖለቲካዊ አሽሙር)፤ የሕይወቴ ምሥጢር (ግለ ታሪክ)፤ የልጅ ኢያሱ አነሣሥና አወዳደቅ (ግለ ታሪክ)፤ አገር የፈታ ሽፍታ (ልብወለድ)፤ ሌላ የፖለቲካ አሽሙር፤ የተሰኙ ሥራዎችን ሠርተው ለኅትመትና ለንባብ አብቅተዋል። አሁን ደግሞ « በፎቶግራፎችና በልዩ ልዩ መረጃዎች አጠናክረው «የታሪክ ቅርስና ውርስ አበበ አረጋይ (ራስ) » የሚል አዲስ መጽሐፍ ይዘውልን ቀርበዋል። የመጽሐፉ ይዘት ስለ ታዋቂው አርበኛ ራስ አበበ አረጋይ ግለታሪክና ስለአደረጉት የነጻነት ተጋድሎና ስለከፈሉት መሥዋዕትነት ነው።
በ38 ምዕራፎች የተከፋፈለው ይህ መጽሐፍ በአምስቱ የመከራ ዘመን ፋሽስቷ ኢጣሊያ ሀገራችንን በግፍ ወርራ በነበረችበት ወቅት በጦር ስማቸው አባ ገስጥ ( ራስ አበበ) በየጦሩ ግንባር ከፋሺስቶች ጋር ፊት ለፊትና በደፈጣ ጭምር በመዋጋት ለኢትዮጵያ ነጻነት መመለስ ስለ ከፈሉት ዋጋና ስለ አስመዘገቡት የድል ውጤት፤ ከነጻነት በኋላም በሀገሪቱ ስለ ነበራቸው ወሳኝ የፖለቲካ ሥልጣን ማለት የአገር መከላከያ ሚኒስትር ስለመሆናቸው ያትታል። ከኢጣሊያ ጦርነት በፊት ስለነበረው ያገራችን ታሪክ ጭምር የሚያስገነዝበው ይህ መጽሐፍ ስለ እንግሊዝ ተንኮለኛነት፤ስለ ጦርነቱ ዋዜማና የክተት ጥሪ፤ አነጋጋሪ ስለሆነው ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስደት፤ ራስ አበበ ዱር ቤቴ ብለው ስለፈጸሙት የዐርበኝነት ተጋድሎ፤ ስለአስካላ አቦ ጦርነት (ጅሩ ደነባ አካባቢ የሚገኝ ቦታ)፤ በወቅቱ ማለት በ1928 ዓ.ም የጠላት ምሽግ የሆነቺውን አዲስ አበባን ከትግል አጋሮቻቸው ከወንድማማቾቹ ከደጃዝማች አበራ ካሳና ከደጃዝማች አስፋወሰን ካሳ፤ ደጃዝማች ኃለማርያም ማሞ፤ ከደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ፤ ከራስ መስፍን ስለሺ፤ ከደጃዝማች ዘውዱ አባ ኮራን፤ ከደጃዝማች ፍቅረማርያም ናደው ጋር 40 ሺ ያህል ሠራዊት አሰልፈው ጠላትን ሲያስጨንቁ ውለዋል።
ወቅቱ ክረምት ሆኖ ኃይለኛ ዝናም ይጥል ስለነበር ዐርበኞቹ እንደልብ መረጃ ለመለዋወጥ እንዳልቻሉና ከታላላቅ አርበኞችም ውስጥ እንደነ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶን የመሳሰሉ በትግል ላይ ስለወደቁ የተጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳልተመዘገበ፤ ግን ከበባው በኢጣሊያ የጦር መሪዎችና ተዋጊዎች ላይ ከፍተኛ መደናገጥን እንደፈጠረ ደራሲ አጥናፍ ሰገድ መረጃዎችን ዋቢ አድርገው ጽፈዋል። ራስ አበበ በሳላይሽ ተራራ በዋዩ ክፍል
