መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ወደ ሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የማስፋት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

10ኛው የአፍሪካ ሲቪል ሰርቪስ ቀን “ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን ቅልጥፍና እና ጽናትን በማሳደግ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን መሙላት” በሚል መሪ ሃሳብ በአፍሪካ ኅብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ትናንት መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደተናገሩት፤ መንግሥት ሰባት ምሶሶዎችን መሠረት አድርጎ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን እያከናወነ ነው። በእዚህም አዲስ እና ልዩ ተቋማዊ መዋቅር የመገንባት፣ የሰው ሀብት አስተዳደርን የማዘመን እና ዲጂታላይዜሽን ይበልጥ ማጠናከር ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

ይህም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአገልግሎት አሠጣጥ ማሕቀፍን ተግባራዊነት የምናረጋግጥበት ነው ያሉት አቶ ተመስገን፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ታሪካዊ ጉድለቶችን እና ክፍተቶችን እየሞላን፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን ወደ ሁሉም የሀገራችን ማዕዘናት እያዳረስን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ወደ ሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የማስፋት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ እያደገ የመጣው የቴክኖሎጂ እድገት፣ ግጭቶች እና ተገማች ያልሆኑ ጉዳዮች በተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ፈተናዎችን እየደቀኑ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል መተማመንን ለማጎልበት አካታችና ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባም ተናግረው፤ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውጤታማ፣ አካታች፣ ልዩና ተወዳዳሪ አገልግሎቶችን በማቅረብ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እየተሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአጀንዳ 2063 የተቀመጡትን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት እና በአፍሪካ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት አገልግሎትን ማዘመን ይገባል ሉት አቶ ተመስገን፤ ዛሬ ላይ ተቋማትን ማዘመንና የአገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋፋት ከቻልን ለቀጣዩ ትውልድ መሠረት እያስቀመጥን ነው ብለዋል።

በተጨባጭ ራዕይ እና በትጋት መሥራታችን ውጤት እያስመዘገበ ነው። ዜጎቻችን በክብር እየተስተናገዱ መሰናክሎችን እየቀነስን እንገኛለን ሲሉም ገልጸዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ተወዳዳሪ እና ቀጣይነት ያለው የሲቪል ሰርቪስ ተቋም ለመገንባት ውይይትና ልምድ ልውውጥ አስፈላጊ ነው። በእዚህም በአፍሪካ የመንግሥት አገልግሎትን ለማጎልበት ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር ፍትሐዊነትን ማስፈን ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ ሲቪል ሰርቪስ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ትብብር ለማጠናከር እንደሚያግዝ እና በአፍሪካ አካታች የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን ለማቀላጠፍ አህጉራዊ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን መሶብ የአንድ ማዕከል የተሰኘ የዲጅታል አገልግሎት ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝም ገልጸዋል።

መሶብ በተለይም ሴቶች፣ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች በአንድ አካባቢ የመንግሥት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You