በአንድ ታክሲ ውስጥ ከአሽከርካሪው ጀርባ ባለው ቦታ በጉልህ የተፃፈ ማስታወቂያ ይነበባል:: ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ቀልብ የሚስብ ማስታወቂያ በመሆኑ እውነታነቱን ለማረጋገጥ ክትትል እንዲያደርጉ ያስገድድዎታል:: እውን በማስታወቂያ ላይ እንደተባለው አሽከርካሪው ተግባራዊ ያደርግ ይሆን በማለትም ጉዳዩ የሚመለከተው አንድ ሰው በኖረ ሲሉም ይመኛሉ::
የማስታወቂያው አስነባቢ ወጣት ኒቆዲሞስ ሳሙኤል ይባላል:: ተወልዶ ያደገው አራት ኪሎ አካባቢ ነው:: በቲአትር ትምህርት ዲፕሎማ አለው:: በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ቀን ቀን ታክሲ ሲሰራ ማታ ማታ በግል ኮሌጅ ሶስተኛ ዓመት የሲስዮሎጂ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል::
የታክሲ ስራ መስራት ከጀመረ ገና ዓመት ከጥቂት ወራት ያህል ነው ያስቆጠረው፤ የታክሲ ስራውን ለመስራት መሪውን የጨበጠ ዕለት አንድ ነገር ወደ አዕምሮው ተመላለሰ:: በታክሲው በጎ ነገር እንዴት ማድረግ እንደሚችል አወጣ አወረደ:: ምላሹንም በልቡ አኖረ፤ ይሁንና በጎ ነገርስ ለእነማ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም፤ ምክንያቱም ለእነማ መደረግ እንዳለበት አሳምሮ ያውቃልና:: በመሆኑም የመጀመሪያው በጎ ነገር ሊደረግላቸው ይገባል ብሎ ከሚያስባቸው ባለሙያዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት መምህራን ናቸው ሲልም ደመደመ:: ስለዚህም ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑም አገልግሎት በሚሰጥበት ታክሲው ውስጥ ማስታወቂያ በጉልህ አስጽፎ ለጥፎ መምህራኑን ተጠቃሚ ማድረግ ጀመረ::
ለምን አስተማሪ ብቻ ሲባልም በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት ነው የሚናገረው:: የመጀመሪያው ምክንያት እርሱ የመምህራን ውጤት በመሆኑ ሲሆን፣ ሌላኛው ምክንያቱ ደግሞ በዚህች ዓለም ላይ ላለ ለየትኛውም ሙያ መነሻው መምህር በመሆኑ ነው:: መምህርነት ከየትኛውም በተሻለ በታማኝነት የሚሰራ ስራ ስለመሆኑም ይናገራል:: መምህርነት ሙስና ያልዞረበትና ትውልድ የሚቀረፅበት ነው:: በጥቂት ብር ደመወዝ እስከ 200 ሺ ብርና ከዚያም በላይ የሚከፈለው ባለሙያ የሚያፈራው መምህር ብቻ እንደሆነም ያስረዳል::
በወጣቱ እምነት ያለውን እውቀት ተማሪው እንዲበልጠው አሟጦ የሚሰጥ መምህር ብቻ እንጂ ሌላ ባለሙያ የለም:: መምህር ግን ተማሪው ከእርሱ በልጦ እንዲገኝ የሚጥር ነው::
ወጣቱን ግን አንድ ነገር ያሳስበዋል:: በዚህ ዘመን ለመምህርነት ሙያ የሚሰጠው ክብር ዝቅ ማለቱና ተማሪዎችም ለመምህራን ያላቸው አስተሳሰብ መውረዱ ለእርሱ ስጋት ነው:: በእርግጥ ከዚህ ዘመን መምህራን አንዳንዶቹ የቁርጠኝነት ችግር ያለባቸው መሆናቸውም በእጅጉ ያሳስበዋል::
የነፃ አገልግሎቱን የሚሰጠው በአሁኑ ወቅት በመምህርነት ሙያ ላይ ለተሰማሩ ብቻ አይደለም፤ መምህር ለነበሩና በጡረታ ለተገለሉም ጭምር እንጂ:: በጎነትን ለማድረግ ከተነሳሳበት ምክንያት አንዱ እርሱ መምህራኑን አክብሯቸው ሌሎችም እንዲያከብሯቸው በማሰብ ነው፤ አሁን ላይ እያሰተማሩ ያሉ መምህራን የያዙት ሙያ የተከበረ በመሆኑ አክብራችሁ ያዙት ለማለት ያህልም ጭምር ነው::
በቀን ከአስር እስከ 15 መምህራን በታክሲው በነፃ ይሳፈራሉ:: ሲወርዱ ደግሞ በጣም አመስግነውና ተገርመው ነው:: አንዳንዴ ደግሞ በተደረገላቸው በጎነት ብቻ ሳይሆን በሐሳቡ ብቻ ውስጣቸው ተነክቶ የሚያልቅሱም አጋጥመዋል:: በስራቸውም ክብር እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸው አይደብቁትም::
ለወጣት ኒቆዲሞስ በጎነት የሚሰጠው ግብረ መልስ ከመምህራኑ ብቻ አይደለም:: ከሌሎችም ጭምር የምርቃት ናዳ ይዥጎደጎድለታል:: እርሱ በቀን እስከ 20 ምልልስ ያደርጋል፤ በአንድ ዙር ደግሞ የሚጭነው 15 ሰው ነው:: ስለዚህ 20ን በ15 ስናባዛው በቀን ከ200 በላይ ሰው ስለመምህራን የሆነ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ያደርጋል:: በእነርሱ ብቻ አያበቃም፤ እቤትም ሄደው ስለዚህ ጉዳይ ይናገራሉ:: እናም ስለመምህራን አንዳች መልካም ነገር ይነገራል:: ወጣቱ የሚኖረው ብቻውን ተከራይቶ ሲሆን፣ በሚያደርገው በጎነት እህትና ወንድሞቹም ያበረታቱታል::
ኒቆዲሞስ፣ ‹‹በጎነት የውስጥ ሰላም ይሰጣል:: ህሊናም ያርፋል፤ እረፍት አለ:: ሰው ሲፈጠር መልካም ተደርጎ ነው የተፈጠረው›› ሲል ገልጾ፣ ክፉ ዘር በውስጡ እንዳልተዘራም ይናገራል:: ‹‹እንዲያ ከሆነ ደግሞ አንዳችን የሌላችንን ሸክም መሸከም እንችላለን:: የእውነት ሲታሰብ የዚህች አገር ድህነት ከአገሪቱ ባለፀጎች በላይ ሆኖ አይደለም ብዙዎች በመሰቃየት ላይ ያሉት:: የብዙዎች ችግር ከጥቂቶች አቅም በላይ ሆኖ ሳይሆን አንዱ የሌላኛውን ችግር ለመሸከም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው:: ሁሉም እርስ በእርስ በአቅሙ መደጋገፍ ቢችል የተሻለች አገር መመስረት ይቻላል:: እንዲሁም የተሻለች አፍሪካን ብሎም ዓለም መገንባት ያስችለናል::›› ይላል::
በኒቆዲሞስ እምነት ለዚሁ ሁሉ መሰረቱ መምህራን ናቸው፤ እነርሱ ትውልድን ይቀርጻሉ:: መምህራን ትውልድን ከጨለማ ወደብርሃን የሚያወጡ ናቸው ሲልም ወጣቱ ይናገራል:: ዛሬ ላይ ዓለምን የሚመሩ ታላላቅ መሪዎች የመምህራን ውጤት መሆናቸውን ይገልጻል::
ወጣቱ፣ ሁልጊዜ በጎነትን ማድረግ እየተመኘ ያደርግም ነበር:: ለምሳሌ ታክሲ ባይኖረውም አቅሙ በፈቀደው መጠን የተወሰኑ ሰዎችን ይረዳል:: ለምሳሌ ያህል ብዙ ጊዜውን በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያሳልፍ ነውና ባለው እውቀት ልጆቹን ከመንፈሳዊ ትምህርት ባሻገርም ከጓደኞቹ ጋር በመሆ ን ያስተምራቸው ነበር::
ምንም እንኳ በማስታወቂያው መሰረት መምህራን መታወቂያ እንዲያሳዩ ቢጠይቅም፣ ‹‹እኔ መምህር አሊያም መምህርት ነኝ›› ማለት ብቻ ነው የሚጠብቅባቸው:: ጡረታ የወጡም ቢሆኑ ‹‹አስተማሪ ነበርኩ›› ማለት ብቻ ነው ያለባቸው:: እርሱም እንደዚያ ሲሉት ያለምንም ክፍያ የትራንስፖርት አገልግሎቱን በእምነት ይሰጣቸዋል::
