
አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ለሕግ ማስከበር ሥራ አራት የሠለጠኑ አነፍናፊ ውሻዎችን ወደ ሥራ ማስገባቱን ገለጸ። ውሾቹ ሕገወጥ አደንን ለመቆጣጠር ዓይነተኛ ሚና እንዳላቸው አስታወቀ።
በባለሥልጣኑ የዱር እንስሳት እና ውጤቶቻቸው ዝውውር ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዳንኤል ጳውሎስ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ሀገራችን የተለያዩ የዱር እንስሳት እና እጽዋቶች መገኛ ናት።
በተለይም የዱር እንስሳቱ ለቱሪዝም ዘርፉ የሚያበረክቱትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ተጨባጭ ለማድረግ፤ ሕገወጥ አደንን መከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጁነት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የዱር እንስሳቱ አሁን ላይ የሕልውና ስጋት ወድቆባቸዋል ያሉት አቶ ዳንኤል፤ በሕገ ወጥ መንገድ የዱር እንስሳት ይታደናሉ፤ ከታደኑ በኋላ ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ፣ ከሀገር ይወጣሉ ብለዋል።
ከሀገር የሚወጡበት በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል መሆኑን ያመለከቱት ባለሙያው፤ ችግሩን ለመቆጣጠር ኤርፖርት ያለውን ቁጥጥር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ለእዚህም የሰለጠኑ አነፍናፊ ውሻዎች ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ውሾቹ በዘርፉ ላይ እየተሠራ ላለው ነባር የጥበቃ እና የሕግ ማሕቀፍ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ያነሱት ባለሙያው፤ ለእዚህ ተግባር ውሾች የተመረጡት ተፈጥሮአዊ የማሽተት አቅማቸው መሆኑን አንስተዋል።
ውሾች በሥነ ሕይወት እንደተረጋገጠው፤ የሰው ልጅ ማሽተት ከሚችለው መቶ ሺ እጥፍ የማሽተት ችሎታ እንዳላቸው ገልጸዋል። አገልግሎታቸው ዘርፉ ላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው ያሉት አቶ ዳንኤል፤ በተለይ ሕገ ወጥነትን ከመከላከል፣ ከመቆጣጠር አኳያ የላቀ ሚና አላቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ መቶ ሰማንያ አምስት ሀገራት የፈረሙት ስምምነት መኖሩን አመልክተው፤ ስምምነቱ ሕጋዊ ዶክመንት የሌላቸውን ሕገ ወጦች በመቆጣጠር በጋራ ለመሥራት እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
የጋራ ትብብር ለሁለንተናዊ ጥቅም ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ እንደ ምሳሌም ሕገወጦች ከኢትዮጵያ ዝሆን ገለው ጥርሱን ወደሌላ ሀገር ይዘውት ቢሄዱ በስምምነቱ መሠረት ወንጀለኞቹ ባሉበት ሀገር እንደሚያዙ አመልክተዋል።
ሕግን ከማስከበር ረገድ እንደ ፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊሶች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት፣ ኢምግሬሽን፣ ኢንተርፖል ያሉ አካላት አብረዋቸው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ከሕግ አስከባሪ ተቋማት በተጨማሪም እንደ ግብርና ሚኒስቴር፣ ብዝሀ ሕይወት ያሉ ተቋማት አብረዋቸው በመሥራት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም