የካቲት ወር በ1952 ዓ.ም ነው የተመሠረተው፤ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር። ማኅበሩ አንድ ብሎ ዛሬ ላይ ያደረሰውን ጉዞ ሲጀምር በተወሰኑ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች እንዲሁም ሥነ ጽሑፍ አፍቃሪያን ለእቁብ በመሰባሰብ ነበር። የእቁቡ አላማም መጽሐፍ ለማሳተም አቅም የሌላቸውን ደራስያን ለማገዝ ነው።
ዛሬ ከ59 ዓመታት በኋላም የሕትመቱ ጉዳይ ለደራስያን ፈተና ከመሆን ያስቀረው ነገር ባይኖርም፤ መጽሐፍን ሰበብ አድርጎ የተጀመረው ኅብረት ግን ዛሬ ድረስ ቀጥሏል። አሁን ማኅበሩ ላለበት ደረጃ ባደረሰው እርምጃ ተጉዟል። በዚህ ጉዞው እንደመልካም የሚታሰቡ ጥቂት የማይባሉ ተግባራትን አከናውኗል። እዚህ ላይ በዋናነት ጥናታዊ ሥራዎች ተሰባስበው የሚታተሙባትን ብሌን መጽሔት መጥቅስ ይቻላል። እንዲሁም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተጀመረውን የንባብ ሳምንት ጨምሮ በየዓመቱ የሚደረገው የክረምት ስልጠና ይጠቀሳሉ።
የዛሬ ነገራችንም ከዚህ ስልጠና ጋር የተያያዘ ነው። ከሰባት ዓመታት በፊት የተጀመረውና በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር አዘጋጅነት የሚካሄደው ይህ የክረምት ስልጠና በየዓመቱ በርካቶችን ያሳትፋል። የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ደራሲ አበረ አዳሙ እንደገለጹት፤ ስልጠናውን ለመጀመር ምክንያት የሆነው ሥነጽሑፍ ያለውን ሚና ከመረዳትና አልፎም ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ነው።
በዚህ የደራስያን ማኅበር ዓመታዊ ስልጠና በእድሜ ትንሽ ከሚባሉ ልጆች አንስቶ ‹‹ማምሻ›› ላይ መጣሁ እስካሉ በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች ድረስ አሳትፏል። ለሥነጽሑፍ ፍቅር ኖሯቸው፤ በተፈጥሮ የታደሉት ፀጋ እያለ ነገር ግን የሚያንኳኩትን በር እንኳ ለማያውቁ ብዙዎች ማኅበሩ ለስልጠና በሩን ክፍት አድርጎ አስገብቷል።
ስልጠናው ያለማቋረጥ ለሰባት ዓመታት የመካሄዱ ነገር እንዴት እንደተሳካና ስላለው ውጣ ውረድ ለደራሲ አበረ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። እርሳቸውም ፈተናው ቀላል እንዳይደለ ነው ያነሱት። ሰልጣኞች የሚከፍሉት የተወሰነ ገንዘብም በሰፊው ቀዳዳ የሚሸፍን ባይሆንም በተለይ በስልጠና ቆይታው አጫጭር ስልጠና በመስጠት፣ ልምድ በማካፈልና በማስተማር የሚሳተፉ ባለሙያዎች ቀናነት ግን ለስልጠናው ቀጣይነት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ከዛም ባሻገር የሰልጣኞች ደስታና ጥያቄ እንዲሁም ስኬት ለማኅበሩ በስልጠናው ለመቀጠል ነዳጅ እንደሆነለት ይጠቅሳሉ። ከሰልጣኞቹ መካከል መጽሐፍ ያሳተሙ፣ ወደ ጥበባዊ ምሽት መድረኮች ብቅ ያሉና በውስጣቸው አኑረው ያቆዩትን አቅም ያወጡ ጥቂት እንዳልሆኑ ገልጸዋል። እዚህ ላይ በሦስተኛ ዙር የማኅበሩ ስልጠና ተሳታፊ የነበሩና የተመረቁ ሰልጣኞች የመሠረቱትን ፍኖተ ጥበብ የተሰኘ ኅብረት መጥቀስም ይቻላል።
