በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መስከረም ላይ ተውበውና ማራኪ ሆነው ተማሪዎችን ለመቀበል ዕድሳት ላይ ናቸው። በምልከታችንም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ቀለም ሲቀቡ፣ የተጎዱ ጣሪያዎቻቸውን በአዲስ ቆርቆሮ ሲተኩ፣ በረጅም ጊዜ አገልግሎት የተቆፋፈሩ ወለሎችን ሲያስተካከሉ ተመልክተናል። የ488 ትምህርት ቤቶች ዕድሳትም እስከመጪው መስከረም ወር ድረስ የሚጠናቀቅ መሆኑን ጥገናውን እያካሄዱ ያሉ ሥራ ተቋራጮችና ማህበራት ገልጸውልናል።
የመንግሥት ቤቶች ዕድሳት፣ የምገባ መርሀ ግብርና የመማሪያ መሳሪያዎች ለመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ድጋፍ መደረጉ ለመማር ማስተማሩና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማፍራት ትልቅ ትርጉም እንዳለው የሚገልጹት የመስከረም አጸደ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ጣዕመ ካህሳይ፤ ተማሪዎች በለጋ ዕድሜያቸው ሁሌም የማይማርክና ያረጀ ትምህርት ቤት እያዩ መማር አስልቺ መሆኑን ይገልጻሉ። ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ›› እንደሚባለው ያረጁት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ታድሰው ለዕይታ ማራኪ ሲሆኑ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ተደስተውና ጓጉተው ትምህርት ቤት እንዲመጡ ያደርጋቸዋል ይላሉ። ሥራው ለትምህርት ጥራት መሻሻል የራሱን ድርሻ ይወጣል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
አቶ ካህሳይ እንደሚሉት፤ ትምህረት ቤቱን ከሁለት ዓመት በፊት ለማሳደስ ጨረታ የወጣ ቢሆንም የዕድሳት ዋጋው የማይቀመስና ከትምህርት ቤቱ አቅም በላይ በመሆኑ ጨረታው ተሰርዟል። አሁን እየተደረገ ባለው ዕድሳትም ያረጁና የተበሉ ቆርቆሮዎች፣ አሸንዳዎች እየተቀየሩ ይገኛሉ። ግድግዳው ቀለም እየተቀባ፣ በቆርቆሮ የነበረው የመምህራን ማረፊያ ፈርሶ በብሎኬት እንደ አዲስ እየተሠራና የተፈነቃቀሉ ወለሎች የማስተካከል ሥራ እየተከናወነ ነው።
በምገባ መርሐ ግብሩ የተጠቃሚ ብዛት ማደጉ ለመንግሥት ተማሪዎች፣ ወላጆቻቸውና ለመምህራንም የብስራት ዜና መሆኑን የሚገልጹት አቶ ካህሳይ፤ ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ምግብ ሳይመገቡ ይመጡ እንደነበረና ራሳቸውንም ስተው የሚወድቁበት አጋጣሚ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህም መምህራን ከኪሳቸው በማዋጣት ጭምር ተማሪዎችን ይረዱና እንዲማሩ ያግዙ እንደነበር በመጠቆም፤ በዚህ መልኩ ስትረዳ የነበረች አንዲት ተማሪ በችግር ምክንያት እናቷ ማረፋቸውን ይገልጻሉ። የምገባ መርሐ ግብሩ በመንግሥት መጀመሩም የመምህራንን ጫና የሚያቃልል፣ ሕፃናትን ከሞት የሚታደግና ለወላጆችም እፎይታን የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።
ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ዕድሳቱ እየተካሄደ የሚገኘው የዳግማዊ አጼ ምኒልክ መሰናዶ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ሀድራ ኑሪ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የትምህርት ቤቶች ዕድሳት መካሄዱ ተማሪዎች በማራኪ፣ ሳቢና ምቹ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲማሩ ያደርጋል። ትምህርት ቤቶቻቸው ናፍቀዋቸው እንዲመጡና እዚያው ቆይተው እንዲያጠኑም የሚያደርግ ነው። መምህራንም ደስ እያላቸው በጊቢው እንዲቆዩና ተማሪዎችንም እንዲያግዙ ያስችላል። ይሄም ተማሪዎች በስነ ምግባርና በዕውቀታቸው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
ሆኖም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው ዝቀተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ልጆች መማሪያ እንደመሆናቸው፤ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም በመሰናዶ ትምህርት ቤቶችም ሊተገበር ይገባል። ምክንያቱም ትምህርት እስኪጠናቀቅ ድረስ የምሳ ዕቃ ይዘው የማይመጡና ካፊቴርያም ገብተው ምሳ የማይመገቡ ተማሪዎች ቁጥር ቀላል የማይባል ነው። በዚህም ከለጋሽ ባለሀብቶች ጋር በመተባባር ለ42 ተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብር ሲከናውን ቆይቷል። በመሆኑም መርሐ ግብሩ በመንግሥትም ሆነ ባለሀብቶች አማካኝነት ቢሰፋ ትምህርት ተጠናቆ ወደ ቤታቸው እስኪሄዱ ድረስ ምሳና ቁርስ የማይበሉ ተማሪዎችን ማካተት ይቻላል።
የዳግማዊ አጼ ምኒሊክን መሰናዶ ትምህርት ቤት ዕድሳት እያከናወነ ያለው የሳራ ኮንስትራክሽን ፎርማን ሙዲን ሰይድ እንደሚለው፤ ዕድሳቱ የተጎዱ ቆርቆሮዎችን የመጠገን፣ የተቆፋፈሩ ወለሎችን የማስተካከል፣ ቀለም የመቀባትና የሚያፈሱ አሸንዳዎችን የመቀየር ሥራዎችን ያካተተ ነው። የጥገና ሥራውም ታሪካዊ ቅርስነቱን በጠበቀ መልኩ የሚከናወን ሲሆን፤ በአንድ ወር ለማጠናቀቅ ከ50 በላይ በሆኑ ባለሙያዎች ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ፣ በክረምቱ መርሐ ግብር የዝግጅት ምዕራፍ 488 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታና ገፅታቸውን ለመማር ማስተማር ምቹ ለማድረግ የዕድሳት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ያብራራሉ። 729 ሚሊዮን ብር በከተማ አስተዳደሩ ተመድም ከአጸደ ሕፃናት እስከ መሰናዶ ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶችን የዕድሳት ሥራ እንዲያከናውኑ 656 ማህበራትና ሥራ ተቋራጮች ተለይተው ሥራ ጀምረዋል።
