በሀገራችን ሴት እና ወንድ በመውለድ ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ። አመለካከቶቹ ከቤተሰብ አንስቶ እስከ ማህበረሰብ ድረስ ይዝልቃሉ። አንዳንዶች ወንድ ቢወለድ የሚመርጡ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ሴት መውለድን ይመርጣሉ። ወንድ ሲወለድ ጥይት የሚተኩስ ማህበረሰብም አለ። የእልልታ ልዩነትም ይስተዋላል አሉ፡፡
አንዳንዶች በተከታታይ ወንድ እና ሴት ይወልዱና ሩጫችንን ጨርሰናል ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ የወለዷቸው ሁሉ አንድ ጾታ ይሆኑባቸውና ‹‹አለ ግና›› ሲባሉም ይደመጣል። ልጆቻቸው ወንዶች ወይም ሴቶች ብቻ እየሆኑባቸው ሌላ ጾታ ፍለጋ ሲሉ የበርካታ ልጆች አባትና እናት የሆኑም ጥቂት አይደሉም።
አሁን አሁን ደግሞ በከተሞች የሚወለደው ወንድ ይሁን ሴት እየታወቀ ነው። በኛ ሀገር ሴት ልጅ መውለድ ፈልገው የተጸነሰችው ሴት መሆኗን ቢያውቁ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚታወቅ ነገር የለም። በዚህ የተነሳ ጾታ እንዲነገራቸው የማይፈልጉ እየበረከቱ ናቸው። ጤነኛ ይሁንልኝ ትሁንልኝ እንጂ ችግር የለውም የሚሉ በርካታ ናቸው። እንዲያም ሆኖ ግን የጾታ ጉዳይ ማነጋገሩን ቀጥሏል፡፡
ወደ ህንድ ብንሄድ ደግሞ ሴት ልጅ መውለድ የሚፈልግ የለም። ምክንያቱ ደግሞ ስታገባ ጥሎሽ መስጠት የሚጠበቅባት ሴት በመሆኗ ነው፤ ጥሎሹ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ በመሆኑም ቤተሰብን ለድህነት እስከ መዳረግ ይደርሳል ይባላል። በዘመኑ ቴክኖሎጂ የጽንሱ ጾታ መታወቁ ደግሞ ህንዶች ሴት ልጅ ከተጸነሰች ጽንሱን እንዲያቋርጡት ሁኔታዎች እንደተመቻቸላቸው ይገለጻል፡፡
በአደጉት ሀገሮች ደግሞ ጨርሶ የመውለድ ፍላጎት እየጠፋ ነው። የመውለድ ምጣኔው ያሳሰባቸው እነዚህ ሀገሮች ታድያ ልጆች ለሚወልዱ ቤተሰቦች የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ ቃል ሲገቡም ይሰማል። የልጅ ነገር ማነጋገሩን ቀጥሏል፡፡
በፓላንዱ አንድ ትንሽ መንደር በቅርቡ የሆነው ደግሞ የወንድ ልጅ ያለህ እያሰኘ ነው። ሜይጅስሲ ኦድርዛንሰከይ በምትባለው በዚህች መንደር የመጀመሪያ ደረጃ የእሳት አደጋ ሰራተኞችን ለማሰልጠን ተወዳዳሪዎችን መመዝገብ ይጀመራል። በዚህ ሂደት ላይ አንድ ሰው የሆነ መረጃ ይሰጣል። ይህ መረጃ ለመንደርዋ አዲስ ይሆናል። በትምህርት ቤቱ የሚታዩ ዩኒፎርም የለበሱ ወጣቶች በሙሉ ልጃገረዶች ናቸው ። ምክንያቱ በጣም አስገራሚ ሆኖ መገኘቱን ዘ ቴሌግርፍ በቅርቡ ይዞት የወጣ መረጃ ያመለክታል፡፡
መረጃው እንዳመለከተው ፤ በመንደሯ ለአስር ዓመታት ያህል ወንድ ልጅ አልተወለደም። የዓለም መገናኛ ብዙሃንም ጉዳዩን ከሰሙ አንስቶ በፓላድ ደቡብ ምስራቅ አርገው ችግሩ ተከስቶበታል የተባለውን አካባቢ ሁሉ ማሰሳቸውን መያያዛቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
‹‹መገናኛ ብዙሃኑ በአካባቢው ላይ ማተኮራቸው በነዋሪዎች፣ በአካባቢውና በእኛም ላይ ጭምር አግራሞት አሳድሮብናል›› ሲሉም እኚሁ የሁለት ሴት ልጆች አባት የሆኑት ከንቲባ ተናግረዋል።
