የትምህርት ጥራቱና አግባብነቱን ማረጋገጥና ጉድለቶችን ለመሙላት መወሰድ የሚገባዉን የማስተካከያ እርምጃ ሳይውል ሳያድር ለመውሰድ መዘጋጀቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ዛሬ በሸራተን ሆቴል እየተካሄደ በሚገኘው የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የለውጥ ስራዎችን ማስጀመሪያ መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስተር ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም ተቋሞቻችንንና የትምህርት ስርአታችንን በየጊዜዉ በመፈተሸ ከሀገራችን የልማት ፍላጎትና ከአለማቀፍ ሁኔታዎች ጋር እያጣጣምን ለዘመኑ የሚመጥን ብቁና ተወዳዳሪ በስነምግባር የታነጸ ዜጋ መፍጠር የሚያስችለንን ሁኔታ ማመቻቸት ለነገ የሚባል ስራ እንዳልሆነ እንረዳለን ያሉት ፕሮፌሰር ሂሩት የትምህርት ጥራቱና አግባብነቱን ማረጋገጥና ጉድለቶችን ለመሙላት መወሰድ የሚገባዉን የማስተካከያ እርምጃ ሳይውል ሳያድር እንወስዳለን ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር ሂሩት ጉባኤዉ የተዘጋጀው በ2012 የትምህርት ዘመን ልንገባባቸዉ ያቀድናቸዉን የትምህርት ፍኖተ ካርታዉንና በቀጣይም የተደረጉ ጥናቶችን መሰረት ያደረጉ የከፍተኛ ትምህርት የለዉጥ ስራወችን ለማቅረብና የጋራ ለማድረግ ተግባብተንባቸዉና ግልጽነት ፈጥረን ሁላችንም የየበኩላችንን ድርሻ መወጣት እንድንቸል ነዉ ብለዋል፡፡
ትምህርት የአስተሳሰብንና የአመለካከትን ልህቀት፣ የሰብዕናን ብስለት፣ የልብንና የአእምሮን ስፋት፣ የእኔነትን ድንበር በማስፋት ከራስ ባለፈ ለሌሎች መኖርን፣ ምክንያታዊ እይታንና ሚዛናዊነትን ለማዳበር የሚያስችል ወሳኝ ቁልፍ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ሂሩት የትምህርት ፋይዳው ዜጎችን በማህበራዊ፣ ስነ-ባህሪያዊ፣ አካላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሙያዊና አእምሯዊ አቅም እንዲጎልብቱ፣ እንዲለሙና የላቁ እንዲሆኑ አካባቢያቸዉን ሀገራቸዉን ብሎም አለምን በበጎ እንዲለዉጡ ማስቻል ነው ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር ሂሩት በንግግራቸው ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የከፍተኛ ትምህርት ከነበረበት ዝቅተኛ ምጥኔ ሽፋኑ እንዲጨምር ለማድረግ በተደረገው ጥረት በአሁኑ ወቅት በመንግሥት የሚተዳደሩ ዩኒቨርስቲዎች ቁጥር 50 የደረሰ ሲሆን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት 4ቱን ዩኒቨርስቲዎች ጨምሮ ኮሌጆችና የኒቨርሲቲ ኮሌጆች 200 መድረሳቸውን ጠቁመዋል።
ሚኒስትሯ ለበርካታ ወጣቶች የትምህርት እድል መፍጠር ቢቻልም ከሕዝባችን ብዛትና አገሪቱ ከምትሻው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን አንጻር የጥቅል ቅበላችን በቂ ቁጥር ነው የሚባል አይደለም ብለው ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ጋርም በጥቅል ቅበላ ስትወዳደር ገና መሆኗን አስረድተዋል፡፡
ከፍተኛ ትምህርት አሁንም የአቅርቦት፣ የፍትሀዊነት የጥራትና የተገቢነት ችግር ያለዉ በመሆኑ ተቋማትን ከመገንባት ባለፈ በርካታ ጥራትና አግባብነትን የማስጠበቅ ስራዎች እንደሚጠበቁ ገልፀው ቀጣይ የትምህርት ሥርዓቱ እንዲሻሻል በመታመኑ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ጥናት ተካሂዶ በሰነዱም ላይ በሀገር ደረጃ (በሁሉም ክልሎች፣ ከተማ መስተዳድሮችና በፌዴራል ባሉ ሴክተሮች) ከምሁራን፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ከሕዝብ ጋር ግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይቶች ሲካሄዱበት መቆየታቸዉን አስታውቀዋል፡፡