የመጀመሪያው ዙር የእድሳት ሥራም እስከ መስከረም ወር ድርስ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ፤ በሁለተኛው ምዕራፍም አጥር፣መጸዳጃ ቤት፣ምድረ ግቢውን የማስዋብና የማደስ ሥራ የሚሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም በሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ያሉ የተሰበሩ ወንበሮችን፣ ጥቁር ሰሌዳዎችን፣የቤተ ሙከራ ቁሳቁሶችን የመጠገን ሥራን በማከናወን ሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ምቹ፣ማራኪና ሳቢ እንዲሆኑ እንደሚደረግ አብራርተዋል።
ከከተማ አስተዳደሩ በተጓዳኝ የተወሰኑ የግል ተቋራጮች ትምህርት ቤቶችን ለማደስ በገቡት ቃል መሰረት ዕድሳቱን እያከናወኑ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል ዳግማዊ አጼ ምኒልክ መሰናዶ፣ ግንቦት 20ና ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል። ይህ ተግባርም የሚበረታታና ለትውልድም የሚተርፍ ሥራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በሌላ በኩል በ240 ሚሊዮን ብር ያህል ወጪ ከ450 ሺ እስከ 600 ሺ ለሚጠጉ ተማሪዎች የደንብ ልብስ በታዋቂ ዲዛይነሮችና ልብስ ስፌት ፋብሪካዎች የማዘጋጅት ሥራ እየተሠራ ነው። ከአጸደ ሕፃናት ጀምሮ እስከ መሰናዶ ደረጃ ያሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የደንብ ልብስ እየተዘጋጀ ሲሆን የሁሉም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በደረጃ የተለያየ ቢሆንም አንድ ዓይነት መሆኑን ገልጸዋል። ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው ስም ባለበት ባጅ ብቻ የሚለያዩ ሲሆን የደንብ ልብሱ ተመሳሳይ መሆኑ አንድ ዓይነት የተማሪ ማህበረሰብና ቅርርብ ለመፍጠር እንደሚረዳ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ለተማሪዎች ደብተር፣ እስክሪፕቶ፣ መቅረጫና ማንኛውንም የትምህርት ቁሳቁስ በከተማ አስተዳደሩ በኩል በነፃ የሚሰጥ ይሆናል። በዚህም ለሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ደብተር የሚያስፈልግ ሲሆን፤ እስከአሁን በከንቲባ ጽሕፈት ቤት በኩል ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ከሦስት ሚሊዮን በላይ ደብተሮች ተሰብስበዋል። በመሆኑም ከወላጆች የሚጠበቀው ልጆቻቸውን እንዲማሩላቸው ወደ ትምህርት ቤት መላክ ብቻ መሆኑን ምክትል ኃላፊው አስረድተዋል።
በምገባ መርሐ ግብሩም 300 ሺ የሚደርሱ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን ቁርስና ምሳ ለመመገብ ዕቅድ ተይዟል። በዚህም ተማሪዎችን ከመመገብ ባለፈ አነስተኛ ገቢ ያላቸው እናቶች ተደራጅተው ለተማሪዎቹ ምግብ እንዲያዘጋጁና እንዲያቀርቡ ይደረጋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም አስፈላጊ ቢሆንም ከመንግሥት አቅም አንጻር በረጅም ጊዜ ዕቅድ ሊሳካ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ ሌላው ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ የወንድ ተማሪዎች በገላን ቁጥር አንድና ለሴቶች ደግሞ የካቲት 12(መነን)አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ ይደረጋል። ነሐሴ መጨረሻ ደግሞ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች በከንቲባው ጽሕፈት ቤት ወጪ በዓለም አቀፍ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲማሩ ዕድል ይከፈትላቸዋል። እነዚህ ነገሮች ወላጆች ልጆቻቻውን በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲያስተምሩ የሚያበረታቱ ናቸው።
በሌላ በኩል በ2011 የትምህርት ዘመን በመንግሥት ትምህርት ቤቶች 410 ሺህ ተማሪዎች የነበሩ ሲሆን በ2012 ደግሞ ወደ 600 ሺ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል። በመሆኑም የፈረቃ ትምህርት የሚሰጥባቸው የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ኃላፊው ጠቁመዋል።
እነዚህ ሥራዎችንና ሌሎች ተግባራትን በማቀናጀት የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን አቅም ከግል ትምህርት ቤቶች አቅም ጋር ተመጣጣኝ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ የጠቆሙት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፤ በግል ትምህት ቤቶች የሚታየውን ልጓም ያጣ የክፍያ ጭማሪን በመንግሥት ትምህርት ቤቶችን አቅም በማሳደግ መከላከል ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 29/2011
ጌትነት ምህረቴ