የማኅበሩ አባል ደራሲ፣ ገጣሚና ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት፤ የስልጠናው ዓላማ ተማሪዎችን ሊቅ አድርጎ ለማውጣት አይደለም ብለዋል። በአንድ ጎን ወደ ስልጠናው የሚመጡ ሰዎች በተፈጥሮ ያላቸውን ተሰጥኦ ኮርኩሮ በማውጣትና ለነገ የሥነ ጽሑፍ ሰው እንዲሆኑ ማድረግ ሲሆን በሌላ በኩል መነሻ ሆኗቸው ለንባብ እንዲበረቱ ማስቻል ነው።
ደራሲና ገጣሚ አያልነህ ሙላት፤ ይህ ስልጠና ወደፊት ማኅበሩ በተጠናከረ ጊዜ የበለጠ እንደሚሰፋም ነው የተናገሩት። እንዳውም የኢትዮጵያን ብዝኀ ቋንቋና የሥነጽሑፍ ሀብት የሚያወጣ እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል። በስልጠናው ላይ የጎላ ድርሻ ያላቸውን መምህራን አሰልጣኞች የሆኑ ሥነጽሑፍና ኪነጥበብ ባለሙያዎችም ሊመሰገኑ ይገባል ይላሉ።
በአራተኛው ዙር ስልጠና ምርቃት ላይ በሥራ አስፈጻሚነትና የስልጠናው አስተባባሪነት የተገኘው ደራሲ ይታገሱ ጌትነት ሥነጽሑፍ የማህበረሰብንና የሕዝብን ሁኔታ ዘመን ተሻግሮ የሚናገር ምስክር ይናገራሉ፤ በእውቀት የጎለበተ ዜጋ ለመፍጠር ያለውን ሚናም ከፍያለ ነው ይላሉ። በጊዜውም ኢትዮጵያ ለነበረችበት ሁኔታ ወሳኙ ሥነጽሑፍ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
በዚህም ሁሉ ምክንያት ለጥበብ ዘርፍ ትኩረትን መስጠት ትውልድን ከመገንባትና ተያይዞም አገርን ከመሥራት አንጻር ሊመረመር ይገባል። በጥበብ ዙሪያ በመሥራትም ነገ ላይ የተሻሉ አንባብያን፣ የበሰሉ ደራስያንና እና የሰሉ ሃያስያን ለመፍጠር ስልጠናው ተመራጭ ነው፤ እንደ ደራሲ ይታገሱ ገለጻ።
ማኅበሩ አሁን ላይ በብዙ መንገድ እጅ ቢያጥረውም በስልጠናው ላይ ግን የተሳካ ጉዞ እያደረገ መሆኑ እየታየ ነው። በዚህም ብቻ ሳይሆን ሳምንታዊውን የጥበብ እልፍኝ የራድዮ መርሃ ግብር፤ ዓመታዊውና ወደ ታላላቅ ታሪካዊ እና የድርሰት መቼት ወደ ሆኑ ቦታዎች የሚደረግ ጉዞ እንዲሁም እየተሟጠጠ ባለው በዚህ ዓመት ጀምሮ ለወራት እየተካሄደ ያለው ብሌን የኪነ ጥበብና የሥነጽሑፍ ምሽትም እዚህ ላይ ሳንጠቅስ አናልፍም።
ብሌን ወርሃዊ የኪነጥበብ ምሽት አድማጭ፣ ተመልካችና ተደራሲን ከአንጋፎቹ ጋር በማገናኘት ሚናው ቀላል አይደለም። ምንም እንኳ አሁን ላይ በርካታ የኪነ ጥበብ ምሽቶች በመዲናችን ቢከናወኑም፤ ብር እየከፈሉ በእነዚህ መሰል መድረኮች መሳተፍ ለማይችሉ መድረኩን በነጻ እንዲታደሙበት አስችሏል። ከዚህም በላይ አዳዲስና ወጣት፣ ለመድረክ አዲስ የሆኑ ሥራዎቻቸውን እንዲያወጡና እንዲያቀርቡ በማድረግ የሁሉም በመሆን እያገለገለ ነው።