የመንደሯ ከንቲባ በመንደሯ ወንዶች አለመወለዳቸውን እንደ ከፍተኛ እጥረት ቆጥረውታል። ከንቲባው ወንድ ልጅ ለሚወለድ ቤተሰብ የገንዘብ ድጋፍ ሽልማት ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ‹‹መገናኛ ብዙሃኑ ይህን ያህል በጉዳዩ ላይ በትኩረት መንቀሳቀሳቸው ለአካባቢው ህብረተሰብ እንዲሁም ለእኛ አዲስ ነገር ሆኖብናል›። ሲሉም ከንቲባ ራጅሙንድ ፍሪስችኮ ለዘ ቴሌግራፍ ተናግረዋል፡፡
በመንደሯ ወንድ ልጅ በመውለድ የመጀመሪያ ለሚሆነው ቤተሰብም የማበረታቻ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግም ነው ያረጋገጡት። በሚወለደው ወንድ ልጅ ስም ጎዳና እንደሚሰየም፣ በጣም የሚገርም ስጦታም እንደሚበረከትለት የኦክ ዛፍ ችግኝ ተተክሎለት በስሙ እንዲሰየም ይደረጋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
‹‹በመንደሯ የሚታዩት ህጻናትና ታዳጊዎች ልጃገረዶች ብቻ ናቸው፤ ሁላችንም በአካባቢያችን ይህንኑ እየተመለከትን ነው፤ እስከ አሁን ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጠነውም›› ያሉት ከንቲባው፣ ችግሩ የታወቀው ልጃገረዶች የተካተቱበት አንድ በጎ ፈቃደኛ የእሳት አደጋ መከላከያ ቡድን ለማቋቋም ምልመላ በተደረገበት ወቅት ጉዳዩ ያሳሰበው አንድ ነዋሪ የሰጠውን አስተያየት ተከትሎ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከንቲባው ከፓላንድ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ አካባቢው የመጡ ሀኪሞች በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ እንዲሰጧቸው ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሀኪሞቹ ወንዶች መውለድ ሊበረታታ የሚችልበትን መንገድ በመፈለግ በኩል አብረው ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸውም ዘገባው ጠቁሟል።
‹‹ወንድ ልጅ መውለድ የሚፈለግ መጥረቢያ ከፍራሽ ስር አርጎ ሁሌም መተኛት አለበት ››ሲሉ አንድ በጡረታ የተገለሉ ሀኪም የፓላንድ ተራራማ አካባቢ ነዋሪዎችን አባባል በመጥቀስ በቀልድ መልክ ተናግረዋል። ሀኪሙ የሚወለደው የጾታ አይነት እናቲቱ ነፍሰጡር በነበረችበት ወቅት ከምትጠቀመው ምግብ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ጠቅሰው፣ ወንድ ልጅ እንዲወለድ ከተፈለገ በካልሲየም የበለጸገ ምግብ መመገብ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአካባቢው አስተዳዳሪና የሁለት ሴት ልጆች እናት የሆኑት ክሪይስቲና ዚይድዛይክ ይህን ጉዳይ በትኩረት መመልከት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ‹‹ተፈጥሮ ነገሮች ሁሌም ሚዛናዊ እንዲሆኑ መንገዶችን ታዘጋጃለች፤ እዚህ በርካታ ሴቶች ሊወለዱ ይችላሉ፤ በዓለም ሌላ አካባቢ ደግሞ በርካታ ወንዶች ሊወለዱ ይችላሉ›› ሲሉም ጉዳዩ ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 14/2011
ዘካርያስ