በእርግጥ እያንዳንዱ መምህር ሶስት ብር መሳፈሪያ አጥቶ አይደለም፤ አሊያም ከቤቱ የሚወጣው አልከፍልም ብሎ አይደለም:: እንዲያውም መምህራንን የማያስከፈል ሰው አለ ብሎም አያስብም:: እርሱም የዚያን ያህል ድጋፍ አደረኩ ለማለት ሳይሆን ዋናው ለእነሱ ያለውን ከበሬታ ለመግለፅና ሐሳቡን ለማጋራት በማሰብ ነው አገልግሎቱን የሚሰጠው::
አንዴ መምህር ያልሆነ ሰው በተደጋጋሚ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ይሳፈር ነበርና ረዳቱ ከዚህ በኋላ መታወቂያ መጠየቅ አለብን በማለቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መምህር የሆነ ሁሉ መታወቂያውን እንዲያሳይ ማድረግ ተጀምሯል::
ወጣቱ ጥቂት ነገር በማድረጉ በብዙ እያተረፈ እንደሆነ ይናገራል:: ምክንያቱም እርሱ ለመምህራን በሚያደርገው ነገር በመማረካቸው ሌሎች ደግሞ ‹‹አንተ እንዲህ በጎነት እያደረክ ከሆነ እኔ ደግሞ ለሁለት መምህር እከፍላለሁ›› በሚል ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች መምህራን በሚል የሚከፍሉ በርካታ ሰዎች ናቸው:: ስለዚህም መልካም ለማድረግ በማሰቡ ለራሱም መልካም እየተደረገለትም ነው ማለት ይቻላል::
በጎነቱ የሚያካትተው ከመዋዕለ ህፃናት እስከ ዩኒቨርስቲ ላሉ መምህራን ሁሉ ነው:: የየትኛውም ቤተ እምነት የሃይማኖት መምህራንንም በዚሁ አገልግሎት ተካተዋል:: የኃይማኖት መምህር ነኝ ካሉ ያለክፍያ ይሳፈራሉ:: ምክንያቱም እነርሱም ቢሆኑ መልካሙን ለትውልድ የሚያስተምሩና ስነ ምግባር እንዲኖር የሚጥሩ ናቸውና ይላል:: እንዲህ በሚያደርግበት ጊዜ ከሚያጋጥሙት ነገሮች መካከል ደግሞ ‹‹ይሄው መታወቂያ አለኝ፤ ግን እከፍላለሁ:: ሐሳቡ ብቻ በራሱ ክፍያ ይገባዋል::›› የሚሉ መምህራን እንዳሉም ወጣቱ አጫውቶኛል::
በአሁኑ ወቅት መጠላላቱ እያለ እንዲህ መልካም የሚያደርጉ እንደ ወጣት ኒቆዲሞስ አይነቶች ያለምንም መስፈርት እና አድልዎ መስጠትን እያስተማሩ ናቸው:: እርሱ መልካምነት ለራስ እንደሆነ ይናገራል:: ወጣት ኒቆዲሞስ እንደሚለውም፤ ሁሉም ሰው ያለ ልዩነት አንድ ሆኖ መስራት አለበት:: ስለዘር የሚያወራ ሰው ያልሰለጠነ፤ አገርንም የሚያፈርስ ነው::
የቀድሞ መምህራን ለሶስትና አራት ሰዓት በእግራቸው እየሄዱ ትውልድን አስተምረዋል፤ እሱ ዛሬ ታሪክ ሆኗል:: ለእነዚህ መምህራን ግን ክብር ይገባቸዋል::
በዚህ ዘመን ያሉ አንዳንድ መምህራን ደግሞ ፀጉራቸውን እየቆጣጠሩ ሲያስተምሩ ይስተዋላሉ፤ አልፎ ተርፎ ተማሪዎቻቸውን ስነ ምግባር ሊያስተምሩ ይቅርና አብረው ከተማሪያቸው ጋር የሚጠጡና የሚቅሙ እንዲሁም የሚያጨሱ አሉ:: ለእነዚህ ደግሞ ማለት የሚቻለው ልቦና ይስጥልን ነው:: በእርግጥ በዚያው ልክ ደግሞ ጨዋና ቁርጠኞች ጎበዝ መምህራን ዛሬም ቢሆን መኖራቸው አይካድምና ለእነሱም ክብር ይገባቸዋል::
ወጣቱ፣ በያዘው ታክሲ በጎነቱን እንደሚቀጥል ይናገራል:: የተሻለ የሚገኝ ከሆነ ደግሞ በዚያው ልክ በጎነቱን ያሰፋል እንጂ እንደማያቋርጥ አረጋግጧል:: በእርግጥ በጎነት በመለገስ ብቻ አይለካም:: የዛሬ ዘመን ወጣት በስነ ምግባሩ መልካም መሆን በመቻሉ ብቻ ለቤተሰብ ብሎም ለአገር በጎ እንዳደረገ ይቆጠራል::
አዲስ ዘመን ነሀሴ 16/2011
አስቴር ኤልያስ