ይህም ሆኖ ፍጽምና ከማኅበሩ ይገኛል ማለት አይቻልም። ከሃምሳ ዓመታት በላይ የኖረ ማኅበር አሁንም እንደልቡ የሚሠራበት ቢሮ የሌለው ነውና ይህ እንደ ችግር ሊነሳ የሚገባው ነው። ማኅበሩ ለግንባታ የተረከበው መሬት ሳይንቀሳቀስ እንደታጠረ መገኘቱ አሳሳቢ ነው። ብዙውን ጊዜ እንደተካሄደ የሚነገርለት የአፍሪካ ደራስያን ኅብረት ከተኛበት እንዲነቃ ለማድረግ ህልም ያለው ማኅበር፤ ይህን ችግር መፍታት ቀዳሚ የቤት ሥራው ሊሆን መገባቱ እሙን ነው።
ሌላው ዘንድሮ ለአራት ጊዜ የተካሄደው የንባብ ሳምንት ዓመታዊ ክዋኔ ከአጀማመሩ አንጻር መቀዛቀዙ ይስተዋላል። ሰኔ 30ን የንባብ ቀን ለማድረግ ታልሞ የተጀመረው እንቅስቃሴ ሊጠናከር የሚገባ ነው። የሚነበቡ መጻሕፍትን ለደራስያን በማቅረብ በኩል ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የተጀመረው የመጻሕፍት ሕትመት ተዘዋዋሪ ፈንድ የሚበረታታ ሆኖ፤ እነዚህም ጉዳዮች ላይ ዓይንን ሳይነቅሉ መከታተል ይጠበቃል።
‹‹ባምር ጠላሁ!?›› እንዳለች ዝንጀሮ፤ ማኅበሩ እነዚህን ችግሮች እንዳይፈታ ብዙ መሰናክሎች ሊኖሩበት ይችላሉ። በእኔነት ስሜት የሚሠራ አመራር በመመደብ፤ የቀደሙት በእውቀትና በልምዳቸው እንዲያግዙ አድርጎ ነገን የሚያልሙና አዲስ ሥራን የማሳየት ድፍረት ያላቸው፤ በሌላ አማርኛ ጥበብን ከመሪነት ያጋመዱ አቅም ያላቸው ወጣቶችን ወደ አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ማቅረብ ያስፈልጋል። የኢኮኖሚ አቅም ብቻም የችግሮች መፍትሔ ላይሆን ስለሚችል፤ ማኅበሩ በሁሉም አቅጣጫ ነገሮችን መቃኘት ያሻዋል።
ከዛም ባሻገር ደግሞ ማኅበሩ በገንዘብ የማይተመን ሀብት ያለው መሆኑን ልብ ይሏል። አንድም በእድሜና በልምድ የተሻለ መሆኑ ሲሆን በዛው ልክ በእድሜም በእውቀትም አንጋፎችንና ‹ኑ!› ብለው ቢጣሩ አቤት ባይ ብዙ ልጆች ያሏቸው የኪነጥበብ ባለሙዎች በማኅበሩ በአባልነት ይገኛሉ። እነሱንም ተጠቅሞ አዳዲስ የእቅድ ሥራዎችን በማቅረብ አቅምን መሰብሰብ ይቻላል። ማኅበሩንም ማሳደግ የሚቻለው አንድም በማኅበሩ አባላት በኩል ነውና፤ እነዚህን ባሙያዎች ተጠቅሞ ገቢዎችን በማሰባሰብ፣ የአባላት ቁጥርን በመጨመርና ተደራሽነትን ማስፋት ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ይሆናል።
ይህ ሲሆን ብቻ በአፍሪካ ደረጃ ለአፍሪካ ደራስያን ማኅበር መቀመጫ ለመሆን ያለውን ምኞት እውን ማድረግ ይቻላል። በትንሹ ሳይታመኑ በትልቁ መሾም የለምና አሁን በእጅ ባለው ሀብት በአግባቡ መሠራትን ይጠይቃል። ‹‹በንባብ ዜጎችን አመዛዛኝና ምክንያታዊ እንዲሆኑ ማገዝ ይቻላል፤ አንባቢ ትውልድ በአዳዲስ አስተሳሰቦች አገርን ይቀይራል›› ተብሎ ከታመነ፤ ማኅበሩን ማገዝና ማጠናከር የሁሉም ጉዳይ መሆኑ አይቀርም። ለዚህም ትኩረት እንዲደረግ ለሚመለከተው ሁሉ አደራው የሁሉም ነው እንላለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ነሀሴ 19/2011
ዳግም ከበደ