(ሰሜን ሸዋ ) መድፍ ከታጠቀው፤ አውሮፕላን ከአሰለፈው፤50 ሺ እግረኛ ጦር ከነበረው ከጀኔራል ትራኪያኒ ሠራዊት ጋር ስለ አደረጉት ጦርነትና የባንዳው ፊታውራሪ መሸሻ ባንቺ ሠራዊት እንዴት እንደተደመሰሰ፤ ደጃዝማች አበራ ካሳ ከአርበኝነት ወደ ጠላት አማኝነት እንዴት እንደገቡ፤ በ1929 ዓ.ም የሸዋ አርበኛ እንዴት ያለ አውራ እንደቀረ፤ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ነውረኛነት ያለው ቃል ስለመናገራቸው፤መጽሐፉ ያስረዳናል።
በተጨማሪም ባንዳው ደጃዝማች ተወንድ በላይ እንዴት እንደተማረከ፤ ከባንዳ ኪዳኔ መሸሻ ጋር ስለተደረገው ጦርነትና ስለኪዳኔ ሞት፤አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ከአበበ አረጋይ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት፤ስለደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ፤የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ. ም በማርሻል ግራዚያኒ ላይ በተጣለው አደጋ ምክንያት በግፍና በጅምላ ስለተጨፈጨፉት የኢትዮጵያ ሰማዕታት የታሪክ ቅርሱ ይተርክልናል።
እንደዚሁም፤ አባ ገስጥ በተጉለት፤ በመንዝና በሌሎች ቦታዎች አርበኞች እንዲጠናከሩና የባንዶች ጦር እንዲዳከም በማሰብ ከትግል አጋሮቻቸው ከነደጃዝማች አውራሪስ፤ ከነ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ፤ ፊታውራሪ ደስታ ሸዋርካብኽ፤ ከነፊታውራሪ አየለ ኃይሌ፤ ፊታውራሪ ዘውዱ አባ ኮራን፤ ከልጅ ማነ ብርሃን አባ ኮራን፤ ከግራዝማች ዘውዱ አስፋው፤ ከቀኛዝማች አበበ አውራሪስ ፤ ከባላምባራስ በሻህ ኃይሌና ከሌሎች ጋር እየተማከሩ የተቀናጀ የተጋድሎ ስልት በመቀየስ ይታወቃሉ።
በዚህም እንደነ ዓለሙ ኤጀርሳ ከመሳሰሉና ከሌሎች መሰል ባንዶች ጋር በተደረገ ጦርነት ለኢጣሊያ ያደሩ ከሐዲዎች ሲደመሰሱና አርበኞች ድል ሲቀዳጁ እናያለን። በጥቅሉ ራስ አበበ በሸዋ ያልተሰለፉባቸው ዐውደ ግንባሮች የሉም ለማለት ይቻላል፡ በዋነኛነትም፡ በሸንኮራ፤ በአሌልቱ፤ በቅምብቢት፡ በወበሪ፤ ግንባር፤ በጦስኝ፤ በቁልቋልበር፤ በከሰም፤ በደንሴና በቡርቃ ግንባር፤ በውግር፤ በሰሞሳ፤ መድፍ፡ በተማረከበት߹ በአሳግርት፤ በእንሳሮ߹ በእነዋሪ፡ በተከታታይ፤ በካቺሴ፤ በምራኔ፤ በሮቢ ወንዝ ጦርነት፤ በያያ ቀጨማ፤ በመንዝ ደንገዜ ገጦ ጦርነት፤ በየይል፤ በሣጋ በር፤ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ በተሠውበት በጎርፎ ሜዳ የጦር አውድማዎች ከኢጣሊያ ጦር ሠራዊትና ከባንዳው ተዋጊ ጋር ተጋድሎ አድርገዋል∷ከዚህ የተነሣም ባንዳው ደጃዝማች ጨቡድ ሊማረክና የኩምቢ ከምሲ ባንዳ ሠራዊት ሊደመሰስ ችሏል። ከኢጣሊያ ጋር የተደረገው ጦርነት ጣሊያኖች ወደጅምላ ጭፍጨፋ እንዴት እንደተሸጋገሩና ተጋድሎው በመሃል ሲዳከምና ጠላት ሲያይል አርበኛው ጥቃትን እየመከተ እንዴት እንዳፈገፈገ አጥናፍ ሰገድ ይተርኩልናል።
በተለይም አርበኛ የነበሩት ባለቤታቸው ክብርት እመቤት ቆንጂት አብነት ከነአራስ ልጃቸው አየለወርቅ አበበ ጋር በካቢ ጦርነት መማረካቸው ከትግሉና ከአርበኝነት መንገዳቸው ሊያግዳቸው አልቻለም። ይልቁንም አይደለም እርሳቸው ወላጅ እናታቸው ክብርት አስካለ ጎበና ዳጨ « ልጄ የተቀበለውን መከራ እኔም እቀበላለሁ» በማለት ከጦሩ ጋር አብረው ይጓዙ ነበር። ጉዞው እንደተጀመረ በጸና ስለታመሙ በቅሎ ለመሄድ ስላልቻሉ በቃሬዛ ጭምር ይጓዙ ነበር።
አስቀድሞ ታምሞ የነበረው ልጃቸው ዳንኤል አበበም እንዲሁ በቃሬዛ ይሄድ ነበር። በዚህም የራስ አበበ ቤተሰቦች ጭምር ለሀገራችን ነጻነት ከፍተኛ መሥዋዕትነት እንደከፈሉ ከታሪኩ እንረዳለን። ራስ አበበ በድንገት ከጠፉ በኋላ እንደገና ተመልሰው ሲመጡ ካገር አገር ሲሳደድ የነበረው አርበኛ ሁሉ ሞራል ገዝቶና ተበረታትቶ በጭቃ ሚካኤል፤ በሰቻት ክብ፤ በዳንሴ፤ በሾላ ገበያ በቆቦ አራዳ በፍቅሬ ግንብ በደነባ፤ በመንዲዳ፤ በወበሪ፤ በሳክላ፤ በዙሪያ ምሁይ፤ በሳሲት ባደረገው ውጊያ ከፍተኛ ድል ለመቀዳጀት ተችሏል።
ትግሉም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር መጀመሪያ በሰሜን ሸዋ መንዝ ጥቅምት 23 ቀን 1831 ዓ. ም ተመሥርቶና ተጉለት አንቀላፊኝ በተባለ ቀበሌ ታኅሣሥ 29 ቀን 1931 ዓ. ም ደንቡ ተሻሽሎ የሥራ መሪ አካላት ሲሠየሙ ራስ አበበ አረጋይ የማኅበሩ የክብር ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን የምንረዳው ውብ በሆነ አገላለጽ የተጻፈውን መጽሐፍ ስናነብ ነው።
መጽሐፉ መልአከ ፀሐይ ኢያሱ እንዴት እንደነገሡ፤ራስ አበበ አርበኞችን ሲያስታርቁና የእርቅና የሰላም ድርድር ሲያደርጉ፤ ስለ ወሌንሶናጎንቤሳ ጦርነት፤ ስለዜና አብሳሪው የደጃዝማች ከበደ ተሰማ ደብዳቤ፤ ስለደብዳቤ ግንኙነት፤ የኢጣሊያ ጀኔራሎች ራስን ለማጥመድ ስለአደረጉት ጥረት፤ የጅሩ አርበኞች በግፍ ስለመገደላቸው ስናነብ የአምስት ዓመቱ የመከራ ዘመን ምን ያህል አሠቃቂ እንደነበረ እንገነዘባለን። የአርበኞች የሥልጣን ሽሚያም በአስገራሚነቱ የሚታይ ነው። አባ ገስጥ ቆራጥ፤ ጀግናና የውሳኔ ሰው መሆናቸውም አስገራሚ በሆነ መልኩ ተመዝግቧል። ናዚ ዐርበኞችን ለመደምሰስ 200 ሺ ሠራዊት አሰልፎ ስለመጠባበቁ፤ አባ ገስጥ በድል ዋዜማና መግሥት፤ ከጄኔራል ካኒንግሃም ጋር ስለመገናኘታቸው፤—–በርካታ ርእሰ ጉዳዮችን በመጽሐፉ ውስጥ እናገኛለን። ንጉሡ በድል አድራጊነት አዲስ አበባ እንደ ገቡ፤ ስለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፤ ከአርበኛ ቆንጂት አብነት ስለአገኙት መረጃ ደራሲ አጥናፍ ሰገድ ጽፈውልናልና ይህንን በታሪክ ሰነድነቱ ጠቃሚ የሆነውን መጽሐፍ ማንበብ ይበጃል ::
አዲስ ዘመን ነሀሴ 19/2011
ታደለ ገድሌ ጸጋየ ዶ/ር