ባለፉት 6 ወራት ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከፌደራል ሙያና ቴክኒክ ተቋም ፣ከከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂክ ማእከል እና ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተውጣጡ 2 የጥናት ቡድኖችን በማደራጀት ሙሉ ጊዜቸዉን እንዲሰጡን ከየተቋማቸውና የስራ ክፍላቸው ትብብር በመጠየቅ ከኛ ጋር በመሆን በሁለቱ ዋና ዋና የለውጥ ጉዳዮች ማለትም በስርአተ ትምህርት ክለሳና የአንደኛ አመት ትምህርት ዝግጅት እንዲሁም ተቋማትን በተልእኮ የማደራጀት ስራዎች ላይ 34 ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ትኩረት ሰጥተዉ ሰፊ ጥናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል ነውያሉት ሚኒስትሯ፡፡
ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመጡ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች በሚጠበቀዉ ደረጃ ትምህርታቸዉን ለመከታተል የሚያስችል መሰረታዊ ክህሎትና እዉቀት ይዘዉ ያለመገኘታቸዉና ተመርቀው ሲወጡም የብቃትና የክህሎት ክፍተቶች የተግባቦትና የምክንያታዊነት ክህሎት ውስንነት የሚታዩባቸው፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ያለማወቅና ያለመረዳት ሁኔታ የሚስተዋልባቸው፤የስራ ፈጠራ ዝግጅትና ተነሳሻነት ውስንነት እንደለባቸው፣የስነምግባርና የግብረገብነት ሕጸጾች የሚስተዋሉባቸው መሆናው ስርዓተ ትምህርቱ መፈተሽና መቃኘት እነዚህን የእውቀት የክህሎትና አስተሳሰብ ክፍተቶች የሚሞላ ስርዓት ትምህርት እንደሚያሰፈልገዉ ከፍኖተ ካርታዉም በተጨማሪ በሌሎች ጥናቶችም ጭምር አስረግጠው አሳይተዋል ተብሏል፡፡
በዚህም መሰረት በአእምሮ የጎለመሱ፣ በሙያቸው የበቁ፣ በመንፈሳቸው የተረጋጉ፣ በስነባህሪያቸው የበሰሉ፣ ምክንያታዊና ሚዛናዊ የሆኑ ስነምግባር ያላቸዉ የአገራቸውንና የማህበረሰባቸውን ታሪክና እሴቶች አዉቀዉ በማክበርና በመጠበቅ ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ለሀገራቸው እድገትና ለሕዝባቸው ልእልና የሚተጉና ለአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ከመዘጋጀት አልፈው የቴክኖሎጅ ፈጣሪዎች፣ አልሚዎች፣ ተግባሪዎች የሚሆኑ ዜጎችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብሎ በትምህርት ሙያና በሌሎች ዘርፎች ምሁራን በጥናት የተለዩና በየደረጃዉ ሰፊ ዉይይቶች የተካሄደባቸዉና ስምምነት የተገኘባቸዉን የኮርሶች ስብስቦች ከነይዘታቸዉ ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩት ፕሮፌሰር ሂሩት ከዩኒቨርስቲ አመራሮችና ማህበረሰብ አባላት ጋር በተለይ ኮርሱን የሚሰጡ ባለቤት የትምህርት ክፍሎች ጋር ሰፊ ውይይት እንደተደረገባቸው ገልፀዋል፡፡
የወጣቶቻችንን ብቃት ሊያድብሩ የሚችሉ ሰርዓተ ትምህርቶች እየተቀረጹ፣ አስፈላጊዎቹ የትምህርት ግባቶች እየተሟሉ፣ ዩኒቨርሲቲዎች በየተለዩባቸው መስኮች እንዲጠናከሩ እየተደረገ፣ የኢኮኖሚ ልማትና የህዝቡ ብልጽግና እንደሚረጋገጥ እምነታቸውን የገለፁት ሚኒስትሯ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በ2012 ሰላማዊ መማር ማስተማርን ከማስፈን አኳያም ሁሉንም ተዋንያን ሃላፊነት እንዲወስዱ የሚያረግ አዳዲስ አሰራር ስርአቶችን ለመዘርጋት ጥናቶች ማስጠናቱንም ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ሚኒስትሮች፣ የቦርድ አመራሮች፣ የፌደራልና የክልል መንግስታት የስራ ሃላፊዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል፡፡